1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የከሸፈው የቱርክ መፈንቅለ-መንግሥት ዳፋ

Eshete Bekeleሰኞ፣ ሐምሌ 11 2008

የቱርክ መፈንቅለ-መንግስት በከሸፈ ማግስት የራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን መንግስት በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል። የእስር እርምጃው ዛሬም ቀጥሎ 103 የጦሩ አመራሮች ታስረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤናሊ ይልድሪም 'ጉድፍ' ካሉት መፈንቅለ-መንግስት በኋላ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ቱርካውያን የግዳጅ እረፍት ተሰጥቷቸዋል።

https://p.dw.com/p/1JR2w
Türkei Nach dem Militärcoup Soldaten werden von Bürger geschlagen
ምስል Reuters

ቱርክ፣ የከሸፈ መፈንቅለ መንግሥት፣ ዳፋ

ቱርክ ከዕለተ አርብ ምሽት ድንገተኛ የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ በኋላ ጸጥታ እና ቁጥጥር ሰፍኖባታል። ራሳቸውን የሰላም ምክር ቤት ሲሉ የጠሩት የጦሩ አባላት በሞከሩት መፈንቅለ-መንግስት ሰበብ ከ2,90 በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከእነዚህ መካከል 161 ሰላማዊ ዜጎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ወታደሮች እና የፖሊስ መኮንኖች ናቸው።

የፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን መንግሥት ከከሸፈው መፈንቅለ-መንግሥት ማግስት በስደት ላይ በሚገኙት ኢማም ፌቱላህ ጉሌን የሚመራው የፌቱላሂች የሽብር ቡድን አባላት ናቸው ያላቸውን 103 ጄኔራሎች እና አድሚራሎች ማሠሩን አስታውቋል። ከከፍተኛ የጦር መኮንኖቹ በተጨማሪ ከዕለተ ቅዳሜ ማለዳ ጀምሮ በመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራው ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ 6,000 ቱርካውያን በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ከእነዚህ መካከል ሁለቱ የቱርክ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ናቸው። በዚህ ግን አልበቃም። 250 ዳኞች እና 2,745 አቃብያነ ሕግ የእስር ማዘዣ ተቆርጦባቸዋል። 8,000 የፖሊስ መኮንኖች በጥርጣሬ ከሥራቸው ታግደዋል።

የፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን መንግስት የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራውን በስደት ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩት ፌቱላህ ጉሌን ቢያቀነባብሩትም የቀድሞው የአየር ኃይል አዛዥ አኪን ኦዝቱርክ መርተውታል ሲል ወንጅሏል። የፕሬዝዳንቱ አማካሪ ኮሎኔል አሊ ያዚቺ በመፈንቅለ-መንግሥቱ ተሳትፎ አድርገዋል ተብለው ከታሠሩት መካከል ይገኙበታል። ምናልባት የቱርክ መንግሥት በኪን ኦዝቱርክ፤ ኮሎኔል አሊ ያዚቺ እና መፈንቅለ-መንግስቱን አቀነባብረዋል በተባሉ ከፍተኛ የጦር ሹማምንት ላይ የሞት ፍርድ ትፈርድ ይሆናል። ፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን በጉዳዩ ላይ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በአገሪቱ ምክር ቤት ሊመክሩበት መዘጋጀታቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
አምባገነን ሆኗል፤ ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን ለፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን በሚመቻቸው መንገድ ጠምዝዟል እየተባለ የሚተቸው የቱርክ መንግሥት፤ ሙከራውን በዴሞክራሲ ላይ የተቃጣ 'ዕድፍ' ሲል ገልጦታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቢናሊ ይልድሪም የከሸፈውን መፈንቅለ-መንግሥት በዕለተ ቅዳሜ «የተከበራችሁ ዜጎች እና የተወደድሽ አገሬ ሆይ የትናንት ምሽት ሐምሌ 15 ቀን ለቱርክ ዴሞክራሲ ጥቁር ዕድፍ ነው።» ነበር ያሉት።
የቱርክ ምክር ቤት በቦምብ ሲደበደብ፤ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በወታደሮች ሲወረሩ እና መፈንቅለ-መንግሥቱ ሲሞከር ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን በአገራቸው የባህር ዳርቻ እረፍት ላይ ነበሩ። ፕሬዝዳንቱ ባረፉበት ሆቴል ላይ ከተፈጸመዉ ጥቃት ያመለጡት ለጥቂት ሲሆን ይጓዙበት የነበረው አውሮፕላን በማርማራ ባህር ሰማይ በተዋጊ የጦር ጀቶች እክል ገጥሞት ነበር ተብሏል።

በአብዛኛው የገዢው የልማት እና ፍትሕ ፓርቲ ደጋፊ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ቱርካውያን የአገራቸውን ሰንደቅ አላማ እያውለበለቡ ወደ አደባባዮች ተመሙ። የፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻንን ጥሪ ሰምተው መንግሥታቸውን ለመታደግ የቆረጡት ዜጎች «አንሸነፍም፤ ሁሉም ነገር ለአገራችን » የሚሉ መፈክሮችን እያሰሙ ነበር። የድንገቴው ዜና በተሰማበት ምሽት በድንገተኛው የህዝብ ሰልፍ «ሰማዕታት አይሞቱም።» «እጆቻችሁን ከቱርክ ላይ አንሱ!» የሚሉ መፈክሮ ከስሜት ጋር ተቀላቅለው በአንካራ እና ኢስታንቡል አደባባዮች ተደምጠዋል።

Türkei Nach dem Militärcoup Soldaten werden von Bürger geschlagen
ምስል Reuters/A. Konstantinidis

መፈንቅለ-መንግስት

ወደ አደባባይ የተመሙት ደጋፊዎች በባዶ እጆቻቸው ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ከታጠቁ የቱርክ ጦር ሠራዊት አባላት ጋር ግብግብ ገጠሙ። ታንኮች ማረኩ። ወታደሮች አንበረከኩ። ግብግቡ የቱርክን ስልጣን ለመቆጣጠር የሚደረግ ያልታሰበ ግን ደግሞ ያልተቀናጀ መፈንቅለ-መንግሥት ጋር ነበር። የዕለተ-አርብ ምሽት እሩምታ ተኩስ እና ፍንዳታዎች የሚደመጡበት አስፈሪ ግን ደግሞ ግራ አጋቢ ምሽት ነበር። ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖች በዋና ከተማዋ አንካራ ሰማይ ሲያንዣብቡ ታዩ። የጦር ሠራዊቱ አባላት በኢስታንቡል ከተማ የሚገኙ ድልድዮችን ዘጉ። ከአገሪቱ ጦር ሠራዊት መካከል የተወሰኑት የፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን መንግሠትን ከስልጣን ማስወገዳቸውን አገሪቱም በቁጥጥራቸው ሥር መሆኗን አወጁ። ራሱን «የሰላም ምክር ቤት» Peace council በማለት የሚጠራ ኃይል የሰብዓዊ መብትን ለማስከበር እና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓትን ለመመለስ ጣልቃ መግባቱን እና ወታደራዊ የሰዓት እላፊ መጣሉን አስታወቀ። በግብግቡ ወታደሮች መፈንቅለ-መንግሥቱን በተቃወሙ ዜጎች ላይ ተኩሰዋል።

የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራው የመክሸፍ ምልክት ያሳየው ፕሬዝዳንቱ እረፍታቸውን አቋርጠው ከኢስታንቡል አየር ማረፊያ መድረሳቸው ሲረጋገጥ ነበር። በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልካቸው ለደጋፊዎቻቸው ያስተላለፉት ጥሪ ስልጣናቸውን ታድጎላቸዋል። ፕሬዝዳንቱ ሙከራው የቱርክን ጦር ለማጽዳት ከፈጣሪ የተሰጠ ስጦታ ብለውታል።

«በስተ መጨረሻ ይህ ተቃውሞ ይህ ሙከራ ከፈጣሪ የተሰጠን ስጦታ ነው። ለምን? ምክንያቱም ይህ እንቅስቃሴው የጦር ሠራዊታችንን ለማጽዳት መነሻ ይሆነናል።»
ማን አሸነፈ?

Türkei Istanbul Demonstration Regierungsanhänger
ምስል Getty Images/AFP/Y. Akgul

በእርግጥ ቱርክ ለመፈንቅለ-መንግሥት አዲስ አይደለችም። የዛሬዋ ቱርክ በአዲስ ራዕይ ከተመሠረተችበት በጎርጎሮሳዊዉ 1920 ዎቹ ጀምሮ የአገሪቱ የልብ ምት ተደርጎ የሚቆጠረው የጦር ሠራዊት ተደጋጋሚ የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራዎችን አድርጓል። የዘመናዊቷ ቱርክ መሥራች ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ የሚያቀነቅኑትን 'መንፈሳዊ ያልሆነ መንግሥት «ራዕይ» ማስጠበቅ ለጦር ሠራዊቱ ጣልቃ-ገብነት በምክንያትነት ይጠቀሳል።

የፖለቲካ ተንታኞች የመፈንቅለ-መንግሥቱ ሙከራ ያልታቀደ፤ ያልተደራጀ እና የጀማሪ ሙከራ ሲሉ አጣጥለውታል። የመፈንቅለ-መንግሥቱ አቀነባባሪዎች የፖለቲካ አመራሩን በቁጥጥር ሥር ለማዋል አሊያም ለሕዝብ ንግግር እንዳያደርግ የሞከሩት አንዳች ነገር አልነበረም። ከተደበቁበት መጋረጃ ወጥተው በይፋ የመሪነት ሚናውን ለመቆጣጠርም አልሞከሩም። መረጃ የሚለዋወጡበትን ዘዴ አልቀየሱም። የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን ተፅዕኖ ጭራሽ ዘንግተውታል። አብላጫውን የቱርክ ጦር ሠራዊትም ይሁን የአገሪቱን ዜጎች ከጎናቸው ለማሰለፍ አልፈቀዱም። ጥቂት መንገዶችን ተቆጣጠሩ፤ ጥቂት የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን ዒላማ አደረጉ። እናም ኤርዶኻን እና መንግሥታቸው አሸነፉ። ዛሬ የቱርክ ዜጎች የመፈንቅለ-መንግሥት ሞካሪዎቹን 'አሸባሪዎች' ብለዋቸዋል። «ይህ የቱርክ ጦር እርምጃ አይደለም። ይህ የሽብር ድርጊት ነው። ቱርክ ደግሞ ለዚህ የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ እጅ አትሰጥም። ቱርክ ሙከራውን ተቋቁማ አሸናፊ መሆን አለባት።» አንድ የአንካራ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ዘጋቢ «ከአንድ መቶ አመታት በላይ የኖርንባትን ይህችን የተቀደሰች መሬት አሳልፈን አንሰጥም። ሦስት እና አራት ዘራፊዎች በእዚህ ዕድል እንዲጠቀሙ ፈቃደኛ አይደለንም።» ሲል ነግሮታል።

መፈንቅለ-መንግሥት በቱርክ እንግዳ ባይሆንም አሁን ግን ፈጽሞ የተጠበቀ አልነበረም። የቱርክን ፖለቲካ የሚከታተሉ ተንትታኞች እንደሚሉት በአገሪቱ የመካከለኛ የጦር መኮንኖች ዘንድ ፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን በሚከተሉት ወግ አጥባቂ ፖለቲካ ደስተኛ ባይሆኑም ለመፈንቅለ-መንግሥት ያደርሳቸዋል ብሎ የገመተ አልነበረም። በጦር ሠራዊቱ እና የፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን የልማት እና ፍትሕ ፓርቲ ግን በመካከላቸው የከረረ ቅሬታ ነበር። በኤርጌንከን (Ergenekon) አለማዊ እና ሕቡዕ ቡድን አማካኝነት የቱርክ መንግሥትን ከስልጣን ለማውረድ አሲረዋል የተባሉ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፤ ታዋቂ ጋዜጠኞች፤ ዳኞችና አቃባያነ- ሕግ እና የተቃዋውሞ ፖለቲከኞችን ጨምሮ 275 ግለሰቦች አወዛጋቢ ክስ ተመስርቶባቸውም ያውቃል። በጎርጎሮሳዊው 2008 ዓ.ም. የተጀመረው ችሎት እስከ 2016 ቢዘልቅም በስተመጨረሻ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግን የተባለው ህቡዕ ቡድን ስለመኖሩ ማረጋገጫ የለም ሲል በይኗል። ትንቅንቁ የቱርክ መንግሥት ዓለማዊ እንዲሆን በሚሹት እና ኃይማኖታዊነትን በሚያቀነቅኑት መካከል ነበር። ፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን ላለፉት አመታት በመንግሥታቸው እና እስላማዊ መሠረት እንዳለው በሚነገርለት የልማት እና ፍትሕ ፓርቲ ላይ የጦሩ እና የፖሊስ ሹማምንት እያሴሩ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ከሰዋል። ፕሬዝዳንቱ በአንድ ወቅት አጋራቸው የነበሩት እና በፈቃደኝነት ስደትን የመረጡት ኢማም ፌቱላህ ጉሌንን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ኤርዶኻን በመፈንቅለ-መንግሥቱ የተገደሉ ሰዎች የቀብር ሥነ-ስርዓት በዕለት እሁድ ሲፈጸም ባደረጉት ንግግር ዩናይትድ ስቴትስ ኢማም ፌቱላህ ጉሌንን አሳልፋ ልትሰጥ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

Türkei Putschversuch Gewalt eskaliert
ምስል picture-alliance/dpa/T. Bozoglu

«ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እነዚህ ሰዎች የመፈንቅለ-መንግሥት እየጠነሰሱ እንደሆነ ነግሬያቸው አውቃለሁ። ነገር ግን ላሳምናቸው አልቻልኩም ነበር። ዛሬ ከዚህ የመፈንቅለ-መንግሥት በኋላ ጉሌንን ለቱርክ አሳልፈው እንዲሰጡ ጥሪ አቀርባለሁ።»

ፌቱላህ ጉሌን በዩናይትድ ስቴትስ የፔንሲልቫኒያ ግዛት ከሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው ሆነው በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ከመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራው ጋር አንዳች ንክኪ የለኝም ሲሉ ተናግረዋል። ቱርክ ተፅዕኖ ፈጣሪው ኢማም ተላልፈው እንዲሰጧት በተደጋጋሚ መጠየቋ የማይቀር ቢሆንም የሚሳካ አይመስልም። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ጆን ኬሪ አገራቸው ጥያቄውን እንደምታጤነው ገልጠዋል፤ ሆኖም ስደተኛው ጉሌን በሴራው እጃቸው ስለመኖሩ ቱርክ ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ አለባት ብለዋል። የቱርክ ሠራተኛና ጸጥታ ሚኒስትር ሱሌይማን ሶይሉ ከከሸፈው መፈንቅለ-መንግሥት ጀርባ የዩናይትድ ስቴትስ እጅ አለበት ሲሉ የሰጡት አስተያየት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የበለጠ ሊያሻክር እንደሚችል ተንታኞች ገልጠዋል።

የመፈንቅለ-መንግስት ሙከራው የቱርክ መንግሥታዊ ስልጣንን ለመጠቅለል ይፈልጋሉ ተብለው ለሚታሙት ፕሬዝዳንት ራቺብ ጠይብ ኤርዶኻን መልካም አጋጣሚ ሊሆንም ይችላል። ፓርላሜንታዊ የሆነውን የቱርክ መንግሥታዊ ሥርዓት ፕሬዝዳንታዊ ለማድረግ ይህ ሁነኛ ደጋፊ መከራከሪያ ሳይሆንላቸዉም አይቀርም።

በተከታታይ በተፈጸፀሙ የአሸባሪ ጥቃቶች ስትናጥ ለከረመችው ቱርክ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች መፍጠሩ አልቀረም። የአውሮጳ ኅብረት በቱርክ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በመከረበት ጉባዔ የተገኙት የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ሙከራውን አውግዘው የኤርዶኻን መንግሥት አምባገነን ለመሆን መፈንቅለ-መንግሥቱን እንደምክንያት እንዳይጠቀምበት አሳስበዋል።

« የቱርክ መንግሥት በመላ ሀገሩ ፀጥታ እና መረጋጋትን እንዲያሰፍን፣ እንዲሁም፣ ለሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እና ለሕግ የበላይነት የተቀመጠውን ከፍተኛ ክብር እንዲጠብቅም አጥብቀን እናሳስባለን። ለመፈንቅለ መንግሥቱ ተጠያቂ የሚባሉት ለፍርድ የሚቀርቡበትን ሂደት በርግጥ እንደግፋለን፣ ይሁንና፣ ሂደቱ ከዚያ እንዳያልፍ ጥንቃቄ እንዲደረግ እና አሁን ያለው ዴሞክራሲያዊ አመራርም እንደተጠበቀ የሚቆይበት አሠራር አስፈላጊ እንደሆነ በአፅንዖት እናጎላለን። »

የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ፌዴሬካ ሞጌሪኒ በበኩላቸው የከሸፈውን የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ ምክንያት በማድረግ ምንም አይነት ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ እርምጃን ተግባራዊ እንዳይደረግ አስጠንቅቀዋል። «መፈንቅለ-መንግስቱን በማውገዝ ቀዳሚ ነበርን።» ያሉት ኃላፊዋ አሁንም የሕግ የበላይነት እንዲከበር አሳስበዋል።

« የሞቱን ቅጣት የሚጀምር ማንኛውም ሀገር የአውሮጳ ህብረት አባል ሊሆን አይችልም። «የጋራ አቋማችን» በምንለው አሰራራችን ይህ ግልጽ ነው። ይህ በአጽንዖት ላነሳው የምፈልገው ጉዳይ ነው፣ ምንም እንኳን ስለዚሁ ጉዳይ የሚመለከተውን ተቋም ወክዬ መናገር ባይገባኝም፣ ቱርክ የአውሮጳ ምክር ቤት ዋነኛ አካል እንደመሆንዋ መጠን፣ በሞቱ ቅጣት ላይ ግልጽ አቋም ባለው በአውሮጳ የሰብዓዊ መብት ውል መገዛት ይኖርባታል።»

የቱርክን የአውሮጳ ኅብረት የአባልነት ጥያቄ የሚመረምሩት ጆሐንስ ሐን በበኩላቸው የቱርክ መንግስት ከመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራው አስቀድሞ ሊያስራቸው የሚፈልጋቸውን እንደ ዳኞች ያሉ ግለሰቦችን ዝርዝር ሳያዘጋጅ አይቀርም ሲሉ ተችተዋል። ቱርክ ለአውሮጳ ኅብረት የአባልነት ጥያቄ ከማቅረቧ በፊት የሞት ቅጣትን በጎርጎሮሳዊው 2004 ዓ.ም. እርግፍ አድርጋ ለመተው መቁረጧን አመላክታለች።

Türkei Aufständischer Soldaten werden vor Gericht in Mugla gebracht
ምስል picture-alliance/abaca/T. Adanali

ፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን ቱርክን ከ'ቫይረስ' የማጽዳት ያሉትን ዘመቻ ሳይጀምሩ አይቀሩም። መንግሥታቸው ለአንካራ የጸጥታ ጥበቃ 3,000 ፖሊሶችን ከአጎራባች ግዛቶች ማምጣቱን ሬውተርስ ዘግቧል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤናሊ ይልድሪም በበኩላቸው ሦስት ሚሊዮን ቱርካውያን በግዳጅ የአመት እረፍት እንዲወጡ መደረጉን አስታውቀዋል። ቱርክ የመፈንቅለ-መንግሥቱ ቢከሽፍላትም ዳፋው ግን እንዲህ በቀላል የሚለቃት አይመስልም።


እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ