1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦነግ ሸኔ ተጠርጣሪዎች

ሐሙስ፣ ጥር 19 2014

በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ከ1 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ እየተጣራ መሆኑን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ዐሰታወቀ። በጦርነቱ ወቅት በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሰብአዊ ጥሰትና የንብረት ውድመት መድረሱን የብሔረሰብ አስተዳደሩ አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/46BPR
Äthiopien Stadtbild aus der Stadt Kemise in der Amhara-Region
ምስል Seyoum Getu/DW

«ከ1 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ እየተጣራ ነው»

በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ከ1 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ እየተጣራ መሆኑን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ዐሰታወቀ። በጦርነቱ ወቅት በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሰብአዊ ጥሰትና የንብረት ውድመት መድረሱን የብሔረሰብ አስተዳደሩ አመልክቷል። የማኅበራዊ መስጫ ተቋማት አገልግሎት እየጀመሩ መሆኑንም አስተዳደሩ ገልጧል። ከከሚሴ ከተማ ንብረት የወደመባቸው ባለሀብት መንግሥት የሕግ ማስከበር ሲል የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። 

ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት ነበራቸው ተብለው የተጠረጠሩ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በወረራው ወቅት ከ260 በላይ ንፁሐን መገደላቸውንና ከ170 በላይ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ያመለከቱት አቶ አህመድ በንብረትም ከ 1ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን አብራርተዋል፡፡ የብሔረሰብ አስተዳደሩን ወደነበረበት ለመመለስ የተፈጥሮ ሥራን ማከናወን፣ የመልሶ ማቋቋምና ሌሎች ተግባራትን እየሰሩ እንደሆነ ነው ያስረዱት።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ጀማል ሐሰን በበኩላቸው፣ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች መመሪያ እንደአዲስ ተቋቁሞ በግብርናው ዘርፍ የተሻለ ለማምረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፣ ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም ወደ ስራ ገብተዋል ብለዋል። በከሚሴ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ ባለሀብት ከ60ና 70ሚሊዮን በላይ የሚገመት ንብረታቸው ውድመትና ዝርፊያ እንደተፈፀመበት አስታውሰው መንግስት የሕግ ማስከበር ሲል የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልና በአካባቢው ሰላም እንዲያሰፍን ጠይቀዋል። የብሔረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ባለሀብቶች ንብረታቸው መዘረፉንና መውደሙን አረጋግጠው የተዘረፉ ንብረቶች እንዲመለሱ፣ አጥፊዎች ደግሞ በሕግ እንዲጠየቁ ይደረጋል ብለዋል።

በከሚሴ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ ባለሀብት ከ60ና 70ሚሊዮን በላይ የሚገመት ንብረታቸው ውድመትና ዝርፊያ እንደተፈፀመበት አስታውሰው መንግስት የጀመረውን የሕግ ማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልና በአካባቢው ሰላም እንዲያሰፍን ጠይቀዋል። የብሔረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ባለሀብቶች ንብረታቸው መዘረፉንና መውደሙን አረጋግጠው የተዘረፉ ንብረቶች እንዲመለሱ፣ አጥፊዎች ደግሞ በሕግ እንዲጠየቁ ይደረጋል ብለዋል። ከአማራና ከአፋር አዋሳኝ አካባቢዎች ጋር ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ውይይቶች እየተካሄዱ መሆንንም ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል። ብሔረሰብ አስተዳደሩ ቀደም ሲል ከአመራሩ ጋር ይነሱ የነበሩ ችግሮችን ለማረመረ እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር አዲስ የአመራር አደረጃጀቶች መደረጋቸውንም አስረድተዋል። 

ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ