1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤቦላ ስርጭት መስፋፋት እና ተፅዕኖው

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 29 2007

ባለፈው መጋቢት ወር በምዕራብ አፍሪቃ ኤቦላ ከተከሰተ ወዲህ ገደማ ከ13,000 የሚበልጥ ሰው በወረርሽኙ አስተላላፊ ተሀዋሲ ሲጠቃ ፣ ከዚሁ መካከል ወደ 5,000 ሰው ሞቶዋል።

https://p.dw.com/p/1DjJv
Ebola Grenze Guinea
ምስል Reuters

በምዕራብ አፍሪቃ ከሚገኙት 16 ሀገራት መካከል ሦስቱ ፣ ማለትም፣ ጊኒ ኮናክሪ፣ ላይቤሪያ እና ሲየራ ልዮን ብቻ ናቸው የኤቦላ ወረርሽኝ የተከሰተባቸው። የወረርሽኙ ስርጭት በነዚህን ሀገራት ላይ በጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ባጠቃልይ እንቅስቃሴአቸው ላይ እያደረሰው ያለው ጉዳት እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን ባካባቢው ተገኝተው ሁኔታዎችን በቅርብ የተመለከቱት የጀርመን መንግሥት የፀረ ኤቦላ ትግል ተጠሪ ቫልተር ሊንድነር አስታውቀዋል።
« የበሽታው ስርጭት መጠን እጅግ ግዙፍ ነው። ምክንያቱም ስርጭቱ በጤናው ዘርፍ ላይ ብቻ አይደለም አሳሳቢ መዘዝ ያስከተለው። በኤኮኖሚው እና በማህበራዊው ኑሮ ዘርፍ እያደረሰው ያለው መዘዝም በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የነዚህ ሶስት ሀገራት ማህበራዊ ኑሮ ዘርፍ በጠቅላላ ትልቅ ስጋት ተደቅኖበታል። »
የኤቦላ ስርጭት የጊኒ፣ ላይቤሪያ እና ሲየራ ልዮንን ኤኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ብዙዎቹ ያካባቢው ሀገራትን የምጣኔ ሀብትንም እየጎዳ መሆኑ ተገልጾዋል። የወረርሽኙ ስርጭት መስፋፋት ባካባቢው አጠቃላይ ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ፣ ብሎም፣ በግብርናው፣ በንግዱ እና በቱሪዝሙ ዘርፍ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፎዋል። በርካታ የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት በመካከላቸው የዕቃ እና የአገልግሎት አሰጣጡን አሰራር ለማፍታታት ባደረጉት ጥረት የንግዱ ዘርፍ ዕድገት ማሳየት ጀምሮ ነበር። ይሁንና፣ ሴኔጋል፣ ኮት ዲቯር እና ጋናን የመሳሰሉት ሀገራት በወረርሽኙ ስጋት ድንበራቸውን የዘጉበት፣ የአየር መንገዶችም ወደተጎዱት ሀገራት በረራ ያቋረጡበት፣ እንዲሁም፣ የውጭ ባለሀብቶች ወረታቸውን በነዚህ ሀገራት ለማሰራት ያመነቱበት ርምጃ ያካባቢው ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ዝግመት ላሳየበት ድርጊት ምክንያት ሆኖዋል። ይኸው ርምጃ በተለይ ወረርሽኙ ለተከሰተባቸው ሀገራት አሳሳቢ መዘዝ እያስከተለባቸው ነው። የውጭ ዜጎች ፣ በተለይ፣ ባለፉት ዓመታት በመላ አፍሪቃ ብዙ ወረት ያፈሰሱት ቻይናውያን ጭምር በጊኒ፣ ላይቤሪያ እና ሲየራ ልዮን በመንቀሳቀሱ አኳያ ትልቅ ጥንቃቄ ሲያደርጉ ይታያል።
የማሊ ተወላጅ የሆኑት ዲያዋራ ኢሳካ ንግድ ቀዝቅዞበታል። ነጋዴው ዲያዋራ ቀደም ባሉ ጊዚያት በባይስክል ወደ ጊኒ በመሄድ ለገበያ የሚያቀርቡትን ዕቃ እየሸመቱ ይመለሱ ነበር። ካለፉት 19 ዓመታት ወዲህ በማሊ እና በጊኒ መካከል በመመላለስ ባካሄዱት በነበረው ንግድ ቤተሰባቸውን ያስተዳድሩ የነበሩት ዲያዋራ አሁን በኤቦላ ስጋት ወደ ጊኒ መጓዝ ማቆማቸውን ነው የገለጹት።
ከጊኒ ጋር የጋራ ድንበር ያላት ትንሿ የማሊ ከተማ፣ ኩሬማሌ ውስጥ ባሁኑ ጊዜ ኤቦላ ዋነኛው የሕዝቡ መወያያ ርዕስ ሆኖዋል። ከአቁመዋል። ልክ እንደ ላይቤሪያ እና ሲየራ ልዮን ወረርሽኙ ባለፈው መጋቢት በመጀመሪያ የተከሰተባት ጊኒ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል። በዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት ግምት መሠረት፣ በሶስቱ ሀገራት ወረርሽኙ ከተከሰተ ካለፉት ዘጠኝ ወራት ገደማ ከ13,000 የሚበልጥ ሰው በወረርሽኙ አስተላላፊ ተሀዋሲ ተይዞዋል። ከሁለት ሳምንታት በፊትም አንዲት በኤቦላ ተሀዋሲ የተያዘች የማሊ ሕፃን ከአያቷ ጋር ከጊኒ ወደ ማሊ ከተመለሰች እና ካጭር ቆይታ በኋላ በዚያ ከሞተች ወዲህ፣ የኩሬማሌ ከተማ ሕዝብ ስጋት እጅግ ከፍ ብሏል። ኤቦላ በከተማይቱ ብዙ ነገር መለወጡን የጊኒ ዜጋ የሆኑት ወይዘሮ ባዬ ዲያሎ ቢያረጋግጡም፣ በጊኒ እና በማሊ መካከል ዝውውሩ በጠቅላላ አለመቋረጡ ጥሩ ነው ይላሉ።
« ሰዎች ከጊኒ ድንበር እየተሻገሩ ወደማሊ ለጉብኝት መሄድ መቻላቸውን ጥሩ ሆኖ አግንቼዋለሁ። »
በንግዱ ሙያ የተሠማሩት የጊኒ ተወላጅ ወይዘሮ ዲያሎ ዕቃ ለመሸመት ወደማሊ ሲጓዙ ሕዝቡ በስጋት እንደሚመለከታቸው ቢገልጹም፣ የማሊ መንግሥት ከጊኒ ጋር የሚያዋስነውን ድንበሩን ባለመዝጋቱ ሊመሰገን እንደሚገባ አስረድተዋል። በማሊ አንፃር፣ ኮት ዲቯር የኤቦላ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ከጊኒ ኮናክሪ ጋር የሚያገናኙዋትን መንገዶች በጠቅላላ ዘግታለች። የማሊ ዜጎች ምንም እንኳን በኤቦላ ስርጭት አኳያ ስጋታቸው ከፍ ያለ ቢሆንም፣ የጊኒን ሕዝብ ይበልጡን እንዳይገለል ለማድረግ የሀገራቸው መንግሥት ድንበሩን ያልዘጋበትን ውሳኔውን ደግፈውታል። በጊኒ እና በማሊ መካከል በረጅም ዓመታት ወዳጅነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ነው ያለው። ከዚህ አልፎም በሁለቱም ሀገራት ብዙዎች በሚናገሩዋቸው ፣ ማለትም፣ በማሊ የባምባራ እና በጊኒ የማንዲንካ ቋንቋዎች መካከል ዝምድና አለ። ይሁንና፣ ይኸው ለብዙ ጊዜ የዘለቀው ወዳጅነት እና ዝምድና ብቻ አይደለም የማሊ መንግሥት ከጊኒ ጋር የሚያዋስነው ድንበር ክፍት ሆኖ እንዲቆይ የወሰነው።
ወደብ ለሌላት ማሊ በጊኒ መዲና ኮናክሪ ያለው ወደብ ከውጭ ው ዓለም ጋር የሚያገናኛት ወሳኝ የኤኮኖሚ ትርጓሜ ይዞዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሰዎች ከጊኒ ወደ ማሊ እንዳይገቡ የጉዞ ዕገዳ ማሳረፉ፣ ቁጥጥሩ አዳጋች ስለሚሆን፣ ጥቅም እንደማይኖረው ብዙዎቹ የማሊ ዜጎች ያውቁታል። እንደሚታወቀው ፣ በዓለም እጅግ ድሆች ከሚባሉት ሀገራት መደዳ የሚቆጠሩት ጊኒ እና ማሊ ከሚጋሩት የጋራ ድንበር መካከል ጥቂቱን ብቻ ነው ጥበቃ ሲደረግበት የሚታየው ። ይህ እና በፖሊስ እና በድን,በር ጠባቂ ኃይላት ዘንድ የተስፋፋው ሙስና የኮንሮባንድ ነጋዴዎች በብዙ መቶ ኪሎሜትር በሚቆጠረው የጊኒ እና ማሊ ድንበር ሕገ ወጡን ንግድ የሚያራምዱበትን መንገድ ፈጥሮላቸዋል። በዚህም የተነሳ የጉዞ ዕገዳ በማድረግ ፈንታ ቁጥጥሩን ማጠናከሩ የተሻለ አማራጭ እንደሚሆን ሁለቱን ሀገሮች በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ በኤቦላ አስተላላፊ ተሀዋሲ ተይዘዋል ተብለው ለተጠረጠሩ አዘውትሮ ትኩሳት ለታየባቸው ሰዎች ርዳታ በመስጠት ላይ ያሉት ብቸኛው ሀኪም ድሪሳ ቤርት ገልጸዋል።
የጊኒ ዜጎች ለንግዱ ብቻ ሳይሆን በማሊ የተሻለ ህክምና እንደሚያገኙ ተስፋ በማድረግም ድንበር እንደሚሻገሩ ሀኪሙ ድሪሳ ቢገልጹም፣ እርሳቸው በሚሰሩበት ማዕከል አንድ ሰው በኤቦላ ተሀዋሲ መያዙን ማረጋገጥ የሚችሉበትን ምርመራ ማካሄድ እንደማችሉ አመልክተዋል። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ብዙ ጊዜ የትኩሳቱ መንሥዔ ወባ ወይም ሌላ በሽታ ሊሆን ይችላሉ። ከአያቷ ጋር ጊኒ ቆይታ ወደ ኩሬሜላ ከተመለሰች በኋላ የሞተችው የሁለት ዓመቷ የማሊ ሕፃን ወደ ክሊኒካቸው አለመምጣቷን እና በዚህም የተነሳ በኤቦላ ተሀዋሲ መያዟ ባለመታወቋ በጊዜ ከሌላው ሕዝብ መለየት አልመቻሉን ሀኪሙ ድሪሳ ቤርት አመልክተዋል።
« ምንም እንኳን በድንበሩ አካባቢ ቁጥጥር ቢደረግም፣ የጤና ባለሙያዎች ሕፃኗ በኤቦላ ተሀዋሲ መያዟን ሳያዩ ወደ ኩርሜላ ተመልሳ ልትገባ ችላለች። »
ይኸው ሁኔታም በሕዝቦች ፣ በዕቃ እና በአገልግሎት ዝውውር ላይ ይበልጡን ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ ነው የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ተመልካች ተቋማት የጠቆሙት። ዓለም አቀፉ የገንዘብ መርህ ድርጅት፣ አይ ኤም ኤፍ ኤቦላ ለተከሰተባቸው ሶስቱ ሀገራት ካሁን ቀደም አቅርቦት የነበረውን በአማካይ በዓመት 5,5% የኤኮኖሚ ዕድገት ትንበያን አሁን ወደ 5% ዝቅ አድርጓል። ይህንኑ የአይ ኤም ኤፍ ግምት በሚጋራው የዓለም ባንክ ግምት መሠረትም፣ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር እስካልተቻለ ድረስ ኤቦላ በምዕራብ አፍሪቃ ኤኮኖሚ ላይ አአአ በ2015 ዓም 32 ቢልዮን ዩኤስ ዶላር ክስረት ያደርሳል።

Mali Guinea Ebola Grenzkontrolle Grenze
ምስል Reuters/J. Penney
Mali Ebola Kourémalé Händler Grenze Guinea
ምስል Jan-Philipp Scholz
Mali Ebola Kourémalé Gesundheitspersonal
ምስል Jan-Philipp Scholz
Mali Kourémalé Ebola
ምስል DW/J.-P. Scholz

አርያም ተክሌ/ያን ፊሊፕ ሾልስ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ