1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሺሪላንካ ሽብር፣ሊቢያ ጦርነት፣ ዩክሬን ምርጫ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 14 2011

የመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት የተጠናቀቀዉ በአራት ዓመቱ ነዉ።ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት የፈጀዉ 6 ዓመት ነዉ።ብቸኛዋ ልዕለ ኃይል ዩናይትድ ስቴትስ የመራችና ያስተባበረችዉ ዓለም አሸባሪዎችን ለማጥፋት ጦርነት ካወጀ 18 ዓመቱ

https://p.dw.com/p/3HELt
Sri Lanka Anschlag Terror Ostern
ምስል Reuters/A. Dave

ሽብር፣ጦርነትና ምርጫ

 

የታሚል ኤላም ነፃ አዉጪ አምበሶች (LTTE) የተሰኘዉ የሺሪላንካ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን በ2009 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)መደምሰሱ ለሕንድ ዉቅያኖሲቱ ትልቅ ደሴት የሠላም መረጋጋት፣ብሥራት ሆኖ ነበር።የድል ማግሥት ፖለቲከኞችዋ ሲሻኮቱ ግን ሕዝብ፣ቤተ-እምነት ሆቴሎታቸዉን የአሸባሪዎች ቦምብ ሲሳይ አደረጉት።ዕሁድ።ሺራላንካ 26 ዓመት ያደማትን  ጦርነት ማቆምዋን ባወጀች በሁለተኛዉ ዓመት የ40 ዘመን ገዢያዋን በህዝባዊ አመፅና በኔቶ ጦር ጡንቻ ያስወገደችዉ ሊቢያ፣ ከፓሪስ፣ለንደን ዋሽግተን የተነገረዉ የሠላም ዴሞክራሲ ቃል፣ተስፋ ለፖለቲከኞችዋ ግርሻ ሆኖ እልቂት ፍጅት ጥፋት ያስተፋቸዋል።ከሺራልካ ከተል፣ ከሊቢያ ቀደም ብላ በሕዝባዊ አመፅ፣ በአማፂ ቡድናት ጦርነት፣ በኃይል ጎረቤትዋ ጫና ግራ ቀኝ ሥትላጋ የቆየችዉ ዩክሬን ግን ዕዉቅ ኮማኪዋን ለመሪነት መርጣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ጅምሯን አፀናች። የእስያ አፍሪቃ አዉሮጶቹ ሐገራት ሰሞናዊ እዉነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።

የቡደሐ ቅርሶችዋ፣ የሐር መንገድ (Silk Road) ከሚባለዉ ጥንታዊ የንግድ ጎዳና እስከ ዘመናዊዉ የባሕር ጎዞ ተፈላጊ የሆነዉ ሥልታዊ አቀማመጥዋ፣ የሻቅጠል የቅመም ምርቷ የየዘመኑን ኃያል ትኩረት እንደሳበች ከ3ሺሕ ዘመን በላይ አስቆጥራለች።ሳይሎን።

ዛሬ የያዘችዉን ሥም፣ ሪፐብሊካዊ አስተዳደርና የፖለቲካ ሥርዓት ካወጀች ከ1972 ወዲሕ ከጥንታዊ ቅርስ፤ ሥልታዊ አቀማመጥ፤ ከማራኪ የባሕር ዳርቻዎቿ፣ ከቅመም ምርቷ እኩል የፖለቲካዋ መጠላለፍ፣ የነገዶችዋ መናቆር፣የምዕራብ-ምስራቆች መሻኮት መለያዋ ሆነ።

Libyen Konflikt l Demonstrationen gegen die Offensive von Khalifa Haftar in Tripolis
ምስል Getty Images/AFP/M. Turkia

ታሚል የሚባለዉ ጎሳ በብዛት የሚኖሩበትን የሰሜናዊና ምሥራቃዊ ግዛትን ከኮሎምቦ ማዕከላዊ መንግስት አስተዳደር ለመገንጠል የሚፋለመዉ የታሚል ኤላም ነፃ አዉጪ አንበሶች (LTTE) ከተመሠረተ ከ1976 በተለይ ይፋ ጦርነት ከታወጀባት  ከ1983 ወዲሕ፣ የኃያላን መሻኮቺያ፣ የርስ በርስ ጦርነት፣ የሽብር ግድያ  ምሳሌ ሆናለች።

ፕሬዝደንት ማሒዳ ራጃፓካሳ እንደ ጠቅላይ አዛዥ፣ሌትናንት ጄኔራል (ኋላ ፊልድ ማርሻል) ሳራት ሳራት ፌንሴካ እንደ ጠቅላይ ኤታማዦር የመሩት ጦር በ2009 የአማፂዉን ነብር ሕልቅት ፈጥርቆ ማጥፋቱ፣ብዙዎች እንዳሉት ለጥንታዊ፣ ሥልታዊ፣ ዉብ ደሴት በርግጥ ትንሳኤ ነበር።

ይሁንና ድል-አድራጊና የድል ማግሥት ፖለቲከኞች የሕዝባቸዉን ደሕንነት፣ የሐገራቸዉን ሠላምና አንድነት ከማስከበር፣ ይልቅ አንዱ ሌላዉን ጥሎ ሥልጣን ለመያዝ ሲጠላለፉ ከጦርነት ሽብር ተላቀቀች በተባለ በ10ኛ ዓመቷ የአሸባሪዎች ጥፋት አብነት ሆነች።«የሆነዉን አናዉቅም።ስልክ ስንደዉል አይመልስም።አሁን መገደሉን ፖሊስ ነገረን።»

Libyen | Libyens international anerkannte Regierungstruppen schießen bei Kämpfen mit östlichen Truppen in Ain Zara
ምስል Reuters/H. Amara

በቦምብ ከተገደሉት ፖሊሶች የአንዱ ታላቅ ወድም።ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራዉ ዘመኑን በጎርጎሪያኑ አቆጣጠር የሚያሰላዉ ክርስቲያን የየሱስ ክርስቶስን ትንሳዔ ለማክበር ሲታደም ዕሁድ ያቺ ትልቅ ደሴት 300 መቶ ዜጋ፣እንግዳ፣ ሐገር ጎብኚችዋን ለአሸባሪዎች ቦምብ ገበረች።«ተከታታዩ ፍንዳታ በ1990ዎቹ በየአዉቶብሱ የሚደርሰዉን ፍንዳታ ያስታዉሰናል።» ይላሉ ማላሐ ዊክራማ የተባሉ የኮሎንቦ ነዋሪ።

የኮሎምቦ ፖለቲከኞች አደጋ እንደሚደርስ ጥቆማ ደርሷቸዉ እንደነበር በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።ይሁንና ፕሬዝደንቱ ከጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከፕሬዝደንቱ ደጋፊ ሚንስትሮች ጋር ሥለሚሻኮቱ የደረሳቸዉን መረጃ አልተጠቀሙበትም።

አደጋዉን መከላከል ያልቻሉት ወይም ያልፈለጉት የኮሎምቦ ባለስልጣን አደጋ አድራሹን ለመጠቆም ግን  ጊዜ አልፈጀባቸዉም።

 «ድርጅቱ፣ ብሔራዊ ተዉፊቅ ጀማዓት ነዉ። የሐገር ዉስጥ ድርጅት ነዉ።ከዉጪ ጋር ግንኙነት ይኑረዉ አይኑረዉ አናዉቅም።»

የጤና ጉዳይ ሚንስትር ራጂታ ሴናራትነ።

የመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት የተጠናቀቀዉ በአራት ዓመቱ ነዉ።ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት የፈጀዉ 6 ዓመት ነዉ።ብቸኛዋ ልዕለ ኃይል ዩናይትድ ስቴትስ የመራችና ያስተባበረችዉ ዓለም አሸባሪዎችን ለማጥፋት ጦርነት ካወጀ 18 ዓመቱ።ዛሬም ሙስሊሞች በየመስጊዱ፣ክርስቲያኖች በየአብያተ ክርስቲያኑ፤ ሐገር ጎብኚዎች በየሆቴል-ባሕርዳርቻዉ፣ መንገደኞች በየአዉቶብስ- ባቡሩ ያልቃሉ።ዓለም ትሸበራለች።ሊቢያ አንዷ ናት።

በ2011 ሳርኮዚ ከፓሪስ፣ ካሜሩን ከለንደን ኦባማ ከዋሽግተን፤ ጅብሪልን ከቤንጋዚ እንደነገሩን ቢሆን ኖሮ ሰሜን አፍሪቃዊቱ አረባዊት ሐገር ዛሬ የአረብ-አፍሪቃ የሠላም፤ዴሞክራሲ፣የፍትሕ ብልፅግና አብነት በሆነች ነበር።

ግን በተገላቢጦሾ፣ ሐብታሚቱ ሐገር ዛሬ ወንበዴዎች በየጎጡ የነገሱባት፣ ጦረኞች የሚፎልሉባት፣ ደካሞች፣ ስደተኞች፣ የሚደበደቡ፣ የሚደፈሩ፤ የሚረግፉባት፤ ፖለቲከኞችዋ የሚያዋጉባት፣ የምዕራብ-ምስራቅ ኃያላን፣የአረብ ቱጃሮች የሚሻኩቱባት ምድር ናት።

የሊቢያ ሕዝብ በረጅም ዘመን ገዢዉ በኮሌኔል ሙዓመር ቃዛፊ ላይ ባደባባይ ከማመፁ ከ7 ዓመት በፊት የዩክሬን ሕዝብ ሙስናን፣ በደልንና የምርጫ ዉጤትን በመቃወም ባደባባይ ተሰልፎ ነበር።ብርቱካናማዉ አብዮት የተባለዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞ በ2005 ለፕሬዝደንትነት ያበቃቸዉ ቪክቶር ያኑኮቪች በተራቸዉ ደም ያፋሰሰ ሕዝባዊ አመፅ ኢላማ ሆነዉ በ2014 ከስልጣን ሲወገዱ የምስራቅ አዉሮጳዊቱ ሐገር ለጋ ዴሞራሲ ተሽመደመደ አሰኝቶ ነበር።

ለሩሲያ ያዳላሉ የሚባሉት ያኑኮቪችን ከስልጣን ያስወገደዉ የአደባባይ ሠልፍና አመፅ ሕዝባዊነቱ፣ፍትሐዊነቱ፣ሠላማዊነቱ፣ ከምዕራባዉያን መንግስታት ጫና የፀዳነቱም ብዙ አጠያያቂ ነዉ።የአመፁ ዉጤት የሞስኮ መሪዎችን አስቆጥቶ ክሪሚያ የተባለችዉን ሥልታዊ ግዛት ከዩክሬን እንዲቀሙ፣ የዩክሬን አማፂያንን እንዲያስታጥቁ ምክንያትም ሆኗል።

ባመፁ ማግስት ስልጣን የያዙት የዩክሬን ፖለቲከኞች ትዕግስት፣ ብልሐት፣ ከሁሉም በላይ ከዋሽግተን ብራስልስ፣ የተንቆረቆረና የሚንቆረቆርላቸዉ ድጋፍ መሠረት ሆኖ ዩክሬን ዩጎዝላቪያን፣ ኢራቂን፣ ሶሪያን፣ ኮንጎን፣ ደቡብ ሱዳንን ወይም ሊቢያን ከመሆን ተርፋለች።ትናንት ያደረገችዉ የመለያ የፕሬዝደንታዊዉ ምርጫ ዉጤት ሲታወጅ ተሸናፊ ፖለቲከኞችዋ፣ ሽንፈትን በፀጋ መቀበላቸዉ ደግሞ 2019ኟ ዩክሬን፣ ከ2004ቷም፣ ከ2014ቷም ዩክሬን ብዙ መብሰሏን መስካሪ ነዉ።ተሸናፊዉ ፕሬዝደንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ።

«ነፃ፣ ትክክል፣ ዴሞክራሲያዊና ተወዳዳሪ ምርጫ ማድረግ በመቻላችን  ደስታዬን መግለጥ እወዳለሁ።ዩክሬን አዲስ ከፍተኛ ደረጃ ያለዉ የዴሞክራሲያዊ የምርጫ ዘመቻ ማስተናገድ መቻልዋን አረጋግጣለች።እና የዩክሬንን ሕዝብ ፍላጎት እቀበላለሁ።ከግባችን ግማሽ መንገድ ላይ ነን።የተሐድሶ አጀንዳችንን መቀጠል አለብን።»

የዩክሬን ሕዝብ ፍላጎት የእስካሁኑ ቀልደኛ  የከንግዲሁ ፕሬዝደንት ናቸዉ።ቮሎድይምየር ዜሌንስኪ።

 «ተፎካካሪያችሁ እንጂ ጠላታችሁ አይደለሁም»

የፖለቲካ እዉቀትም ልምድም፣የሌላቸዉ፣የ41 ዓመቱ ጎልማሳ የሸማቂዎች ዉጊያ፣ ድሕነት፣ ሙስና ተብትቦ የያዘዉን የዩክሬን ፖለቲካ፣ ከሁሉም በላይ ከሩሲያ ጋር የተካረረዉን እሰጥ አገባ መፍታት መቻል-አለመቻላቸዉ አዉሮጶችን እያከራከረ ነዉ።

Ukraine | Präsidentschaftswahlen | Reaktion Wolodymyr Selenskyj
ምስል Reuters/V. Ogirenko

በ1980 ማብቂያ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ በተደረገዉ ምርጫ የቀድሞዉ የራዲዮ ጋዜጠኛና የፊልም ተዋኝ ሮናልድ ዊልያም ሬጋን ሲያሸንፉ ትልቂቱ ሐገር ከተዋኝ እጅ ወደቀች የሚል ትችት፣ወቀሳ ሲጎርፍ ነበር።ሰዉዬዉ ግን የአሜሪካኖችን የወግ አጥባቂ ፖለቲካን ይበልጥ አጥብቀዉ ከአንጎላ እስከ ኒካራጓ፣ ከበርሊን እስከ ሞስኮ የነበረዉን ፖለቲካዊ ስርዓት መነቃቅረዉ፣ የሶቬት ሕብረትን ሞት አጣደፉት።

ጆርጅ ዊሕ ላይቤሪያን እንዴትና ወዴት እንደሚመሯት በርግጥ አላየንም።ከኳስ ተጫዋችነት ወደ ፖለቲከኝነት መለወጡ ግን ብዙ የከበዳቸዉ አይመስልም።ከ1994 ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ በሠላማዊ ምርጫ፣ በሠላማዊ የስልጣን ሽግግር ለመሪነት የበቁ ፖለቲከኛ ሆነዋል።ሰሞኑን ቢሯቸዉን የወረረዉ እባብ ግን ለላቤሪያዎች ሚልኪ ይኖር ይሆን?

የአሸባሪዎችና የደፈጣ ተዋጊዎች ጥቃት፣ የካሽሚር ዉዝግብ ፤ከሕንድ ጋር ያለዉ ፍጥጫ፣የአክራሪ ኃይማኖተኞች ጫና የሚዳክራት ፓኪስታንን  ከነኑክሌር ቦምቧ የሚመሩት ጠቅላይ ሚንስትር ኢምራን ካሕን ናቸዉ። ኪሪኬት ተጫዋች ነበሩ።

እርግጥ ነዉ ዶናልድ ትራም እንደ ልዕለ ኃያል ሐገር መሪ ዓለምን እያስተባበሩ መሆን አለመሆኑ ብዙ ያጠያይቃል።ትራምፕ በትክክል መሩም አልመሩም፣ አስተባበሩም አላስተባበሩ፣ የአሜሪካ ሕዝብ ፖለቲካን ከባለቤታቸዉም፣ከሴናተርነትም፣ ከዉጪ ጉዳይ ሚንስትርነትም የተማሩትን ሒላሪ ክሊንተንን «እንቢኝ» ብሎ የመረጣቸዉ ፕሬዝደንቱ ናቸዉ።

Ukraine | Präsidentschaftswahlen | Reaktion Poroschenko
ምስል DW/L. Rzheutska

ድሮ የቴሌቪዥን ትርዒት አቅራቢና ነጋዴ ነበሩ።ንግዱን አሁንም አልተዉትም።ፖሮሼንኮም ቸኮላት አምራች ነጋዴ ነበሩ።ናቸዉም።ቀልደኛዉ ዜሌንስኪስ ፕሬዝደንት ቢሆኑ ምን ያቅታቸዋል።«የማይቻል የለም» ይላሉም-ሌሎችን ሲመክሩ።

«እናንት የድሕረ-ሶቭየት ሐገራት ሆይ።እነግራችኋለሁ።እኛን ተመልከቱ።ሁሉም ነገር ይቻላል።»

ቮላዲሚየር ኦሌክሳንድሮቪየች ዜሌንስኪ።መቼም የምር ነዉ።ቀልድ አይሆንም። ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ተስፋለም ወልደየስ