1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤቦላ ሥርጭትና ተመድ

ረቡዕ፣ መስከረም 21 2007

ግብረ-ሃይሉ በ60 ቀናት ውስጥ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት አስቧል። እንደ አንቶኒ ባንበሪ አሁን አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ ዓለም ከፍተኛ አደጋ ሊገጥመው ይችላል።

https://p.dw.com/p/1DOOl
ምስል Zoom Dosso/AFP/Getty Images

የኤቦላን ወረርሽኝ ለመግታት የተቋቋመው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ-ሃይል የተኅዋሲውን መስፋፋት በ60 ቀናት ውስጥ ለመቆጣጠር አቅዷል።ግብረ-ሃይሉ ይህን ዕቅድ ማሳካት ፈታኝ መሆኑ ግን አልጠፋውም።የግብር ሐይሉ አስተባባሪዎች በወረርሽኙ የተጠቁትን የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራትን ዛሬ ይጎበኛሉ። የግብረ-ሃይሉ መሪ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከጋና መግለጫ ሰጥተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ-ሃይል የኢቦላን ወረርሽኝን የመግታት አላማ አንግቧል። የግብረ-ሃይሉ መሪ አንቶኒ ባንበሪ ይህን አላማ ከግብ ለማድረስ የማይፈነቀል ድንጋይ የለም ይላሉ።

''ይህ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግብረ-ሃይል ስራው አንድ ብቻ ነው።ኢቦላን ማቆም -መስፋፋቱንም መግታት። ይህ አላማ ሲሳካ ይህ ግብረ-ሃይል ይዘጋል። ይህም በቅርብ ጊዜ ይሆናል። ይሁንና በዚህ ስራ ውስጥ በጋራ የምንሳተፍ ሁሉ መንግስታዊ የግብረ-ሰናይ ድርጅቶችን ጨምሮ ከፊታችን ትልቅ ስራ ተደቅኗል። ኢቦላን ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት ባለበት መግታት ይኖርብናል።''

Anthony Banbury, Vorsitzender der UNO-Sondermission UNMEER
ምስል imago/Xinhua

ግብረ-ሃይሉ ከለጋሽ ሃገሮች ባገኘው ድጋፍ ደስተኛ ነው።ይህ የገንዘብ ድጋፍ በወረርሽኙ ለተጠቁ ሃገሮች የሚደረገውን የሰብዓዊ እርዳታ ሊያግዘው እንደሚገባ አንቶኒ ባንበሪ ይናገራሉ። ግብረ-ሃይሉ በ60 ቀናት ውስጥ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት አስቧል። እንደ አንቶኒ ባንበሪ አሁን አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ ለም ከፍተኛ አደጋ ሊገጥመው ይችላል።

''ለም ጤና ድርጅት የህክምና ባለሙያዎች የተኅዋሲውን መስፋፋት ለመግታት ሊደረግ ይገባል ብለው ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት የ3060 እና 90 ቀናት እቅድ አስቀምጠናል።በ60 ቀናት እቅዳችንን ለማሳካት መደረግ ያለበትን ሁሉ እናደርጋለን። እቅዱ የተለጠጠ ነው።''

ጋና የግብረ-ሃይሉ መቀመጫ ከመሆኗ ባሻገር ለዕቅዱ መሳካት ድጋፍ እያደረገች ነው። የጋና ኮምዩንኬሽን ሚኒስትር ዶ/ር ኦማን ቦማህ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢቦላን መስፋፋት ለመግታት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ-ሃይል ሃገራቸው ተጠቃሚ እንደምትሆንም ይናገራሉ።

'ግብረ-ሃይሉ አላማውን በማሳካት ጋናን ጨምሮ በመላው ዓለም ላይ የተጋረጠውን አደጋ ማስወገድ ከቻለ ያ ጥቅም ነው። ግብረ-ሃይሉ አላማውን ማሳካት ከተሳነው ደግሞ ችግሩ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ ለም ለአደጋ ይጋለጣል።''

አንቶኒ ባንበሪ የኢቦላ ወረርሽኝን ለመግታት የሚታገሉ ሃገሮች የሚጎበኘውን አነስተኛ ቡድን ይመራሉ። ቡድኑ በሃገራቱ በአስቸኳይ የሚያስፈልጉ እገዛዎችንም ይለያል። ጋናውያን ግን የግብረ -ሃይሉ ሰራተኞች ተሕዋሲዉን ይዘዉ ወደ ጋና እንዳመጡ ሰግተዋል።

''በጋና የኢቦላ ወረርሽኝ ሳይከሰት የግብረ-ሃይሉን ዋና ጽህፈት ቤት በዚህ ማድረግ ለምን አስፈለገ?ምን ማለት ነው?ወደዚህ የመጡት ኢቦላን ሊያመጡልን ነው?የእነሱ በዚህ መገኘት ለእኛ ስጋት ነው።''

Ebola in Sierra Leone Gemeinsam gegen das Virus Bildergalerie
ምስል DW/Scholz/Kriesch

''የመጡት የኢቦላ ወረርሽኝ ከተከሰተባቸው የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት አይደለም ።እናም ጋናውያን ምንም አይነት ፍርሃት ሊሰማን አይገባንም ብዬ አምናለሁ።''

አንቶኒ ባንበሪ ጋናውያን ምንም ስጋት አይገባቸውም ባይ ናቸው።እኔም ሆነ የግብረ-ሃይሉ ቁጥር አንድ ሃላፊነት የሰራተኞቻችንን ጤንነት በመጠበቅ በኢቦላ እንዳይያዙ ማድረግ ነው። የአለም ጤና ድርጅት የዚህ ተልዕኮ አንድ አካል በመሆን ለግብረ-ሃይሉ ሰራተኞች ጥብቅ የስራና የጉዞ መመሪያዎች እና ልናደርግ የሚገባንን ጥንቃቄዎች አዘጋጅቷል።''

ዓለም አቀፉ ድርጅት ጋናውያን የግብረ-ሃይሉን አላማ ተረድተው ለስኬታማነቱ እገዛ ያደርጋሉ የሚል ተስፋ አድሮበታል።

አይዛክ ካሌድዚ

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ