1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእንጦጦ የሕዋ ምርምርና ማሰልጠኛ ማዕከል

Eshete Bekeleረቡዕ፣ ጳጉሜን 4 2007

ኢትዮጵያ በእንጦጦ ተራራ ላይ በሁለት ቴሌስኮፖች የመጀመሪያውን የሕዋ ምርምርና ማሰልጠኛ ማዕከል ከፍታ ስራ ከጀመረች ጥቂት ወራት አስቆጠረች። ማዕከሉ ከሶስት እስከ አምስት አመታት ውስጥ ሳተላይት የመስራትና የማምጠቅ እቅድም ሰንቋል።

https://p.dw.com/p/1GTrn
Installation Teleskope in Addis Abeba
ምስል DW/Getachew Tedla Hailegiorgis

lእንጦጦ የሕዋ ምርምርና ማሰልጠኛ ማዕከል

ከባህር ጠለል በላይ 3200 ሜትር (10, 500 ጫማ)ከፍታ ላይ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አናት እንጦጦ ላይ ኢትዮጵያውያን ሩቁ፤ ውስብስብና ምስጢራዊውን ሕዋ የሚመለከቱባቸው ሁለት ዘመናዊ ቴሌስኮፖች ተተክለዋል። ቴሌስኮፖቹ የአንድ ሜትር የጎን ስፋት ያላቸው ሁለቱ ቴሌስኮፖች ቴክኖሎጂው ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ አንፃር አነስተኛ ይሁኑ እንጂ ለአገሪቱ ብሎም ለቀጣናው አዲስና ብርቅ ሆነዋል።

ዶ/ር ሰለሞን በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰርና መምህር ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዋ ሳይንስ ሶሳይቲን ከመሰረቱ በዘርፉ በፍቅር ከተነደፉ ሰዎች አንዱ ናቸው። የፖለቲካ ሰዎችን፤ የህግ ባለሙያዎችን እና የዘርፉ ምሁራንን ያካተተው የነ ዶ/ር ሰለሞን ማህበር ከተመሰረተ አስር ዓመታት አልፈውታል።

ሶስት ሚሊዮን ዶላር ወይም 2.7 ሚሊዮን ዩሮ አካባቢ ወጪ የተደረገባቸውና ከጀርመን ኩባንያ የተገዙት ቴሌስኮፖች ያረፉት ከገበሬ መንደሮች አቅራቢያ ነው። የእንጦጦ ኦብሰርቫቶሪ ወይም እንጦጦ ህዋ ምርምርና ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና ኋላፊ ዶ/ር ሰለሞን «እኛ ከጠበቅንው በላይ በሩቅ ያለውን ጋላክሲ ተመልክተናል።ፕላኔቶችንም በሙሉ ተመልክተናል። » ሲሉ የአዳዲሶቹ ቴሌስኮፖች የመጀመሪያ ስራ ይናገራሉ።

Neue Modellrechnung zur Entwicklung des Universums
ምስል picture-alliance/dpa/Illustris Collaboration

የኢትዮጵያ ሕዋ ሳይንስ ማህበር ከሼክ ሙሐመድ አላሙዲ በተደረገለት የገንዘብ ድጋፍ በእንጦጦ ነው፤ እንጦጦ ላይ የሰፈረውን ማዕከል ያስገነባው። ስራ ከጀመረ ጥቂት ወራት ብቻ ያስቆጠረው ማዕከል በሕዋ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ላይ ትኩረት ካደረጉ ጥቂት የአህጉሪቱ አገሮች ተርታ አስመድቧታል። ገና ካሁኑም በሩን ለተማሪዎች ክፍት አድርጓል። ዶ/ር ሰለሞን ማዕከሉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምሰሶ ለሆነው ግብርና የሚያበረክተው አስተዋፅዖ አለ ብለው ተስፋ ሰንቀዋል።

«መሬት ምልከታ በቀጥታ ከግብርና ጋር ግንኙነት አለው። የአየር ሁኔታን፤ዘመናዊ አመራረትን፤ድርቅን አስቀድሞ ለመተበይና ውሃን ለማጥናት ይረዳናል።»

የሰው ልጅ የሚኖርባት ምድር፤የሚሞቃት ጸሐይ በውበቷ የሚደመምባት ጨረቃና ክዋክብቱ የት መጣነት ከሐይማኖት ባሻገር ዛሬም ድረስ ምላሽ አላገኘም። አንዳንዶች ባዶ የኮረት ስብስብ የሚሉት ውስብስቡ ሕዋ የሰው ልጅን ማባከን ከጀመረ ዓመታት አስቆጠረ። የስነ-ፈለክ ምርምር ሩሲያና አሜሪካ በቀደምትነት ጀምረውት በሐብታም ምዕራባውያን አገራት ያደገ ዘርፍም ነው።

ዶ/ር ያብባል ታደሰ የዶክትሪት ማዕረግ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በሮም ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ላይ ተሰማርተዋል። ወጣቱ ዶ/ር በአውሮጳ ሕዋ ሳይንስ ማዕከል የመረጃ ትንተና ሥራም ይሰራሉ። «በደንብ የተራቀቀ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ደሐ አገር ነው የሚያስፈልገው።» የሚሉት ዶ/ር ያብባል የእንጦጦ ሕዋ ምርምር ማዕከል ያሉበትን የሰለጠነ የሰው ሃይል ችግሮች በሂደት መፍታት እንደሚችልም ተስፋ አላቸው። እንደ ዶ/ር ያብባል ከሆነ ማዕከሉ የራሱን ጥናትና ምርምሮች ከመስራት ባሻገር በሌሎች መሰል ተቋማት የተገኙ መረጃዎችን የመተንተን አቅምን በማዳበር ለጥቅም ማዋል ይችላል።

ማዕከሉ የሕዋ ሳይንስ ትምህርትን በአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመጀመር እቅድ አለው። በመገባደድ ላይ በሚገኘው የትምህርት ዘመን 17 የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን አሰልጥኗል። ካሁን ቀደም በሕዋና ተዛማጅ የጥናትና ምርምር ዘርፎች የተማሩ ኢትዮጵያውያን ከአገር ከወጡ አይመለሱም። ዶ/ር ሰለሞን በላይ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንን ጭምር ተመልሰው በማዕከሉ እንዲሰሩ በመጋበዝ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የእንጦጦ ህዋ ምርምርና ማሰልጠኛ ማዕከል ጅማሮው የቅርብ ቢሆንም ሰፊ እቅድ ሰንቋል።በሕዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ማካሄድ፤የኢትዮጵያን አቅም መገንባትና በዘርፉ ዓለም አቀፍ ግንኙነት መፍጠር ቀዳሚ ናቸው ሲሉ ዶ/ር ሰለሞን በላይ አስረድተዋል።

NASA Mond Erde
ምስል NASA

ኢትዮጵያ እስካሁን ብሄራዊ የጠፈር ምርምር ተቋም ባይኖራትም መንኮራኩር ወደ ሕዋ ለማምጠቅ ካሰበች ከራርማለች። ከእነዚህ መካከል አንዱ ከመሬት እስከ 30 ኪ.ሜ ርቀት የሚወነጨፍ መንኮራኩር ለመስራት ያቀደው የመቀሌ የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ይገኝበታል።

እንጦጦ የከተመው አዲሱ የሕዋ ምርምርና ማሰልጠኛ ማዕከልም ከሶስት እስከ አምስት በሚደርሱ ዓመታት የራሱን ሳተላይት የማምጠቅ አሳብ ሰንቋል።

የእንጦጦ ሕዋ ምርምርና ስልጠና ማዕከል ከሁለቱ ቴሌስኮፖች የተሻለ አቅም ያላቸውን በላሊበላ አካባቢ ለመትከል ጥናት ጀምሯል። የኢትዮጵያ መንግስትም ብሄራዊ የሕዋ ምርምር ተቋም ለመመስረት ሃሳብ ላይ ነው ተብሏል። ኢትዮጵያውያኑ የሕዋ ምርምርና ጥናት ለድህነት መፍትሄ ነው ብለው ተስፋ አድርገዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ