1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካንኩኑ ጉባዔ ውሳኔ፣

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 4 2003

ለ 2 ሳምንታት በካንኩን ሜክሲኮ ሲካሄድ የሰነበተውና ባለፈው ቅዳሜ የተደመደመው የዓለም የአየር ንብረት ጥበቃ ነክ ጉባዔ፣ ከ 194 ቱ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአየር ንብረት ውል ደጋፊ አገሮች መካከል ፣

https://p.dw.com/p/QXBc

ቦሊቪያ ብቻ ከመቃወሟ በስተቀር፣ የተቀሩት በመጨረሻ የቀረበውን የስምምነት ሰነድ ተቀብለውታል ። ሰነዱ የሆነአሣሪ አለመሆኑ የታወቀ ነው። ከዚያው ከካንኩን የዶቸ ቨለ ራዲዮ ባልደረባ ሄለ የፕሰን የላከችውን ዘገባ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው ሰብሰብ አድርጎ አቅርቦታል።

እ ጎ አ ታኅሳስ 31 ቀን 2012 የሚያከትመውን ከሞላ ጎደል 40 ያህል በኢንዱስትሪ የበለጸጉ መንግሥታት ከየፋብሪካዎቻቸው የሚለቀቀውን የተቃጠለ አየር እንዲቀንሱ ስምምነት የተደረገበትን የኪዮቶው ውል የሚተካው በቅርቡ በካንኩን የተካሄደው ጉባዔ ያስገኛቸው ዋና- ዋና ውጤቶችም ሆኑ ነጥቦች እንዴት ይሆን የሚገመገሙት?!የጀርመን የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ሚንስትር ኖርበርት ሮዖትገን--

1,«2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ፣ ገደብ ይሆን ዘንድ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተቀባይነትን አግኝቷል።ደን ይጠበቅ ዘንድ ግልጽ ውሳኔ ተላልፏል። ዓለም አቀፍ የሥነ ቴክኒክ ትብብር እንዲደረግ፣ የረጅም ጊዜ የገንዘብ ድጋፍም እንዲሰጥ ስምምነት ተደርጓል። በእነዚህ ምክንያቶች፣ እንደሚመስለኝ፤ ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጥበቃ ነክ የድርድር ሂደት እንደገና ለመንቀሳቀስ በቅቷል።»

የድርድሩ ሂደት አሣሪ ወደሆነ ውል እንዲያመራ ማድረግ ያልተቻለበት ምክንያት ፣ በዓለም ውስጥ የተቃጠለ አየር ወደ ከባቢ አየር በመልቀቅ ግንባር ቀደም የሆኑት ቻይናና ዩናይትድ እስቴትስ ተቃውሞ በማቅረባቸው ነው። በመጪው ዓመት መንግሥታት፣ ሜክሲኮ ላይ የተደረሰውን ስምምነት መነሻ በማድረግ፣ እ ጎ አ ከ 2020 አንስቶ የሚመደበውን የ 100 ቢሊዮን ዶላር ድጎማ ፣ ደን ለመንከባከብና ለአየር ንብረት ጥበቃ የሚበጅ ሥነ ቴክኒክ ለመቅሠም እንደሚጠቀሙበት ካሁኑ ማሰላሰል ይዘዋል። የኪዮቶውን ስምምነት በአግባቡ ለመተካት ፣ በመጪው ዓመት በዚህ ወቅት ፣ ደርባን ፤ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በበለጸጉና በአዳጊ አገሮች መካከል ብዙ ፍትጊያ እንደማይቀርም ከወዲሁ እየተነገረ ነው። ዩናይትድ እስቴትስ፣ ወይም የኦባማ አስተዳደር ፣ በዚህ ረገድ አዲስ የተባበሩት መንግሥታት ውል ለማጽደቅ፣ እንበል ከ 100 የህግ መወሰኛ ም/ቤት አባላት ቢያንስ የ 67 ቱን ድጋፍ ማግኘት ይኖርበታል። የሆነው ሆኖ፣ የካንኩኑ ጉባዔ በተደመደበት ሰዓት ፣ የጉባዔው ሊቀመንበር ፣ የሜክሲኮ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ወ/ሮ ፓትሪሲያ ኤስፒኖሳ የስምምነቱን ነጥቦች በዝርዝር ሲያስታውቁ ፣ ሄለ የፕሰን እንደምትለው፣ ሮዖትገንም መርካታቸው ከፊታቸው ይነበብ ነበር። ---

2,(Atm---)

የምድራችን የሙቀት መጠን በአማካይ ከ 2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንዳይበልጥ ስምምነት ላይ መደረሱ ፣ የአየር ንብረትን ለመጠበቅ የሚረዳ ገንዘብ መመደቡ፤ ደኖች እንዲጠበቁ ሆኖም በውስጣቸው የሚኖሩ ነባር ህዝቦች መብት ትኩረት እንዲሰጠው መባሉ ሰፊ ተቀባይነትን ነው ያገኘው። እርግጥ ነው፤ ኪዮቶን በቀጥታ መተካት የሚያስችል ውል መፈረም ባለመቻሉ፣ ካንኩን የተሟላ ስኬት አስገኝቷል ማለት አይቻልም። ይሁንና እ ጎ አ በ 1992 ዓ ም በሪዮ ደ ጃኔሮ የተጀመረው በአየር ንብረት ጥበቃ ላይ ያተኮረው ጉባዔ፣ በመንግሥታትና የመንግሥት ባልሆኑ ድርጅቶች ታምኖበት ቀጣይነት እንዲኖረው ማብቃቱ ዋናው የካንኩን ጉባዔ አዎንታዊ ውጤት ነው ተብሏል። «ጀርማን ዋች» የተሰኘው ፣ ከጀርመን በኩል የመንግሥት ያልሆነው የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ድርጅት ተጠሪ ክሪስቶፍ ባልስ እንዲህ ነበር ያሉት።--

4,«በመጀመሪያ ደረጃ፤ ሂደቱ ሳይጨናጋፍ እንዲቀጥል ለማድረግ ተችሏል። ተሰናክሎ ቢሆን ኖሮ፣ ይኸው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጥበቃ የውይይት ሂደት ትርጉም የለሽ ሆኖ በቀረ ነበር።»

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ