1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤች አይቪ ክትባት

ረቡዕ፣ ጥቅምት 11 2002

ዛሬ በፓሪስ ፈረንሳይ በመካሄድ ላይ የሚገኘዉ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ በታይላንድ መገኘቱ ስለተነገረለት የኤች አይቪ ቫይረስ መከላከያ ክትባት ይነጋገራል።

https://p.dw.com/p/KC4n
ምስል AP

በተጨማሪም በታንዛኒያ ተሞክሮ የተሻለ ዉጤት አሳይቷል የተባለዉ በስዊድን ተመራማሪዎች የተገኘዉ የክትባት ዉጤትም ይፋ ይሆናል። በኤች አይቪ ዙሪያ የሚሰራዉ የፀሐይ ፕሮጀክት ኃላፊ ዶክተር ሰሎሞን ዘዉዱ ከዶቼ ቬለ ጋ ይህን ክትባት አስመልክቶ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ምንም እንኳን ክትባት መገኘቱ መልካም ዜና ቢሆንም ጉዳዩ በምርምር በደንብ ቢጠናከር እንደሚበጅ ገልጸዋል።

Infografik HIV Weltweite Verbreitung Stand: 2007 englisch
በዓለም የኤች አይቪ ቫይረስ ስርጭት

በታይላንድ መገኘቱ ከተነገረለት የተሻለ የተባለዉ በታንዛኒያ የተካሄደ የኤች አይቪ ባይረስ ክትባት በታንዛኒያ አዎንታዊ ዉጤት እንዳስገኘ ከስዊድን ስቶክሆልም ተመራማሪዎች አስታወቁ። ከተመራማሪዎቹ መካከል የስዊድን ካሮሊንስካ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ብሪታ ቫህረን ክትባቱ 50በመቶ ቫይረሱን ለመከላከል ይረዳል የሚል እምነት አላቸዉ። የታይላንዱ ክትባት እዛዉ በአገሩ በአሜሪካን ተመራማሪዎች የተሞከረና ስርጭቱን በሶስት እጅ እንደሚቀንስ ይነገራል። ቫይረን ግን እነሱ የሞከሩት ክትባት በአዉሮጳ፤ አፍሪቃ፤ አሜሪካና እስያ የሚታየዉን የቫይረሱን ዝርያ ለመከላከል የሚያስችል ሰፋ ያለ ጠቀሜታ አለዉ ይላሉ። ይህ ሂቪስ የሚል ስያሜ የተሰጠዉ የስዊድኑ ክትባት ታንዛኒያ ዉስጥ በ60 ጤናማ የፖሊስ አባላት ላይ የተሞከረ ሲሆን ሙከራዉ ደረጃ ሁለት መሆኑ ተገልጿል። የመጀመሪያ ደረጃ ሙከራዉ ፈቃደኛ በሆኑ ጥቂቶች ላይ የተካሄደ ሲሆን ሶስተኛ ደረጃና አስተማማኝነቱን የሚያሳየዉ ሙከራዉ ደግሞ በሺዎች በተቆጠሩ ሰዎች ላይ ማካሄድ ይሆናል። ለጊዜዉ ባለባቸዉ የገንዘብ አቅም አናሳነት ምክንያት ግን ወደደረጃ ሶስት ሙከራ አልተሸጋገሩም። ተመራማሪዎቹ እስካሁን የክትባቱን አስተማማኝነት እና ከሰዉነት በሽታን የመከላከል አቅም ጋ የሚኖረዉን አግባብ ተመልክተዋል። ፕሮፌሰር ቫረን እንደሚሉት ዉጤቱ አበረታች ነዉ። በአዉሮጳ ኅብረት ኮሚሽን የኤች አይቪ ኤድስ ምርምር ኃላፊ ማኑዌል ሮማሪስ በበኩላቸዉ የስዊድኑ ክትባት የመጀመሪያ ዉጤት ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ገልፀዋል። እስከዛሬ በዚህ ረገድ ከተካሄዱ ሙከራዎች አበረታች ነዉ ያሉት የስዊድን ተመራማሪዎች ጥረትም በትክክለኛዉ ጎዳና እየተጓዘ ነዉ ሲሉ ምስክርነታቸዉን ሰጥተዋል። የዚህ የስዊድን ተመራማሪዎች የሙከራ ዉጤት እስካሁን ታትሞ አልወጣም። ሆኖም ነገ ፓሪስ ላይ በሚካሄደዉ የኤች አይቪ ኤድስ ክትባት ጉባኤ ላይ ይቀርባል።

ጌታቸዉ ተድላ

ሸዋዬ ለገሠ