1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያታ ድልና ፖለቲካዊ ሥብዕና

ሰኞ፣ መጋቢት 2 2005

ከኬንያዎች መማር የሚገባቸዉ፥ ከአዲስ አበባ እስከ ጀቡቲ፥ ከካርቱም እስከ ካምፓላ፥ ከዳሬኤሰላም እስከ ማፑቶ የሚገኙ የአካባቢዉ ሐገራት ባለሥልጣናት ወይም የድርጅት ተጠሪዎች እዚያዉ ኬንያ ድረስ ሔደዉ የአስተማሪዉን የምርጫ ሒደት ተመልክተዉታል።አበል ከመቁጠር ባለፍ ለመማር ይሻሉ ወይ ነዉ ጥያቄዉ።

https://p.dw.com/p/17v9q
Kenya's presidential candidate Uhuru Kenyatta (C) greets supporters beside his running mate William Ruto (2nd L) as they celebrate winning the presidential election after the official result was released in Nairobi March 9, 2013. Kenyatta, indicted for crimes against humanity, was declared winner of Kenya's presidential election on Saturday with a tiny margin, just enough to avoid a run-off after a race that has divided the nation along tribal lines. REUTERS/Siegfried Modola (KENYA - Tags: POLITICS ELECTIONS)
ኬንያታ-የድል ፌስታምስል Reuters


ዩጋንዶች ይሞክሩታል።ኢትዮጵያዉያን ይናፍቁታል።ኤርትራዉያን ያልሙታል።ሱዳኖች ይመኙታል። ጀቡቲዎች ይከጅሉታል።ሶማሌዎች ያስቡታል።ምርጫን።ነፃ ፍትሐዊ ምርጫን።እርግጥ ነዉ፥ታንዛኒዎች አድርገዉታል።ኬንያዎች ደግሞ ደገሙት።መረጡ።የገለልተኛዉ የምርጫና የድንበር ኮሚሽን ሊቀመንበር ኢሳቅ ሐሰን አረጋገጡት።ቅዳሜ።

«ሥለዚሕ ኡሑሩ ኬንያታ የኬንያ ሪፐብሊክ ተመራጭ ፕሬዝዳት መሆናቸዉን አስታዉቃለሁ።»በነፃነት ሥም የተሰየሙት-በነፃዉ ምርጫ አሸነፉ።ኡሁሩ ሙይጋይ ኬንያታ።የኬንያታ ማንነት፥ የድላቸዉ መሠረት፥ የአስተምሕሮቱ እንዴትነት ያፍታ ዝግታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።

መጀመሪያ ምርጫ ነበር።2007 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።የምርጫ ዉጤት፥ የሒደቱን ነፃ፥ ትክክለኛና ፍትሐዊነቱን አጠራጠረ።ጥርጣሬዉ ዉዝግብ፥ ዉዝግቡ ግጭት፥ ግጭቱ ሞት፥ ቁስለት፥ ስደት፥ መፈናቀል፥ ቂምንም አስከተለ።

ያሁኑ ምርጫ ዉጤትም ከቅሬታ፥ ጥርጥሬ፥ የፀዳ አይደለም።እንዲያዉም የኡሑሩ ኬንያታ ዋነኛ ተፎካካሪ ራይላ ኦዲንጋ እንደሚሉት የፍርድ ቤት እሰጥ አገባ ያስከትልም ይሆናል።እስከዚያዉ ግን ኬንያዎች ከሁለቱ ሺ ሰባቱ ምርጫ ዉጤት ደም አፋሳሽ ዉዝግብ እንማር አሉ።ወይም ያሉ መለሰሉ።

መጀመሪያ ምርጫ ሳይሆን የመጀመሪያዉ ምርጫ ሥሕተት እንዳይደገም-ሁሉንም የሚያስር የሚያግባባ፥ ሕግ በማፅደቁ ተስማማሙ።ኦዲንጋ እንደ ጠቅላይ ሚንስትር ከፕሬዝዳት ምዋዪ ኪቢካ አነስ፥ ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ኡሑሩ ኬንያታ በለጥ ባለ ሥልጣናቸዉ የተሳተፉ፥የተስማሙበት ሕግ ፀደቀ።እና መጀመሪያ ሕግ ነበረ።

«ኮሚሽኑ፥ የማጠሪያና የማረጋገጪያ ሥልቶችን ገቢር ማድረጉን ለኬንያዉያን ለማረጋገጥ እወዳለሁ። ማንኛዉም አስመራጭ ባለሥልጣን (የምርጫዉን) ዉጤት ማዛባት አይችልም።ድምፅ መሥረቅን ጨምሮ ዉጤቱን ለማዛባት የሚሞክር ባለሥልጣን ካለ፥ እሱ በሕጉ መሠረት በወንጀለኝነት የመጠይቅ ሐላፊነት አለበት።»

የአስመራጭ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ኢሳቅ ሐሰን።ሕጉ እንዲሕ ገቢር ሆነ።ኬንያም መረጠ።የምርጫዉ ሒደት ትክክለኛነት፥ የኬንያዎች ትዕግስት ተደነቀ።የአዉሮጳ ሕብረት የታዛቢዎች ቡድን መሪ አሊዮስ ፔተርለ እንዳሉት ደግሞ ኬንያዎች መብት ነፃነታቸዉን ለማስከበር ያሳዩት ትዕግሥት ለአካባቢዉ ሐገራት ብቻ ሳይሆን ለሌላዉም ዓለም አስተማሪ ነዉ።


የኬንያዎች አይነቱን ምርጫ ሞክሮ የከሸፈ፥ የተቀለበሰበት፥ ተመኝቶ ያልሆነለት፥ ያን አይነቱን ነፃነት እደናፈቀ፥ እንዳለመዉ ዓመት የሚያሰላዉ የአካባቢዉ ሐገራት ሕዝብ ሙከራ፥ ምኞት፥ናፍቆቱ በጠመንጃ እየተደፈለቀ መከነበት እንጂ ከኬንያዎች ለመማር እስከ በርግጥ ዘንድሮ አልጠበቀም ነበር።

ዘንድሮ የአዉሮጳ ሕብረቱ የታዛቢዎች ቡድን መሪ እንዳሉት ከኬንያዎች መማር የሚገባቸዉ፥ ከአዲስ አበባ እስከ ጀቡቲ፥ ከካርቱም እስከ ካምፓላ፥ ከዳሬኤሰላም እስከ ማፑቶ የሚገኙ የአካባቢዉ ሐገራት ባለሥልጣናት ወይም የድርጅት ተጠሪዎች እዚያዉ ኬንያ ድረስ ሔደዉ የአስተማሪዉን የምርጫ ሒደት ተመልክተዉታል።አበል ከመቁጠር ባለፍ ለመማር ይሻሉ ወይ ነዉ ጥያቄዉ።

መልሱ-አይም ሆነ አዎ ምግባር ነዉ-በያኙ።ኡሑሩ ኬንያታ ግን ገለልተኛዉ አስመራጭ ኮሚሽን እንዳስታወቀዉ በጠመንጃ፥ በጉልበት፥ በማጭበርበር ሳይሆን በአዉሮጳ የታዛቢዎች ቡድን መሪ ታላቁን የሠላም ሽልማት ኖቤልን በተመኙለት በኬንያዎች ትዕግሥት፥ ብስለት፥ በድምፅ ብዛት አሸነፉ። ሰዉዬዉም ፖለቲካዊ ብልጣብልጥነቱን አላጡበትም።«ዲሞክራሲ እና ሠላም አሸነፉ» እንጂ ቢያንስ ላደባባዩ ቃል «አሸነፍኩ» አልወጣታቸዉም።

«ኬንያዉን ወገኖቼ ሆይ! ዛሬ የምናከብረዉ የዲሞክራሲን ድል ነዉ።የሠላም፥ የብሔራዊ አንድነትን ድል ነዉ።ብዙዉ ዓለም ቢጠራጠርም፥ የደረስንበት ፖለቲካዊ ብስለት የነበረዉን ጥርጣሬ እና ግምት ሁሉ መና አስቀርቶታል።»

የአባታቸዉ የጆሞ ኬንያታ የነፃነት አርበኝነት፥ ጀግና ተዋጊ፥ በሳል መሪነት የእድገት፥ የትምሕርት፥ የእዉቀት፥ ሐብታቸዉ ምንጭ መሆኑ አላከራከረም።የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎችን የተፋለሙ አርበኞች ጀግና መሪ፥ የኬንያዎች የነፃነት ተምሳሌት፥ የመጀመሪያዉ ፕሬዝዳት ነበሩ-ጆሞ ኬንያታ።

ከአባታቸዉ በገቢር ያዩትን የአመራር፥ የፖለቲካ ብልጣብልጥነት ዩናይትድ ስቴትስ ድረስ ተሻግረዉ ተምረዉታል።የፖለቲካ ሳይንስን።ከትልቁ ሰዉ የመወለዳቸዉን ያክል የትልቁ ጎሳ የኩኩዩ አባል ናቸዉ። የናጠጡ ሐብታምም።በ1978 የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን ከጆሞ ኬንያታ ለወረሱት ለዳንኤል ቶሮኢቲቺ አራፕሞይ ኬንያዎች ጥሩ ቅፅል አላቸዉ።«ንያዮ» የሚል።ፈለግ ተከታይ፥እንደማለት ነዉ የስዋሒሊኛ ፊቺዉ።

ሞይ ሃያ አራት ዘመን ከኖሩበት ሥልጣን በጡረታ ለመሰናበት ሲያስቡ ኡሑሩ ኬንያታን ለወረሽነት ያጩት የጆሞ ኬንያታን ፈለግ መከተላቸዉን ለማረጋገጥ እንጂ የኡሑሩን ፖለቲካዊ እዉቀት፥ ሐብት፥ ጎሳቸዉን አስበዉ አልነበረም።

ከካሌንጂን ጎሳ የሚወለዱት ሞይ ጎሳን አስበዉ፥ ቢሆን ኖሮ ሥልጣናቸዉን ከኩኩዩዉ ኡሁሩ ይልቅ ለካሌንጂ ፖለቲከኞች፥ ልምድ እዉቀትን ምክንያት አድርገዉ ቢሆን ኖሩ ምክትላቸዉ ለነበሩት ለምዋዪ ኪባኪ ለማዉረስ በወሰኑ ነበር።አላደረጉትም።

ሞይ የገዢዉን የኬንያ አፍሪቃዉያን ብሔራዊ ሕብረት (KANU) ፓርቲን የመሪነት ሥልጣን ያወረሷቸዉ ለፕሬዝዳትነት ያጩዋቸዉ ኡሁሩ ኬንያታ የአባታቸዉ ሥም፥ ዝና፥ የሞይ ፍቃድ ፍላጎት፥ ሐብታቸዉም የድላቸዉ መሠረት ቢሆን ኖሮ በሁለት ሺሕ ሁለቱ ምርጫ ባሸነፉ ነበር።

ሞይ፥ ኡሑሩ ኬንያታን «ለአልጋ» ወራሽነት ማጨታቸዉ፥ የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን ከእጃቸዉ እንደቀሟቸዉ ለቆጠሩት ለምክትል ፕሬትዳት ለምዋዪ ኪባኪ «ሳይደግስ አይጣላም» አይነት ነበር።ኪባኪ ዴሞክራቲክ የተሰኘዉን ፓርቲያቸዉን፥ በሞይ ዉሳኔ ተበሳጭተዉ ገዢዉን ፓርቲ የለቀቁ ፖለቲከኞች ከመሠረት የፖለቲካ ፓርቲ ጋር አጣምረዉ «የኬንያ ብሔራዊ ሕብረት (NKA)ን መሥርተዉ ኡሑሩ ኬንያታን ተጋፈጡ።እና ኪባኪ በሰፊ ልዩነት አሸነፉ።

ወጣቱ ፖለቲከኛ ኡሑሩ ኬንያታ ሽንፈታቸዉን በፀጋ ተቀበሉት።ዘንድሮ እርግጥ ሐምሳ-አንድ ዓመታቸዉ ነዉ።ግን አሁንም ልክ እንደ ዛሬ አስራ-አንድ ዓመቱ ሁሉ ተሸንፌ ቢሆን ኖሮ አሉ ባለፈዉ ቅዳሜ፥ ሽንፈቴን በፀጋ እቀበል ነበር።

«የኬንያ ሪፐብሊክ መሪ እንዲሆን የተመረጠዉ ሰዉ፥ ሌላ ቢሆን ኖሮ፥ ያን ሰዉ እንኳን ደስ አለሕ ለማለት እና አብሬ ለመስራት ፍቃደኝነቴን ለመግለፅ የመጀመሪያዉ እሆን ነበር።»

ቅዳሜ ያሉትን ያድርጉት አያደርጉት አይታወቅም።በሁለት ሺሕ ሁለቱ ምርጫ ግን አድርገዉታል። በኬንያ የነፃነት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የመሪነት ሥልጣን ያጣዉን ፓርቲ በተቃዋሚነት ከመምራት አልፈዉ የአባታቸዉን ሥም፥ ዝና፥ሐብት፥ የአዉራሻቸዉን ምኞት፥ ጉልበት አድርገዉ ቢነሱ ኖሩ የኬንያ ፖለቲካዊ ሒደት ሌላ መልክና ባሕሪ በያዘ ነበር።

በሁለት ሺሕ ሰባት ማብቂያ በተደረገዉ ምርጫ ደግሞ በሁለት ሺሕ ሁለቱ ምርጫ ያሸነፏቸዉን ምዋዪ ኪባኪን ከመቃወም ይልቅ ደግፈዉ ከጎናቸዉ ቆሙ።ምዋዪ ኪባኪና ራይላ ኦዲንጋ የተፎካከሩ፥ የተወዛገቡበት የምርጫ ዉጤት ሕይወት፥ አካል ሐብት ንብረት አጥፍቷል።ዋንኞቹ ተፎካካሪ፥ ተወዛጋቢዎች ኪባኪና ኦዲንጋ ተጣማሪ መንግሥት ሲመሰርቱ ኡሑሩ ኬንያታና ብጤዎቻቸዉ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ICC በዘር ማጥፋት ወንጀል መከሰሳቸዉ ነዉ-እንቆቅልሹ።

ፍርድ ቤቱ የኡሑሩ ኬንያታ፥የምክትልቻዉን የዊልያም ሩቶ እና የሌሎች ተከሳሾችን ጉዳይ ለመመልከት ለመጪዉ ሐምሌ ቀጠሮ አለዉ።በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶበት ለፕሬዝዳትነት በመመረጥ ኬንያታ የመጀመሪያዉ ፖለቲከኛ ናቸዉ።

ክሱ እና የሐያሉ ዓለም ዲፕሎማቶችና መገናኛ ዘዴዎች ሥለ ክሱ የሚያራግቡት ዜና ግን፥ ብሪታንያዊዉ ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ ዳንኤል ብራንች እንደሚሉት፥ ኡሑሩ ኬንያታና ዊሊያም ሩቶን ከመጉዳት ይልቅ «ለድላቸዉ ትልቅ መሳሪያ» ሆኗል።በተለይ ምዕራባዉያን ሐገራት ክሱን አስታከዉ በኬንያ ላይ ሊያሳርፉት የሞከሩት ተፅዕኖ ብራንች እንደሚሉት ኬንያዎች ከዕልሕ ዶሎ የኬንያታ ደጋፊዎችን ቁጥር አበራክቷል።

የናይሮቢ ዩኒቨርስቲዉ የፖለቲካ ሳይቲስት ሙሳምባዬ ካቱማንጋ በበኩላቸዉ እንዳሉት የICCክስ ኬንያዉያንን «ልጆቻችንን ለመዉሰድ የሚያሰሩ ጠላቶቻችን» በሚል እልሕ ለኬንያታ ድምፅ እንዲሰጡ ነዉ ያደረጋቸዉ።ሌላዉ ኬንያዊ የፖለቲካ አዋቂና የሕግ ባለሙያ ዩሱፍ አቡበከር እንደሚሉት ደግሞ ከእንግዲሕ ኬንያዉያን የመረጡትን ፖለቲከኛ ወንጀለኛ ማለት መራጮቹን ከመወንጀል የሚቆጠር ነዉ።

«(ምርጫዉ) ኬንያዉያን በኡሑሩ ኬንያታ ላይ ትልቅ እምነት እንዳላቸዉ የሚያሳይ ነዉ።ሥለዚሕ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት፥ ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ የመረጣቸዉን ፖለተከኛ በሰዎች መግደል ተጠያቂ ከማድረጉ በፊት ሁለቴ ማሰብ አለበት።»

ለኬንያታ ድል፥ ገንዘባቸዉ፥ ጎሳቸዉ፥ የአባታቸዉ ሥም ዝና አስተዋፅኦ አድርጓል የሚሉ አሉ።ሐሰት ነዉ ማለት አይቻልም።ከሁሉም ግን ታዛቢዎቹ እንዳሉት የተመሰረተባቸዉ ክስና የዉጪዎቹ ተፅዕኖ የወለፊንድ ዉጤት ለድሉ ትልቅ ምክንያት ሆኗል።ምናልባት በዓለ-ሲመታቸዉን ባከበሩ ማግሥት ፍርድ ቤት የሚቀርቡ የመጀመሪያዉ ፕሬዝዳት ይሆኑ ይሆናል።ግን ኬንያዎች የነፃ ምርጫን እንዴት ነት አሳይተዋል።ሰዉዬዉም ተመርጠዋል።ኡሑሩ ሙይጋይ ኬንያታ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ























Den Haag, NETHERLANDS: People enter the International Criminal Court, 20 June 2006 in the Hague. Former Liberian president Charles Taylor was today en route to the Netherlands for trial for war crimes. Taylor will be kept in the same jail that held Yugoslav ex-president Slobodan Milosevic. Taylor faces 11 charges of war crimes and crimes against humanity arising from the decade-long civil war in neighbouring Sierra Leone. As soon as he arrives, the former President will be transferred to the detention unit of the International Criminal Court (ICC) which shares a prison with the UN court which tried Milosevic, known as the International Criminal Tribunal for the former Yugoslavia (ICTY). AFP PHOTO ANP JUAN VRIJDAG ** NETHERLANDS OUT ** (Photo credit should read JUAN VRIJDAG/AFP/Getty Images)
ኬንያታ የተከሰሱበት ፍርድ ቤትምስል Getty Images
Supporters of Kenyan presidential candidate Uhuru Kenyatta celebrate on the outskirts of Nairobi March 9, 2013. Kenyan Prime Minister Raila Odinga will not concede this week's election and will launch a legal challenge if rival Kenyatta is officially declared president, an adviser said on Saturday. REUTERS/Goran Tomasevic (KENYA - Tags: POLITICS ELECTIONS)
የኬንያታ ደጋፊዎችምስል Reuters
(130309) -- NAIROBI, March 9, 2013 () -- Kenya's Independent Electoral and Boundaries Commission (IEBC) chairman Issack Hassan addresses the press at the national tallying center in Nairobi, capital of Kenya, March 8, 2013. Kenya's Jubilee Alliance's presidential candidate Uhuru Kenyatta has secured 50.03 percent of votes in general elections, provisional results on early Saturday shows. (/Meng Chenguang)
አስመራጭ ኮሚሽኑምስል picture alliance/Photoshot
Kenyan Vice President Kalonzo Musyoka addresses supporters in Nairobi on December 4, 2012 after agreeing with Prime Minister Raila Odinga and Trade Minister Moses Wetangula to form a powerful alliance as running mates in presidential elections due in March 2013. The former rivals along with leaders of 10 other smaller parties, signed an agreement in front of thousands of supporters to form the Coalition for Reform and Democracy (CORD) party. Odinga is widely tipped to be the presidential candidate with Musyoka as his deputy, although no formal announcement was made. AFP PHOTO / TONY KARUMBA (Photo credit should read TONY KARUMBA/AFP/Getty Images)
ኦዲንጋ:ኪባኪም፤ ኬንያታም አሸነፏቸዉምስል Getty Images/AFP
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ