1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንጎዉ ቪሩንጋ ፓርክ አደጋ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 7 2007

ቪሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ ወይም አልበርት ብሔራዊ ፓርክ በመባል የሚታወቀዉ በምሥራቃዊ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ በደቡብ ከቪሩንጋ ተራራዎች ተነስቶ እስከ ሰሜን የሪዋንዞሪ ተራራዎች ድረስ 3,000 ስኩየር ሜትር ስፋት ላይ ተዘርግቶ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/1FyXj
ምስል DW/S. Schlindwein

ይህ ስፍራ ከሩዋንዳዉ ቮልካኖስ ከሚባለዉ ብሔራዊ ፓርክ እና ከሩዋንዙሪ ተራራዎች ብሄራዊ ፓርክ እንዲሁም ከዩጋንዳዉ የንግሥት ኤልሳቤጥ ብሔራዊ ፓርክ ይዋሰናል። እድሜ ጠገቡ የኮንጎ ብሔራዊ ፓርክ አሁን ለአደጋ ተጋልጧል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ቪሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ ኮንጎ ዉስጥ ከተቋቋመ ወደ90 ዓመታት ያልፈዋል። ይህ ብሔራዊ ፓርክ በቅድሚያ በጎርጎሪዮሳዊዉ 1925ዓ,ም የተመሠረተዉ ሀገሪቱን በቅኝ ግዛትነት ይዘዉ በቆዩት የቤልጅግ ንጉሣዉያ ቤተሰቦች መሆኑም ይነገራል። በርካታ አስርት ዓመታትን ዘለቀናም በዚሁ የዘመን ቀመር በ1979 ላይ የተመ የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት UNESCO ጥብቅ አካባቢ ሆነ። በኮንጎ ብሔራዊ የፓርኮች ባለስልጣን እና የቪሩንጋ ጥብቅ ተቋም ሥር የሚተዳደረዉ ቪንሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሕገወጥ አደንና በኮንጎ የእርስበርስ ጦርነት በዉስጡ የያዛቸዉ አራዊት ለከፋ ጉዳት ተጋልጠዋል። በኮንጎዉ ጥብቅ አካባቢ የሚገኙት ወገኖች ቁጥራቸዉ እየበረከተ በመሄዱ በአንድ በኩል ለብሔራዊ ፓርኩ ስጋት ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ስፍራዉ የአማፅያን መመሸጊያ ሆኖ ለዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት አዉድማ ሆኖ መቆየቱም ሌላዉ ችግር ነዉ። አሁን እንኳ M23 የሚባለዉ የኮንጎ አማፂ ቡድን ከመንግሥት ጋ ተስማማ ተብሎም ሰላም የማስከበሩ እንቅስቃሴ አጥጋቢ አለመሆኑም ይነገራል።

Kongo Nyaragongo Vulkan im Nationalpark
ምስል DW/S. Schlindwein

በዚህ አካባቢ ይህና የመሰሳሉት ረዥም ዓመታት ላስቆጠረዉ ብሔራዊ ፓርክ አደጋነታቸዉ ተነግሮለት ሳያበቃ በቅርቡ ከደኑ ዉስጥ የተፈጥሮ ነዳጅን ቆፍሮ ለማዉጣት የተጀመረዉ እንቅስቃሴ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ዓይነት ሆኗል።

ቪሩንጋ ፓርክ አካባቢ የሚኖረዉ ሕዝብ ወደአራት ሚሊዮን ይጠጋል። ኗሪዎቹ አብዛኞቹ በእርሻ ላይ የተደገፈ ሕይወት ነዉ የሚመሩት። ከእሳተ ጎሞራ የተገኘዉ አፈር ለም ነዉ። የእርሻ ቦታዎቹ በባቄላና አደንንጓሬ ዘሮች በሽንኩርትና በአበባ ጎመን የተሞሉ ናቸዉ። ከእርሻዉ ሜዳ ባሻገር በሽቦ የታጠረ ሥፍራ ይታያል። በላዩም ላይ «ሰዎች በዚህ አካባቢ መኖር አይፈቀድላቸዉም» የሚል ምልክት ተሰቅሏል። ምን ማለት ይሆን? የስነሰብ ተመራማሪዉ ኤማኑዌልደሜሮድያስረዳሉ፤

Bildergalerie Virunga-Park Demokratische Republik Kongo
ምስል WWF/Brent Stirton

«የዚህ ብሔራዊ ፓርክ አመሠራረት ለሰዎች ፍላጎቶች ሲባል የተዘጋጀ የዓለም ቅርስ አካባቢ ነዉ።ከዚህም የዓለም ማኅበረሰብ ይጠቀማል። እዉነታዉ ግን ለዚህ ብሔራዊ ፓርክ ሕልዉና የአካባቢዉ ኗሪ ኅብረተሰብ ዋጋ ይከፍልበታል።ያንን ደግሞ በቁጥርና ዋጋ መተመን ይከብዳል። እጅግ ለም የሆነ ሚሊዮን ወይም ከዚያ በላይ ሄክታር የእርሻ መሬት አለ፤ የኮንጎ ገበሬ ቤተሰብ በወር በሄክታር 600 ዶላር ማግኘት ይችላል። እናም የምናወራዉ ቢያንስ 600 ሚሊዮን ዶላር ከዓለማችን እጅግ ድሀ የሆነ ኅብረተሰብ እንዳይጠቀምበት ተይዟል ማለት ነዉ። ይህም ኢፍትሀዊነት ነዉ።»

ሜሮድ በቅኝ ግዛት ዘመን ይህን ብሔራዊ ፓርክ ያቋቋመዉ የቤልጅግ ንጉሣዊ ቤተሰብ አካል ናቸዉ።የስነሰብ ተመራማሪዉ ተፈጥሮና ሰዎችን ከተፅዕኖ ለመከላከል እንዲቻል ሚዛናዊ ሕግ እንዲያረቅቁ በኮንጎ መንግሥት ተቀጣሪ ናቸዉ። በየዓመቱ ብሔራዊ ፓርኩን ለመጠበቅ አምስት ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል። ከመንግሥት ካዝና ከጠቅላላዉ ወጪ አምስት በመቶ ብቻ ነዉ የሚገኘዉ። ቀሪዉ ፓርኩን ለመጠበቅ ከሚሰበሰብ እርዳታ የሚገኝ ነዉ። ደ ሜሮደ አዲስ ሀሳብ አለኝ ይላሉ፤

Kongo Gorilla Junges
ምስል DW/S. Schlindwein

«የቱሪዝሙን ዘርፍ የመገንባቱ አዲስ ሀሳብ የመጣዉ የዛሬ ስድስት ዓመት ነዉ። ከምንም በላይ ደግሞ ለኅብረተሰቡ የሥራ እድል የሚከፍት አጋጣሚ ነዉ የሆነዉ። በአካባቢዉ ያለዉን ተሞክሮ አይተናል። ኬንያ ለምሳሌ ከቱሪዝሙ ዘርፍ 3,5 ቢሊዮን ዶላር ታገኛለች። ለብሄራዊዉ ኤኮኖሚም ከፍተኛ አስዋጽኦ ያደርጋል። ያ ማለት ከኮንጎ መንግሥት ዓመታዊ በጀት በመቶ ሚሊዮን ዶላር ይበልጣል። ኮንጎ ዉስጥ እንዲህ ያለዉን ጥቅም ማግኘት የቱሪዝሙ ዘርፍ በአግባቡ መልማት ይኖርበታል።»

የስነሰብ ተመራማሪዉ ምሥራቅ ኮንጎ ጎማ ዉስጥ በሚገኝ አንድ ምግብ ቤት ዉስጥ ተቀምጠዋል። እንደ500ዎቹ የደን ጠባቂ ባልደረቦቻቸዉ እሳቸዉም የለበሱት የደንብ ልብስ ነዉ። ደኑን እንደዐይናቸዉ ብሌን የሚንከባከቡትን ጠባቂዎች በበላይነት የሚመሩት እሳቸዉ ናቸዉ። አለባበሳቸዉ ወታደራዊ ይምሰል እንጂ ከጦር ሠራዊቱ ገለልተኛ ናቸዉ። ግን ደግሞ ተመሳሳይ ተግባር ያከናዉናሉ። ቪሩንጋ አካባቢ ጦርነት መነሳቱ የተለመደ ነዉ፤ የግጭቱ መንስኤ ደግሞ የተፈጥሮ ጥሬ ሀብት ነዉ። በአካባቢዉ በቅርቡ የብሪታንያዉ የነዳጅ ኩባንያ በምኅፃሩ SOCO የተባለዉ የነዳጅ ክምችት አግኝቷል። እናም የነዳጅ ማዉጣት ሙከራ ለማካሄድ ይሻል። የኮንጎ መንግሥት ለኩባንያዉ ፈቃድ ሰጥቷል። ሆኖም ግን የአካባቢዉን ተፈጥሮና የሕዝቡን ደህንነት የሚከላከለዉን ሕግ ይፃረራል። ይህን ለመከላከል የሞከሩት የሕጉ አርቃቂ የስነሰብተመራማሪዉ ለጥቂት ሕይወታቸዉን ሊያጡ ነበር። ከጎማ ወደፓርኩ በተሽከርካሪያቸዉ ሲጓዙ ከተተኮሰባቸዉ ጥይት ለጥቂት ተርፈዋል።

Kongo Goma Vulkan Nyiragongo
ምስል picture alliance/Mary Evans Picture Library/W. Warren

በዚህ ምክንያትም የፓርኩ ዳይሬክተር ከሆቴላቸዉ በአጀብ ነዉ የሚወጡት። ጠባቂዎቻቸዉ እጆቻቸዉን በመሣሪያቸዉ ላይ እንዳደረጉ በተጠንቀቅ በተሽከርካሪዉ የኋላ ክፍል ገቡ። የፓርኩ አስደዳደር ጽሕፈት ቤት የሚገኘዉ ወደሰሜን 30 ኪሎ ሜትር ገደማ ላይ ነዉ። የደ ሜሮደ ኑሮኛ ሥራ የተቆራኘበት ስፍራ። በአሁኑ ጊዜ ከቦታ ቦታ በጣም ይዘዋወራሉ። ከመላዉ ዓለም የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ጋር ያገኛሉ። ሰሞኑን አንድ የለንደን ኩባንያ ስለቪሩንጋ ፓርክ ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅቷል። ፊልሙ የሆሊዉድን የኦስካር ሽልማት ለጥቂት ነዉ ያጣዉ። ፊልሙ ዓለምን ያነጋግራል ነዉ የተባለለት።

በመንገዱ ላይ የተበላሹና የተቃጠሉ ታንኮች እዚህም እዚያም ተገትረዋል። ለአንድ ዓመት ተመንፈቅ ያህል አካባቢዉ የጦር አዉድማ ነበር። ከፓርኩ አስተዳደር ጣቢያ አቅራቢያ M23 የተሰኘዉ የቱትሲ አማፅያን ቡድን ዋና ጽሕፈት ቤት ይገኛል። ዊስኪ ለመጠጣት በአካባቢዉ ወደሚገኘዉ የእንግዶች መዝናኛ ስፍራ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ አማፅያኑ ገቡ። ደ ሜሮደ ከዚህ ቀደም እንደታሰበዉ የቱሪዝም እንቅስቃሴን ለመገንባት ከእነሱ ጋ ይደራደሩ ጀመር። ግን ደግሞ የብሪታንያዉ የነዳጅ ኩባንያ የሙከራ ቁፋሮዉን ለመጀመር ተዘጋጅቷል።

Kongo Bevölkerung Gebiet Rutshuru
ምስል DW/S. Schlindwein

በእሳተ ገሞራ በተዳፈነባቸዉ ተራሮች መካከል ሁለት ወንዞች ይፈሳሉ። ኤሌክትሪክ ለማመንጨት በቂ ኃይል አላቸዉ። በአካባቢዉ ኤሌክትሪክን ለቤት መጠቀም ያልተለመደ ነዉ። ሜሮደ አዲስ ሀሳብ ይዘዉ ብቅ አሉ፤ ከዉኃ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ግድብ መገንባት።

«ከዚህ የሚገኘዉ ገቢ ፓርኩን ለመደገፍ የሚዉል ይሆናል፤ ከዚህ ግማሹ ደግሞ ማለትም ሃምሳ በመቶዉ የፓርኩን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠበቅ፤ ቀሪዉ ሃምሳ በመቶ ደግሞ ለማኅበረሰቡ ልማት እንዲዉል ማለት ነዉ። እናም ከዚህ የኃይል ምንጭ ከእያንዳንዱ 50 ሜጋ ዋት በመቶና ሺህ የሚገመት የሥራ መደብ መፍጠር ይቻላል። እናም በያዝነዉ በዚህ ዓመት መጨረሻ ወይ ሥራዉን እናጠናቃለን ወይም 50 ሜጋ ዋት ማምረት እንችላለን። የዚህ ጠቀሜታም በእርሻ ኢንዱስትሪዉ ዘርፍ 50 ሺህ የሥራ እድሎችን መፍጠር ያስችላል።»

እሳቸዉ እንደሚሉት በታጣቂዎቹ ቡድን ዉስጥ በአምስትና ስምንት ሺህ መካከል የሚገመቱ አባላት ይንቀሳቀሳሉ።የሥራ እድልን ለብዙዎች እንዲፈጥር የሚሹት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ደግሞ እስከጎርጎሪዮሳዊዉ 2021 ድረስ 100 ሜጋ ዋት ማመንጨት ከቻለ ወደአንድ መቶ ሺህ የሥራ እድል መፍጠር ይቻላል ብለዉ ያምናሉ። ይህ እቅዳቸዉ ከዳር ከደረሰም ጠብመንጃ አንግቶ ወደጫካ የሚገባወጣት በአካባቢዉ አይኖርም ማለት ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ/ ዚሞነ ሽሊንድቫይን

አርያም ተክሌ