1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንጎ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 10 2008

ዴኒ ሳሱ ንጌሶ ካለፉት 31 ዓመታት ወዲህ በኮንጎ በሀገሪቱን ከፍተኛ ስልጣን ላይ ላይ ይገኛሉ። እጎአ መጋቢት 20፣ 2016 ዓም በኮንጎ ሬፓብሊክ በሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫም ላይ በስልጣን ለመቆየት የሚፈልጉት ዴኒ ሳሱ ንጌሶ የስልጣን ዘመናቸው በሰባት ዓመታት እንዲራዘምላቸው በነገው ዕለት፣ እንደገና በተወዳዳሪነት ቀርበዋል።

https://p.dw.com/p/1IG02
Kongo Präsident Denis Sassou Nguesso
ፕሬዚደንት ዴኒ ሳሱ ንጌሶምስል picture-alliance/AA/A. Landoulsi

[No title]

የኮንጎ ሬፓብሊክ ሕዝብም እንደሚመርጣቸው አያጠራጥም፣ ይላሉ በፕሬዚደንቱ የምርጫ ዘመቻ ውስጥ የተጠቃለሉት የወጣቶቹ ፓርቲ ቃል አቀባይ ቤርናዲን ጋቬ ።

«አንድ ሰው እውር ካልሆነ በስተቀር በሀገሪቱ የተገነቡትን አዲሱን የአየር ማረፊያ እና መንገዶች፣ ባለወረቶችን ለመሳብ ከነሱ ጋር የተደረጉ ውሎችን ማየት ይችላል።»

ሳሱ ንጌሶ ራሳቸውን የሰላም እና የልማት ዋስትና አድርገው ይመለከታሉ። በድረ ገጻቸው በመላይቱ ኮንጎ 17,000 ኪሎ ሜትር መንገድ መሰራቱን ለራሳቻቸው እንደ ማስታወቂያ አቅርበዋል። ሳሱ ንጌሶ እጎአ ከ1979 ዓም እስከ 1992 ዓም ድረስ፣ ከዚያ ከአምስት ዓመት መቋረጥ በኋላ ከ1997 ዓም ወዲህ ስልጣን ላይ ይገኛሉ። በተቃዋሚዎቻቸው አስተያየት እነዚህ አሰርተ ዓመታት በፖለቲካውም ሆነ በልማቱ ውጤት ያልተመዘገበባቸው ናቸው ሲሉ አንድ የሳሱ ንጌሶ ተፎካካሪ የሆኑኑት የዦን ማሪ ሚሼል ሞኮኮ ደጋፊ አማረዋል።

« አምባገነናዊ አገዛዝ የሰፈነበት ጊዜ ነው። ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ አባቶቻችን ሳይቀሩ ስራ አጥ ናቸው። የስራ አጥነቱ መጠን እየጨመረ ነው የሄደው። በዚህ ሁኔታ በጣም ተሰላችተናል። ቀድሞ እንደነበረችው የተሻሻለች ኮንጎን ማየት እንፈልጋለን። »
የሞኮኮ ደጋፊ በዚሁ አነጋገራቸው እጎአ በ1992 እና በ1997 ዓም መካከል ሀገሪቱ በፕሬዚደንት ፓስካል ሊሱባ የስልጣን ዘመን የተዳደረችበትን ጊዜ ማለታቸው ነው። እንደ ደጋፊው አስተያየት በዚሁ ጊዜ በኮንጎ ይሰራበት ነበር ያሉት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሀገሪቱ የርስበርሱ ጦርነት እስከተቀሰቀሰበት እና ዴኒ ሳሱ ንጌሶም ለሁለተኛ ጊዜ ስልጣኑን በኃይል እስከያዙበት ጊዜ ድረስ ቀጥሎ ነበር። በ1990ኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ በኮንጎ ታይቶ የነበረው ዴሞክራሲያዊ አሰራር ካከተመለት ብዙ ጊዜ መሆኑን በሀምበርግ የሚገኘው የአርኖልድ ቤርግሽትሬሰር የፖለቲካ ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ክፍል ባልደረባ አንድሪያስ ሜለር አመልክተዋል።

«በኮንጎ አለ የሚባለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለይምሰል የተተከለ ነው። ብዙ ፓርቲዎች እና ምርጫ የሚፈቀድበት፣ ብሎም የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ያለ ይመስላል፣ ግን፣ ገሀዱ ሀቀኛ ምርጫ የሚባል ነገር የለም። ገዢው ፓርቲ እና የፕሬዚደንት ሳሱ ንጌሶ ጎሳ አንጃ ሀገሪቱን የሚገዙት እና ከሀገሪቱም ሀብት ኤኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያገኙት።»


አንድሪያስ ሜለር እንዳስታወቁት፣ ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ በሳሱ ንጌሶ አንፃር በተፎካካሪነት ከቀረቡት ሰባት እጩዎች መካከል ብዙዎቹ ከመንግሥት ጋር ቅርበት ያላቸው እና ለይስሙላ የቀረቡ ናቸው።

ከፕሬዚደንታዊ እጩዎች በጠቅላላ ለፕሬዚደንቱ ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉት «ዢ ትሯ ኤም» በሚል ምህፃር የሚታወቁት የተቃዋሚው ቡድን ተወዳዳሪ ዦን ማሪ ሚሼል ሞኮኮ ዋነኛው ናቸው። የቀድሞ የጦር አባል እና የመንግቱ ባለስልጣን ሞኮኮ የውስጥ አዋቂ በመሆናቸው ለመንግሥቱ አደገኛ በመሆናቸውም መንግሥት ምን ያህል እጩነታቸውን ለማከላከል ወደኋላ እንደማይል አንድሪያስ ሜለር አስረድተዋል።

Kongo General Jean-Marie Michel Mokoko
ጀነራል ዦን ማሪ ሚሼል ሞኮኮምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo

«ጀነራል ሞኮኮ ቀድሞ የፕሬዚደንት ሳሱ ንጌሶ የቅርብ አማካሪ ሆነው ሰርተዋል። ሞኮኮ በጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓም መጀመሪያ ላይ በ2016 ዓም መጀመሪያ ላይ ነበር በእጩነት ለመቅረብ የወሰኑት። ከዚያ ጥቂት ቆይቶ ሞኮኮ የመፈንቅለ መንግሥት ሴራ ሲያቅዱ ያሳያል የተባለ አንድ ቪድዮ ወጣ፣ ይህ እንዲያው ያጋጣሚ ነገር አልነበረም። ወዲያው ሞኮኮ ላጭር ጊዜ ታስረው መፈታታቸው የሚታወስ ነው።»

የተቋቋሚ ኮሚቴ ወይም በምህጻሩ «ክራክ» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የተቃዋሚ ፓርቲ ሊቀ መንበር ሮማ ቤዴል ሱሳ እጩ ሆነው የመቅረብ እቅዳቸው የምርጫ ዘመቻው ሳይጀመር ገና ወዲያው ነበር ያበቃው። በፈረንሳይ ሀገር የሚኖሩት ሱሳ ባለፈው ጥር ወር ወደ ኮንጎ በመመለስ በእጩነት ለመቅረብ የሚጠየቀውን ቀብድ ከባንክ ሂሳባቸው አውጥተው ለማስያዝ ሲሞክሩ፣ የባንክ ሂሳብ እንደሌላቸው ይነገራቸዋል፣ ይህን ለማጣራት ያደረጉት ሙከራም በቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ ከተጓተተ በኋላ በእጩነት የመቅረብ እቅዳቸውን እንደተው ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። እርግጭ የተቃዋሚ ቡድኖች ባለፈው ጥር አንድ ትልቅ ህብረት ቢፈጥሩም በአንድ የጋራ እጩ ላይ መስማማት ያልቻሉበት ድርጊት በፕሬዚደንቱ አንፃር የመፎካከሩን እና የማሸነፉን እድላቸውን አጥቦታል።

Brazzaville Kongo Wahlen Wahlkampf
ምስል Getty Images/M.Longaria

የኮንጎ ሕዝብ ባለፈው ጥቅምት ወር ባካሄደው ሬፈረንደም ነበር ሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ እንዲደደረግበትና ፕሬዚደንት ሳሱ ንጌሶም ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን እንዲወዳደሩ መንገዱን ክፍት ያደረገላቸው። ከሕዝበ ውሳኔው ውጤት በኋላ ኮንጎ ብራዛቪልን እጎአ ከ1979 ዓም ወዲህ፣ ብሎም ካለፉት 31 ዓመታት ወዲህ በመምራት ላይ የሚገኙት ፕሬዚደንት ሳሱ ንጌሶ በትዊተር ባስተላለፉት መልዕክት የኮንጎ ተወላጅ በመሆናቸው የሚሰማቸውን ኩራት ገልጸዋል።

የሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ሬፈረንደም 90% የመራጩን ድምፅ አግኝቶ ነው ያለፈው፣ ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ ወቀሳ ቢፈራረቅበትም። ሕዝበ ውሳኔው በተካሄደበት ሰሞን በታየው ተቃውሞ ወቅት በተፈ,ጠረ ግጭት፣ ቢያንስ አራት ሰዎች ሲሞቱ፣ በርካታ የተቃዋሚ ቡድኖች ፖለቲከኞች በቁም እስር ውለዋል። በሀገር ውስጥ ተቃውሞ የገጠማቸው ንጌሶ ግን ራሳቸውን ውዝግብ በሚታይበት አካባቢ ሰላም ለማውረድ የሚጥሩ ሸምጋይ አድርገው ለማቅረብ ታትረው እየሰሩ ነው፣ በአንድሪያስ ሜለር አስተያየት።

Karte Republik Kongo
ምስል DW

«ባካባቢው ተሰሚነት ያገኙ የሀገር መሪ ሆነው ይታያሉ። የጋቦ ፕሬዚደንት ኦማር ቦንጎ ከሞቱ በኋላ ለማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውዝግብ መፍትሔ በማፈላለጉ ረገድ ዋነኛ የሸምጋይነት ሚና መጫወት ጀምረዋል። ይህ ሊሆን የቻለው ግን ባካባቢው ሀቀኛ የሚባሉ ቢያንስ በስልጣና የሚገኙ ዴሞክራቶች ጥቂቶች በመሆናቸው ብቻ ነው፣ በመንግሥታዊ አስተዳደራቸው በወቅቱ በሚታየው መረጋጋት የተነሳ ይህንኑ የሸምጋይነት ሚና ሊይዙ ችለዋል።»

ይሁንና፣ ኮንጎ በዋነኝነት በንግድ ወደ ውጭ የምትልከው የነዳጅ ዘይት ምርት ዋጋ በዓለም ገበያ እየቀነሰ የመጣበት ድርጊት የሀገሪቱን ድህነት ማስፋፋቱ አልቀረም፣ በሰበቡም፣ በሕዝቡ ዘንድ አለመረጋጋት ከፍ እያለ ሄዷል። በመዲናይቱ ብራዛቪል ከሚኖሩት መካከል አንዳንዶቹ ከፕሬዚደንታዊው ምርጫ በኋላ ሁከት ሊፈጠር ይችል ይሆናል በሚል ስጋት ካሁኑ ከተማይቱን እየለቀቁ ወጥተዋል። አንድሪያስ ሜለር እንዳመለከቱት፣ ዓለም አቀፍ ቡድኖች ምርጫውን በታዛቢነት አይከታተሉም፣ ለምሳሌ፣ በዓመት ሶስት የታዛቢ ቡድኖችን ብቻ ማሰማራት የሚችለው የአውሮጳ ህብረት የኮንጎ ምርጫ ለውጥ ያመጣል ብሎ ስለማያሰብ ወደዚችው ሀገር የምርጫ ታዛቢዎቹን አይልክም።

ፊሊፕ ዛንድነር/ አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ