1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእነ ዶክተር መረራ ጉዲና የወንጀል ክስ

Merga Yonas Bula
ዓርብ፣ የካቲት 17 2009

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፣ዶክተር መረራ ጉዲና፣ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ፣ እና አቶ ጀዋር መሃመድን የአገሪቱን «ሕገ መንግሥታዊ ስርዓት በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል» ከሷል። የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቬዥንና የኦሮሞ ሚድያ ኔትዎርክ ለነዚህ ተከሳሾች እንደ «ልሳን» አገልግለዋል ሲል የክስ ዝርዝሩ ይጠቅሳል።

https://p.dw.com/p/2YE7R
Äthiopien Journalisten Martin Schibbye und Johan Persson
ምስል AP

Merera et al Criminal Charge - MP3-Stereo

በትናንትናዉ እለት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲናን ጨምሮ ሁለት ግለሰቦችና ሁለት ተቋሞች ላይ የወንጀል ክስ መሥርቷል። ዶክተር መረራ ከኅዳር 21 ቀን 2009 ዓ/ም ጀምሮ እስር ላይ ይገኛሉ። ሌሎቹ ማለትም ዶክተር ብርሃኑ ነጋ፣ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመነበር እና የየፖለቲካ እና የመብት ተሟጋች የሆኑት አቶ ጀዋር መሃመድ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሳትላይት ቴሌቪዥንና የኦሮሞ ሚድያ ኔትዎርክ በሌሉበት አቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል።

ሦስቱም ተጠርጣሪዎች «ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ስረዓቱን በኃይል እንናስወግዳለን» በማለት እንደተንቀሳቀሱ የወንጀል ዝርዝሩ ያመለክታል። ሁለቱ ተቋሞች ደግሞ ለሦስቱም ግለሰቦች «ልሳን» በመሆን በአገሪቱ ዉስጥ የነበረዉን ተቃዉሞ አባብሰዋል፣ ለንብረት መዉድምና ለሰዉ ሕይወት መጥፋትም ምክንያት ሆኖዋል በሚል ተከሰዋል።

ዶክተር መረራ በማዕከላዊ እስር ላይ እንደሚገኙ የሚናገሩት ጠበቃቸዉ አቶ ወንድሙ ኢብሳ ደንበኛቸዉ በወንጀል መቅጫ መከሰሳቸዉ ይናገራሉ። 

Dr. Merera Gudina Addis Abeba Äthiopien Oromo Pressekonferenz PK
ምስል DW/Y.Egziabhare

መንግሥት «የሽብርተኛ» የሚለዉ ቡድን አመራር መሆንን ጨምሮ በተመሳሳይ ክስ የተመሠረተባቸዉ ሁለተኛዉ ተከሳሽ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶክተር ብርሃኑ ነጋ፤ እንዲህ ዓይነት ክስ ለእኔ መጀመርያ አይደለም ይላሉ። እሳቸዉ በሚመሩት ድርጅት ላይ የቀረበዉን ዉንጀላም መሰረተ ቢስ ክስ መሆኑን ይናገራሉ።

«ስርዓቱ የኔን ስም ተጠቅሞ ዶክተር መረራን ለመጉዳት ያሰበበት ክስ ነዉ» የሚሉት ደግሞ ሦስተኛ ተከሳሽ አቶ ጀዋር መሃመድ ናቸዉ።

አቶ ጀዋር በአምስተኛ ደረጃ ላይ ክስ የተመሰረተበት የኦሮሞ ሚድያ ኔትዎርክ (OMN) ሥራ አስኪያጅም ናቸዉ። የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ ግዜያት «ሲወነጅለን ነበር» የሚሉት አቶ ጃዋር የሚመሩትን ተቋም ከክሱ ነፃ መሆኑን ይናገራሉ።

ዶክተር መረራ እስከ ትላንትና ድረስ ክስ ሳይመሰረትባቸዉ ለ85 ቀናት በእስር እንደቆዩ ጠበቃቸዉ አቶ ወንድሙ ኢብሳ ገልጸዋል። ትላንትና የዋስትና መብት እንዲጠበቅላቸዉ ስምንት ሰዓት ላይ ቀጠሮ ነበራቸዉ። ይሁን እንጂ የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት «ጠዋት ሁለት ሰዓት ላይ ሦስት ዳኞች ባሉበት  እሳቸዉ ብቻ ቀርበዉ ክሱ እንዲነበብላቸዉ ሲጠየቁ ጠበቆቼ ሳይቀርቡ አይቻልም በማለታቸዉ ለዛሬ ሳምንት ቀጠሮ» እንደተሰጣቸዉ አቶ ወንድሙ አመልክተዋል።

ለበለጠ ማብራርያ አዉድዮዉን ያዳምጡ።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ