1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦነግ አመራር አካላት ውዝግብና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 10 2013

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራር አባላት፤ ሊቀመንበርም ሆነ በሊቀመንበሩ ታግደዋል የተባሉት ስራ አስፈጻሚዎች ህጋዊ የድርጅቱ አካላት ሆነው እንዲቀጥሉ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ መግለጫውን ተከትሎ ሁለቱ ወገኖች መግለጫውን በይሁኝታ መመልከታቸውና አፈጻጸሙንም በቀጣይነት እንደሚከታተሉት ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/3mx8y
 Logo Oromo Liberation Front

የኦነግ ባለስልጣናት ለምርጫ ቦርድ መግለጫ የሰጡት ምላሽ

በአመራር አካላት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት አስመልክቶ የተለያዩ አቤቱታዎች ሲደርሱት እንደነበር ያስታወቀው ቦርዱ፤ የፓርቲው የተወሰኑ የስራ አስፈጻሚ አባላት ነሃሴ 01 ቀን 2012 ዓ.ም በተጻፈ እና በድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አራርሶ ቢቂላ በተፈረመ ደብዳቤ የድርጅቱ ሊቀመንበር መታገዳቸውን ለቦርዱ ማሳወቃቸውን ጠቅሷል፡፡ በሌላ በኩል የድርጅቱ ሊቀመንበር መስከረም 02 ቀን 2013 ዓ.ም ድርጅቱ ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ አድርጎ የፓርቲውን ምክትል ሊቀመንበር፣ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት እስከሚቀጥለው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ ከሃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩ መወሰኑንም አሳውቆ እንደነበር ቦርዱ ገልጿል፡፡ 
በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀፅ 74 ንዑስ አንቀፅ 6 መሠረት ከሁለቱም ወገኖች አንድ አንድ ሰው ተወክለው በተሳተፉበት በባለሙያዎች ጉባኤ ጉዳዩን ለማየት ጥረት ማድረጉንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡ ሆኖም በሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳ በኩል ተወካይ አለመቅረቡና ቦርዱ ይህንን ጉዳይ ለማየት ፍቃደኛ የሆነ ባለሞያ ባለማግኘቱ በራሱ ጉዳዩን መርምሮ ለመወሰን መገደዱንም ነው ያሳወቀው፡፡ 
በዚህም መሰረት በሁለቱም ወገን ያሉ የፓርቲው አመራሮችን ማነጋገሩን ያሳወቀው ቦርዱ፤ በድርጅቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አራርሶ ቢቂላ ፊርማ የተላከለትን የድርጅቱን ሊቀመንበር የታገዱበትን ስብሰባ የሚገልጸውን ቃለጉባኤ ተመልክቶ በቃለጉባኤው ላይ የተገኙት ስራ አስፈጻሚ አባላት ከስምንቱ አምስት መሆናቸውን፣ ከአምስቱ መካከልም አንዱ አባል ከዚህ ቀደም በዜግነታቸው የተነሳ ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የተቀነሱ በመሆናቸው ስራ አስፈጻሚው ስብሰባ የሚጠበቀውን 2/3ተኛ ምልዓተ ጉባኤ ያልተሟላበት በመሆኑ ውሳኔ ህጋዊ ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡
በሌላ በኩል በአቶ ዳውድ ፊርማ የብሔራዊ ምክር ቤት ውሳኔ ነው ተብሎ ለቦርዱ የቀረበው የፓርቲውን ምክትል ሊቀመንበር፣ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት እስከሚቀጥለው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ ከሃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩ የተወሰነው ውሳኔ ስብሰባው በትክክል መካሄዱን የሚያሳይ ቃለጉባኤ የሌለው፣ ምን ያህል የምክር ቤት አባላት እንደተሳተፉበት እና በምን አይነት ድምጽ አሰጣጥ የሚለውን የማያሳይ በሊቀመንበሩ ፊርማ ብቻ የተላከ ውሳኔ በመሆኑ ህጋዊ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አክሏል፡፡
በመሆኑም የፓርቲው ሊቀመንበርም ሆነ በሊቀመንበሩ ታግደዋል የተባሉት ስራ አስፈጻሚዎች ህጋዊ የድርጅቱ አካላት ሆነው ይቀጥላሉ ብሏል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በውሳኔው፡፡ 
ቦርዱ ከሁለቱም ወገኖች ጋር ባደረገው ውይይት የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ በታህሳስ 2013 ዓ.ም መደረግ እንደሚገባው ምክር ቤቱ ቀደም ሲል የወሰነ እንደነበረ በማረጋገጥ፤ ኦነግ እስከ ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ ከሚገባቸው ፓርቲዎች አንዱ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ሁለቱም ወገኖች የሚገኙበት የመጀመሪያ ስብሰባቸውንም በቦርዱ ስብሰባ አዳራሽ እንዲያከናውኑ መወሰኑንም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አሳውቋል፡፡
ስዩም ጌቱ

ልደት አበበ