1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንሶዎች ጥያቄ፤ ግጭትና ጥፋት

ሐሙስ፣ መስከረም 5 2009

ሰሞኑን ደግሞ ፀጥታ አስከባሪዎች ጥያቄ ያቀረበዉን ሕዝብ አስተባብረዋል ባሏቸዉ ሰዎች ላይ እርምጃ በመዉሰዳቸዉ ግጭት ተከስቷል።በግጭቱ በርካታ ሰዎች መገደላቸዉን፤ ቤትና ንብረት መጥፋቱን የአይን ምስክሮችና ፖለቲከኞች አስታዉቀዋል

https://p.dw.com/p/1K390
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Deutsch

[No title]


ደቡብ ኢትዮጵያ የኮንሶ ወረዳ ነዋሪዎች ያነሱት የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄ ሰሞኑን ደም አፋሳሽ ዉዝግብና ግጭት አስከትሏል።የአካባቢዉ ነዋሪዎች እንደሚሉት የኮንሶ ሕዝብ ከዚሕ ቀደም አካባቢዉ የነበረዉ የልዩ ወረዳ የአስተዳደር ሥልጣን እንዲመለስለት በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ የክልልንና የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች አቤቱታ አቅርቦ ነበር።አቤቱታዉ ግን ሰሚ አላገኘም።ሰሞኑን ደግሞ ፀጥታ አስከባሪዎች ጥያቄ ያቀረበዉን ሕዝብ አስተባብረዋል ባሏቸዉ ሰዎች ላይ እርምጃ በመዉሰዳቸዉ ግጭት ተከስቷል።በግጭቱ በርካታ ሰዎች መገደላቸዉን፤ ቤትና ንብረት መጥፋቱን የአይን ምስክሮችና ፖለቲከኞች አስታዉቀዋል።የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንርን አነጋግሮ ተከታዩን ዘገባ ልኮልናል።


--------------------------------------------
እዚያዉ ኮንሶ የሚገኙ ነዋሪዎችም ሰሞኑን የተነሳዉ ግጭት ከባድ ጉዳት መድረሱን ይናገራሉ።ለአጭር ጊዜ ልምምድ አብሮን የሚገኘዉ ተስፋአለም ወልደየስ ያነጋገራቸዉ የአይን ምስክሮች እንደሚሉት የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች በርካታ ሰዎችን ገድለዋል።ቤትና ንብረት አቃጥለዋልም።የኮንሶ ሕዝብ ጥያቄ ለመንግሥት አካል እንዲያቀርብ የተሰየመዉ ኮሚቴ አባልንም አነጋረናል። የደቡብ መስተዳድር ባለሥልጣናትም ግጭትና ጥፋት መድረሱን አምነዋል።

በኮንሶ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት እና በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት የተመለከቱት አቶ ዕድሉ አይለቴ ጳጉሜ 5 የተቀሰቀሰው ግጭት እስካሁንም ቀጥሏል ይላሉ፡፡ በግጭቱ ምክንያት የጠፋውን ህይወት እና ሁኔታውን በዝርዝር ያስረዳሉ፡፡

የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሒክማ ከይረዲን ግጭቱ እንደነበር ቢያምኑም የጉዳቱ መጠን በዓይን እማኞች ከተገለጸው ያነሰ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

በኮንሶ ከዞን ይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመትም ተመሳሳይ ደም አፋሳሽ ግጭት ተከስቶ ነበር፡፡ የሰሞኑ ግጭት መንስኤ ግን በአካባቢው ባለስልጣናት ለረጅም ጊዜ ሲቀናበር የቆየ እና በአጎራባች ወረዳዎች ተሳትፎ የታገዘ እንደነበር የዞን ጥያቄው አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ገመቹ ገንፌ ይናገራሉ፡፡

አቶ ገመቹ በኮንሶዎች ላይ ያነጣጠረ ነው ባሉት ጥቃት "የመከላከያ ሰራዊት እና የጸጥታ ኃይሎች ተሳትፈዋል" ይላሉ። የክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ግን ክሱን ያጣጥሉታል፡፡ እንደውም ለግጭቱ መነሻነት ኮሚቴውን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

ኮንሶ አሁንም በውጥረት ላይ ትገኛለች፡፡ ነዋሪዋቿ 23 አባላት ባሉት ኮሚቴ አማካኝነት ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡት ጥያቄም በእንጥልጥል ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ስብሰባውን ያካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የፌደሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን ተመልክቶ መፍትሄ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ተስፋዓለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ