1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤቦላና ማርቡርግ ተሐዋሲያን ስጋት

ማክሰኞ፣ መስከረም 27 2007

አፍሪቃ ዉስጥ በስተምዕራብ በሚገኙ አራት እና አምስት ሃገራት ቀስ በቀስ የተስፋፋዉ ኤቦላ ወደአዉሮጳም እንዳይዛመት ስጋቱ አሁንም አለ። ዓለም ከገዳዩ የኤቦላ ተሐዋሲ ጋ የተያያዘዉን ፍልሚያ ገና በድል ሳያጠናቅቅ እሱን መሰል ማርቡርግ የተሰኘ አደገኛ ተሐዋሲ ዩጋንዳ ዉስጥ መታየቱ ተሰምቷል።

https://p.dw.com/p/1DRmL
Ebola 30.09.2014 Schutzanzüge Gebet
ምስል Reuters/Christopher Black/WHO

ባለፈዉ ዓመት የካቲት ወር ገደማ ገና የኤቦላ ተሐዋሲ ጊኒ ዉስጥ ሲከሰት በገጠራማ አካባቢዎች እጅግም ጥንቃቄ ሳይደረግ በርካቶችን እንደዋዛ ሲለክፍና ሊፈጅ ሰነበተ። የበሽታዉ ምንነት ከታወቀ በኋላም ባጠቃላይ በሀገሪቱ 1,157 ሰዎች በተሐዋሲዉ መያዛቸዉን 710 ደግሞ መሞታቸዉን የዓለም የጤና ድርጅት መዝግቧል። ከጊኒ ቀጥላ በኤቦላ የተጎዳችዉ ሀገር ላይቤሪያ ናት። በዚህች ሀገር ኤቦላ 1,998 ሰዎችን ሲገድል 3,696 ደግሞ በተሐዋሲዉ ተይዘዋል። ሴራሊዮን ዉስጥ ደግሞ ኤቦላ 622 ሰዎች መግደሉ 2,304 ደግሞ በበሽታዉ መያዛቸዉ ተመዝግቧል። ኤቦላ ዘግየት ብሎ የተዛመተባት ናይጀሪያ 20 ሰዎች በተሐዋሲዉ መያዛቸዉ ተመዝግቧል፤ ስምንቱ ሞተዋል። ሴኔጋል ዉስጥ በኤቦላ መያዙ የተረጋገጠዉ የጊኒ ዜጋ የሆነ ተማሪ ሲሆን ከህመሙ እያገገመ ነዉ ተብሏል። ሴኔጋል ከኤቦላ ነፃ ናት ሊባል የሚቻለዉ ግን በ42ቀናት ዉስጥ ሌላ ተጨማሪ ታማሚ ካልተገኘ ነዉ። ይህ ወጣት በኤቦላ መያዙ የተሰማዉ ባለፈዉ ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ ነበር።

Symbolbild - Ebola Virus
የኤቦላ ተሐዋሲምስል picture-alliance/dpa

ስፔን ዉስጥ በኤቦላ ተሐዋሲ መያዛቸዉ ከሁለት ጊዜ የደም ምርመራ በኋላ የተረጋገጠዉ ነርስ በሽታዉ የተጋባባቸዉ ሴራሊዮን ዉስጥ በህክምና እርዳታ ተግባር ተሰማርተዉ የነበሩ ሌላ የሀገሪቱን ዜጋ ሲያስታምሙ መሆኑን ነዉ ዘገባዎች የሚያመለክቱት። ቀደም ብለዉ በኤቦላ ተሐዋሲ የተያዙት ማኑዌል ጋሪቺያ ቪቾ ከሴራሊዮን ወደማድሪድ ቢወሰዱም ህይወታቸዉ አልተረፈም። ከሁለት ሳምንታት በፊት ኤቦላ ገደላቸዉ። ሁኔታዉ ያሰጋዉ የስፔን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስቸኳይ የቀዉስ መከላከል ስብሰባ ጀምሯል። ዜናዉም በምዕራብ አፍሪቃ በጊኒ፣ ላይቤሪያ እና ሴራሊዮን ተገድቧል ተብሎ የተገመተዉ የኤቦላ ተሐዋሲ ባህር ተሻግሮ የሌሎችም ስጋት መሆኑን አመላክቷል።

ዩናይትድ ስቴትስ የኤቦላ ተሐዋሲ ወደምድሯ እንዳይገባ በግዛቷም ሆነ በአፍሪቃ ሃገራት አዉሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ተጓዦች ከበሽታዉ ነፃ መሆናቸዉን የማጣራት ርምጃዎች እንዲጠናከሩ የበኩሌን አደርጋለሁ ብላለች። ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ አብዛኞቹ ሃገራት ጠንካራ ርምጃ አለመዉሰዳቸዉን በመጠቆም፤ የኤቦላ መዛመት ለመግታት ዓለም ዓቀፍ ጥረት እንዲኖር ጥሪ አድርገዋል።

ቀደም ሲል አንድ የላይቤሪያ ዜጋ ሀገሩ ቆይቶ በኤቦላ ተሐዋሲ እንደተያዘ ወደአሜሪካዋ ዳላስ ከተማ ይመለሳል። ህመሙ ሲጠናም ሃኪም ቤት ሄዶ ይመረመርና በሽታዉ ይታወቃል። ቴክሳስ ዉስጥ በሚገኝ አንድ ሃኪም ቤት ምርመራ ያደረገችለት ነርስ ምንም እንኳን ታማሚዉ ቶማስ ዱንካን ከላይቤሪያ መመለሱን ቢነግራትም የበሽታዉ ምንነት ሳይጣራ ወደቤቱ እንዲመለስ አድርጋዉ ነበር። ትልቁ የሀገሪቱ ብሄራዊ የነርሶች ማኅበር ባለፈዉ ሳምንት እንዳስታወቀዉ አብዛኞቹ ነርሶች በዚህ ተሐዋሲ የተያዘን ለማከምም ሆነ የበሽታዉን ምልክቶች ለመረዳት የሚያስችል በቂ ስልጠና እንደሌላቸዉ ግልፅ አድርጓል። በተለያዩ የሀገሪቱ ግዛቶች ከሚገኙ ነርሶች አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት የሚሠሩበት ሃኪም ቤት በቂ የፊት መከለያ ጭምብልና ፈሳሽ ወደአካላቸዉ እንዳይደርስ ሊያደርግ የሚችል የህክምና ትጥቅ እንደሌለዉ ማመልከታቸዉም ተገልጿል። ለዚህም ነዉ ፕሬዝደንት ኦባማ የሀገሪቱ የጤና ባለሙያዎች የኤቦላ ተሐዋሲን የመለየት ተገቢ ስልጠና እንዲያገኙ፤ በሀገሪቱ የአዉሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎችም ተገቢዉ የጥንቃቄ ፍተሻ እንዲደረግ መመሪያ ያስተላለፉት። ከላይቤሪያ ተሐዋሲዉን ወደአሜሪካ ያሻገረዉ ግለሰብም ለሙከራ በተቀመመዉ የኤቦላ መድሃኒት ይታከማል ተብሏል።

Ebola Westafrika I.S.A.R. GERMANY Liberia
ምስል I.S.A.R. GERMANY

በኤቦላ ተሐዋሲ የተያዙ የህክምና እርዳታ ሠራተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መሄዱም እየታየ ነዉ። በቅርቡ ሴራሊዮን ዉስጥ ለተመሳሳይ ተግባር የተሠማራ አንድ የኖርዌይ ዜጋ በኤቦላ በመያዙ ለህክምና ወደሀገሩ ዛሬ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል። ሌላዉ ሴኔጋላዊ የድንበር የለሽ ሃኪሞች ባልደረባ ጀርመን ዉስጥ ህክምና እየተደረገለት ነዉ። አንድ ፈረንሳዊ የቡድኑ አባልም ወደሀገሩ ተወስዷል።

Marburg Virus
የማርቡርግ ተሐዋሲምስል picture alliance/dpa/CDC

ኤቦላ ከምዕራብ አፍሪቃ እና ወትሮ ከሚከሰትባቸዉ የአፍሪቃ ሃገራት ዉጭ በአዉሮጳና ዩናይትድ ስቴትስ መገኘቱ ያስከተለዉ ስጋት መፍትሄ ሳያገኝ፤ ከሳምንት በፊት ዩጋንዳ ዉስጥ የተከሰተዉ ተመሳሳይ ተሐዋሲ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል። የ30 ዓመቱ በካምፓላ ሜንጎ በተባለዉ ሃኪም ቤት የራጅ ባለሙያ በማርቡርግ ተሐዋሲ ባለፈዉ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነዉ ህይወቱን ያጣዉ። የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ከታማሚዉ ጋ በቅርብ ግንኙነት የነበራቸዉ አስራ ስምንት ሰዎች ለጊዜዉ ተገልለዉ ክትትል እንዲደረግላቸዉ አድርገዋል። ማርቡርግ የተሰኘዉ ተሐዋሲ ልክ እንደኤቦላ፤ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ማስመለስ እና ማስቀመጥ እንዲሁም ከባድ የደም መፍሰስን ያስከትላል። ማርቡርግም እንደኤቦላ ከሰዉነት በሚወጣ ማንኛዉም ፈሳሽ አማክኝነት ነዉ የሚተላለፈዉ። የገዳይነት ደረጃዉም ከ24 እስከ 88 በመቶ ከፍና ዝቅ እንደሚል ነዉ የተገለጸዉ።

የዩጋንዳ የጤና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጄን አሴንግ ለጀርመን የዜና ወኪል እንደገለጹት አሁን ህዝቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መመሪያ ተላልፏል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለዉ በአምስቱ የአፍሪቃ ሃገራት በኤቦላ የተያዘዉ ቁጥር 7,178 ደርሷል፤ 3,338ቱን ደግሞ መግደሏ ተረጋግጧል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ