1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬክሮስ የሳይንስ ሽልማት

ረቡዕ፣ ግንቦት 13 2006

በአሁኑ ዘመን ፤ በኢንዱስትሪ እጅግ ደርጅተው የሚገኙ ሃገራት እዚህ ደረጃ ለመድረስ የበቁት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምርምር አማካኝነት ሳይንስንና ቴክኖሎጂን የሙጥኝ በማለት እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም። ከምዕራባውያኑ ሃገራት መካከል የኢንዱስትሪው

https://p.dw.com/p/1C3o0
ምስል Fotolia/Abdone

አብዮት ጀማሪ ብሪታንያ ፣ ከዚያም ቀደም ብላ በተለያዩ ዘርፎች ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ለሕብረተሰብ ጠቃሚ አገልግሎት በሚሰጡ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ እንደነበሩ መለስ ብሎ ታሪኩን መመልከት አያዳግትም። በዓለም ዙሪያ ቅኝ ግዛት ለማስፋፋትም በስነ ቴክኒኩ ምጥቀት መጠቀሟ ሳይረሳ ማለት ነው!

የሳይንስ ጠበብት ለህዝብ አገልግሎት ፤ ለሀገርም ጥቅም ይሰጣል በማለት ነው አብዛኛውን ጊዜ በረዥሙ ፣ መጪውን ዘመንና ተግዳሮቱን በማሰብ ነው ምርምር የሚያካሂዱት።

በመጪው ሐምሌ ወር በብሪታንያ ፣ ፓርላማው የ«ሎንግትውድ ደንብ» (Longitude Act ) የተሰኘውን ለሕብረተሰብ የሚበጅ የምርምር ውጤት ለሚያቀርቡ ሰዎች ሽልማት የሚሰጠበትን ድርጊት ያጸደቀበት 300ኛ ዓመት ይታሰባል። ይህን መንስዔ በማድረግ የብሪታንያው የቴሌቭዥንና ራዲዮ ድርጅት (BBC) Horizon የተሰኘውን የሳይንስ ዝግጅቱን የጀመረበትን 50ኛ ዓመት በልዩ ፕሮግራም ግንቦት 14 ቀን 2006 ዓ ም እንደሚያስብ ሲያስታውቅ፤ ከ 300 ዓመታት ወዲህ ለዛሬው ዘመን ሰውና ለመጪው ትውልድ ተግዳሮቶች መላ ለመሻት በዐበይት ጉዳዮች ምርምር እንዲደረግ ተመራማሪዎችን በመጋበዝ ነው። አርእስቱ የትኞቹ እንደሆኑ ከመጠቃቀሳችን በፊት፤ ከ 300 ዓመት በፊት ለምን ጉዳይ ዐቢይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደነበረ ሳይንስ ቢሆንም ዝግጅታችን ወደ ታሪኩ ላፍታ እንመለስ።

Schiff Navigation Kompass
ምስል FikMik/Fotolia

እ ጎ አ በ 1714 ዓ ም፤ በንግሥት Anne ዘመነ መንግሥት መሆኑ ነው፣ የባህር ላይ ጉዞ፤ የተለመደ እንቅሥቃሤ ሆኖ ፣ መርከቦች አትላንቲክ ውቅያኖስን ሰንጥቀው ራቅ ወደአሉ የዓለም ክፍሎች ፣ ይቀዝፉ የነበረበት ጊዜ ነው። እናም ጠቃሚ የምርምር ውጤት ለሚያቀርብ ሰው ሽልማት የሚሰጥ የሎንግትውድ ቦርድ የሚባል ያኔ ተቋቁሞ፣ በቀላል ዘዴ አንድ መርከብ በጉዞ ላይ የት እንደሚገኝ ፣ ከመነሻውም ሆn ከመድረሻው ርቀቱ ምን ያህል እንደሆነ ማመላከት ለሚችል የገንዘብ ሽልማት ለመስጠት ዝግጁ ነበረ።

፣ ከኮርን ዎል ዌልስ ጠረፍ በስተደቡብ ምዕራብ አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ 45 ኪሎሜትር ያህል ራቅ ብለው በሚገኙት «ሲሊ» የተጫፈሩ ደሴቶች፣ እ ጎ አ ጥቅምት 22 ቀን 1707 ዓ ም ፤ የብሪታንያ ባህር ኃይል 4 ትልልቅ መርከቦች፣ በኃይለኛ ማዕበል ሳቢያ ሰጥመው ከ 1400 በላይ መርከበኞች ከሞቱ በኋላ ነበረ፣ ነጋዴዎች እንዲሁም የመርከብ ቀዛፊዎችና ሠራተኞች፤ የብስ ሳያዩ አያሌ ሳምንታት በውቅያኖስ ላይ የሚቀዝፉ መርከቦች፤ የት እንደሚገኙ፤ ከሞላ ጎደል በትክክል የሚጠቁም ዘዴም ሆነ መሣሪያ ያስፈልጋል በማለት ፣ ባመለከቱት መሠረት ሐሳቡ በግንቦት ወር ለፓርላማ ቀርቦ፤ በሐምሌ ለመጽደቅ የቻለው።

Weltall Erdumlaufbahn
ምስል REUTERS

እ ጎ አ ከ 1737-1764 ፣ በዘመኑ አስደናቂ የተሰኘውን «ክሮኖሜትር» የተሰኘውን መለኪያ መሣሪያ በመሥራት ላይ የነበረው፣ ራሱን ያስተማረ ታዋቂ የሰዓት ሠሪ እንደነበረ የሚነገርለት ጆን ሐሪሰን የተባለው እንግሊዛዊ ፤ የመጀመሪያውን የቦርዱን 3,515 ፓውንድ ሽልማት፣ በ 1765 ደግሞ አጠቃላዩን ሽልማት ፤ 10 ሺ ፓውንድ ለማግኘት በቅቷል። ጆን ሃሪሰን፣ በቀጥታ ከፓርላማውም ከምሥጋና ጋር 8,750 ፓውንድ በማግኘቱ ፤ በአጠቃላይ በሕይወት ዘመኑ ለሠራው ሥራ ያገኘው ሽልማት 23,065 እንደነበረ ተመዝግቧል።

ሌሎች ተመራማሪዎችም፤ በየጊዜው ክሮኖሜትርን ለማሻሻል ባደረጉት ጥረት ፣ የጆን ሃሪሰንን ያክል ጠቀም ያለም ባይሆን ሽልማት አግኝተዋል።

የክሮኖሜትር ዋጋ ውድ ስለነበረ፤ መርከበኞች፤ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በጨረቃም ይጠቀሙ ነበር። የቀረው፤ ሽቦ አልባው የጽሑፍ መልእክት( ቴሌግራፍ) ቀርቦ ከክሮኖሜትሩ ጋር በመጣመር ፣ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ነበር።

በባህር ረዥም ጉዞ በማድረግ ፣ ኬክሎስን (ኬክሮስ) (Longitude) በትክክል ለማመላከት አስቸጋሪ ነበር። አንድ መርከብ ከምድር ሰቅ ወደ ሰሜን ወይም ደቡብ የቱን ያህል ይርቃል ? ለሚለው ጥያቄ መልሱን ለማቀረብ ፣ ፣ እንደሚባለው መለኪያው የሚያስቸግር አይደለም፤ ቀትር ላይ ፣ ፀሐይ፣ አናት አቅጣጫ ላይ ከደረሰች በኋላ ፣ ወደ አድማስ የምታሽቆለቁልበትን አካሄድ በመለኪያ ምልክት በማድረግ ለማወቅ የሚያዳግት አይደለም። ኬክሎስ ግን አስቸጋሪ ነው ።ቀደም ባለው ዘመን ለረጅም ጉዞ መርከበኞች የሚመኩት በጭፍን ምልክት ወይም በአቅጣጫ ግምት (Dead Reckoning) ነበር።

)
ምስል Reuters

ይህም በቀዘፋ ላይ ቅጽበታዊ ይዞታን ፤ ፣ ከዚያ በፊት በተለካ መነሻና መድረሻ መሠረት የጉዞውን ሂደት በግምትም ሆነ በተሰላ ፍጥነት የሚወስደውን ጊዜና አቅጣጫ ማመላከት የሚቻልበት ብልሃት ነው። ይህ በእርግጥ እንደ ዘመናዊው ሳቴላይት አቅጣጫ መምሪያ ወይም የሳቴላይት ቁጥጥር ፍጹም አስተማማኝ አይደለም።

የ«ሎንግትውድ ደንብ » በብሪታንያ ፓርላማ ከጸደቀና ሽልማትም መስጠት የተጀመረበትን 300 ኛ ዓመት መንስዔ በማድረግ ፤ ብሪታንያ ሌላ የዘመኑ «ጆን ሃሪሰን »ያስፈልግናል በማለት ፤ ለአሁኑና ለመጪው ዘመን ዐበይት ተግዳሮቶች መፍትኄ ለሚያስገኙ ተመራማሪዎች ሽልማት ለመስጠት፣ Nesta የተባለው የብሪታንያ ለትርፍ የማይሠራ ፣የአዳዲስ ግኝት አበረታች ድርጅትና የመንግሥት የሆነው የቴክኖሎጂ ስልት ቦርድ (The Technology Strategy Board) የተሰኘው ተዘጋጅተዋል።

የተመደበው ሽልማት 10 ሚሊዮን ፓውንድ ነው። ሽልማቱ የሚሰጠው ከ 6 ዐበይት አርእስት መካከል በሚመረጠው በአንደኛው ርእስ፣ ተፈላጊውን የምርምር ውጤት ያሳካ ይሆናል። በነገው የBBC ቴሌቭዥን የሳይንስ ተከታታይ ዝግጅት «ሆራይዘን» ፣ አርእስት መራጭ ፣ ህዝቡ ፣ ተመልካቹ ይሆናል። ከትናንት በስቲያ የመጪው ዘመን ተግዳሮቶች የተዘረዘሩት «አስትሮኖመር ሮያል» በሚል ማዕረግ የሚጠሩት አንግሊዛዊው የሥነ ፈለክ ሊቅ ፕሮፌሰር ሰር ማርቲን ሪስ በሊቀመንበርነት በመሩት የሎንግትውድ ኮሚቴ ነው። ከዚያ በፊት ግን በተለያዩ መስኮች ከሚመራመሩ ጠብበት ጋር ሰፊ ውይይትና ምክክር ሲደረግ መቆየቱ ነው የተነገረው። የነገውን ዕጣ ፈንታ ከወዲሁ ዛሬ ለመወሰን ፤ የተመረጡት አርእስት፤

Litauen Schiff mit Flüssiggas nach Klaipeda
ምስል picture-alliance/AP

1, ለእያንዳንዱ ሰው ያልተቋረጠ አልሚ ምግብ የማግኘቱን ዋስትና እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል--

2, ባክቴሪያ የሚያስከትላቸውን በሽታዎች መከለከያ ፣ ፔንስሊን መሰል መድኃኒቶችን ፍቱንነት የሚፈታተኑ ሁኔታዎችን መቋቋሚያ ብልሃት

3, በሚመጡት 50 ዓመታት የተፈጥሮ አካባቢን በመበከል ረገድ 15 ከመቶ አስተዋጽዖ የሚኖረውን ከኣኤሮፕላኖች የሚትጎለጎል ጢስ መግቻው ዘዴ---

4, እ ጎ አ በ 2050 በዓለም ዙሪያ 135 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በእርጅናና በጎልማሳነት ዕድሜም ሊያጋጥም የሚችል የማስታወስ ማቃትን ወይም የመዘንጋትን ሳንክ ተቋቁመው ራሳቸውን ችለው እንዲኖሩ መላው ምን ይሆን?

5,የአካልን ስንኩልነትን (መሽመድመድን) መከላከያው ብልሃት

6,እያንዳንዱ ሰው አስተማማኝና ንጹህ ውሃ የሚያገኝበት ዘዴ፣ ረከስ ባለ ዋጋ ለተፈጥሮ አካባቢም የሚበጅ ቀጣይነት ያለው ከጨውማ ውሃ ንፁህ ውሃ ማግኛው መፍትኄ፣

የተሰኙት ናቸው።

Feierlichkeiten zu 100 Jahre Titanic, in Belfast FLASH-GALERIE
ምስል picture alliance/empics

በ 18ኛው ክፍለ ዘመ በተንጣለለው ውቅያኖስ ፣ የሆነ መርከብ ከመነሻውም ሆነ ከመድረሻው ወደብ ምን ያህል ርቆ የት እንደሚገኝ የማመላከቱ ተግዳሮት ነበረ ያኔ አስጨናቂ ሆኖ ፤ በአንድ ታታሪ ተመራማሪ መላ የተገኘለት።

ባልንበት ዘመን ግን ፤ ከተዘረዘሩት 6 ዐበይት ችግሮች በተጨማሪ የተደረደሩ አያሌ ሳንኮችም በቀላሉ የሚታለፉ አይደሉም። ስለሆነም፤ ብዙ ወጣቶች፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ላይ በትጋት እንዲያተኩሩ ሁኔታዎች ይጋብዛሉ።

በአጠቃላይ ስለእኛይቱ ፕላኔት፤ ስለ ሥነ ፍጥረት ፤ ስለሕዋ የምናውቀውም ውሱን ነው። ኮስሞስ ወደ ቀውስ ወይስ ወደ ፈውስ ነው የሚያመራው? ስለሕዋ ብዙ ጊዜ ይነገር እንጂ ፣ 0,4 ከመቶ በከፊል ስለከዋክብትና ስለመሳሰሉት እናውቅ ይሆናል። 74 ከመቶው ሕዋ ጽልመታዊ ኃይል፤ 22 ከመቶው ጽልመታዊ ቁስ አካል፤ 3,6 ከመቶው ደግሞ

በከዋክብትና ፕላኔቶችና በመሳሰሉት መካከል በሚገኝ ጋዝ የተሞላ ነው --ጥናቱ-- ማለት ይከብዳል ፤ ግምቱ እንደሚለው ማለት ነው። ስለሆነም የሰው የመመራመር ትጋት በእጅጉ ተፈላጊ ይሆናል። በዋናነት የሚፈለግው ግን ፣ በምድራችን የተደቀኑትን ችግሮች ፤ ተግዳሮቶች ፣ በመቋቋም መፍትኄውን አግኝቶ የፕላኔታችንን ሕይወት ደጋፊነት፣ የሰውንም ህልውና ቀጣይነት ለማረጋገጥ መሆን ይኖርበታል።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ