1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንጎ ምርጫ ሲገመገም

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 25 1998

ድምፅ ከተሰጠባቸው ጣቢያዎች አንዱ

https://p.dw.com/p/E0iJ
ምስል AP

በዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባለፈው ዕሁድ የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አድናቆት እየተቸረው ነው ። ዩናይትድስቴትስና የአውሮፓ ህብረት የምርጫው ሂደት ሰላማዊና የተሳካ ነበር ብለዋል ። በሀገሪቱ ታሪክ ከአርባ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የመድብለ ፓርቲ ምርጫ ነፃና ዲሞክራሲያዊ እንደነበር የኮንጎ ዜጎች እና ታዛቢዎችም መስክረዋል ። ይሁንና ከዕጩ ተወዳዳሪዎች ሁለቱ የምርጫው ሂደት ነፃ ካልመሰላቸው ውጤቱን እንደማይቀበሉ ከወዲሁ እያስታወቁ ነው ። ዓለም ዓቀፍ ታዛቢዎች በበኩላቸው ማንኛውም ቅሬታ በህጋዊ መንገድ መልስ ያገኛል ይላሉ ። “እኔ ደስተኛ ነኝ ። ትኩረት የተሰጠው እና ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደውን የዚህን ምርጫ ውጤት በናፍቆት እንጠብቃለን ። የምርጫውን አስተናባሪዎች እናመሰግናለን “
በኮንጎ ድምፅ ከሰጡት አንድዋ የተናገሩትን ነበር ። ብዙዎች ተመሳሳይ አስተያየት ነው የሚሰጡት ።ዕሁድ ዕለት በዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባተካሄደው ምርጫ የተሰጠው ድምፅ ቆጠራ ተጀምሮዋል ። የቆጠራው ውጤት ግን እንዲህ በአጭር ጊዜ ሊታወቅ አይችልም ።የትራንስፖርትና የመገናኛ አገልግሎት ሰፊ ግዛት ባላት ኮንጎ ደካማ በመሆኑ የመጀመሪያው ውጤት ይፋ እስኪሆን ድረስ ሶስት ሳምንት ይወስዳል ነው የተባለው ። በውጤቱ ከዕጩ ተወዳዳሪዎች አንዳቸውም ከሀምሳ በመቶ በላይ ድምፅ ካላገኙ ሌላ ምርጫ መካሄዱ አይቀርም ። ውጤቱ ይህ ከሆነ መምረጥ የሚችለው ሀያ አምስት ሚሊዮን የኮንጎ ዜጋ በሚቀጥለው ዓመት በጥቅምት ወር በአሁኑ ምርጫ ከፍተኛ ድምፅ ላገኙት ሁለት ተፎካካሪዎች እንደገና ድምፅ ለመስጠት ይወጣል ። የዚህ ውጤትም እስከ ህዳር ይቆያል ። ሰላሳ ሶስት ዕጩዎች ለፕሬዝዳንትነት እንዲሁም ከዘጠኝ ሺህ ሰባት መቶ የሚበልጡ ተፎካካሪዎች ለምክርቤት አባልነት በተወዳደሩበት ምርጫ ከተጠበቀው በላይ ህዝብ ነበር ድምፅ ሊሰጥ የወጣው ። የድምፅ አሰጣቱ ሂደትም እንደተፈራው አልነበረም ። የምርጫው ሂደት በመላው ሀገሪቱ በአጠቃላይ ሰላማዊ ሆኖ ነው የተገባደደው ። ምርጫውን ለመከታተል ከአውሮፓ ብቻ ሶስት መቶ ያህል ታዛቢዎች ነበሩ ። አንዳንዶቹ እንዳሉትም ምርጫው በቀና መንገድ ነው የተካሄደው ። የተሳካም ነበር ።ከታዛቢዎቹ አንዱ ጀርመናዊው ኡልሪሽ ሽቶክማን ናቸው ።
“እኔ የታዘብኩት የምርጫው ሂደት ነፃና ግልፅ በተጨማሪም ከተጨባጩ ሁኔታ አንፃር ሲታይ ስኬታማ መሆኑን ነው “
ከታዛቢዎች አንዳንዶቹ በዚህ መልኩ የምርጫውን ሂደት ሲያወድሱ ሌሎች ደግሞ ከምርጫው በህዋላ ለሚመጣው ስራ መዘጋጀት ዋነኛው ትኩረት ሊሆን ይገባል በማለት ያሳስባሉ ።
“ምርጫን ከከሰርግ ቀን ጋር ነው የማመሳስለው ። ትልቅ ድግስ ነው ። ትዳሩ የሚጀምረው በማግስቱ ነው ።ያኔ ነው ዕውነተኛው ዓለም የሚጀምረው ። ይህም ከምርጫ ጋር ይመሳሰላል ። ይህ ለሀገሪቱ አንድ ትልቅ ዕርምጃ ነው ። በጣም ጠቃሚ ምዕራፍ ነው ይሁንና በኮንጎ ሰላም ለማስፈን ከሚጥሩ ወገኖች በኩል ብዙ ስራና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል ።”
እዚህ ውጤት ላይ ለመድረስ የኮንጎ ዜጎች ብዙ አስተዋፅኦ አድርገዋል ። ያምሆኖ የኮንጎ ምርጫ ውጤት በርካታ ፈተናዎች እንደሚገጥሙት ማስጋቱ አልቀረም ። ምርጫውን ያሸንፋሉ ተብሎ በስፋት የሚነገርላቸው የጆሴፍ ካቢላ ተቀናቃኞች የቀድሞዎቹ ዓማፅያን የምርጫው ውጤት ፍትሀዊ ካልሆነ ላንቀበል እንችላለን ሲሉ ከአሁኑ ማስፈራራት ጀምረዋል ። ከዚህ በተጨማሪም በምስራቅ ኮንጎ የህግ የበላይነት አለመስፈኑ ሌላው አሳሳቢ ችግር ሆኖዋል ። በዚህ አካባቢ የሚንቀሳቀሱትና በጦር ወንጀለኝነት የተከሰሱት ዓማፂው ጀነራል ሎሮን ንኩንዳ አናሳ ቡድኖች በአዲሱ መንግስት ካልታቀፉ ዕርምጃ እንወስዳለን ማለታቸውም አስግቷል ። ከዚህ ሌላ አነስተኛ ደሞዝ የሚያገኙት የመንግስት ወታደሮችም ህዝባቸውን ይዘርፋሉ ። እነዚህ ሁሉ ችግሮች እያሉም ግን ህዝቡ ምርጫው በርስ በርስ ግጭት በደቀቀችው ኮንጎ ሰላም ያወርዳል የሚል ተስፋ አለው ።