1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ-እሥራኤላውያን እስር በእስራኤል

ማንተጋፍቶት ስለሺረቡዕ፣ ሰኔ 17 2007

ባለፈው ሰኞ ቴል አቪቭ ውስጥ ፖሊስ 15 የሚጠጉ የተቃውሞ ሰልፈኞችን መጥፎ ባህርይ በማሳየት በሚል በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጧል። ዓርብ ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ያስተላለፈው ውሳኔ ታምቆ የነበረው የኢትዮጵያ አይሁዳውያን ብሶት ዳግም እንዲፈነዳ እና ወደ ግጭት እንዲያመራ ሰበብ መሆኑን ተጠቅሷል።

https://p.dw.com/p/1FmvA
Israel Festnahmen bei Demonstration äthiopischstämmiger Israelis
ምስል Reuters/B. Ratner

[No title]

የኢትዮጵያውያን ይሁዲዎች ባለፉት ሰባት እና ስምንት ሳምንታት ውስጥ በእስራኤል የተለያዩ ከተሞች ውስጥ ከአምስት በላይ የተቃውሞ ሰልፎችን አኪያሂደዋል። የሰላማዊ ሰልፎቹ መንስዔ ዘርፈ-ብዙ ቢሆኑም ውጥረቱ አይሎ ወደ ጡዘት ያመራው ግን አንድ የኢትዮጵያ አይሁድ ወታደር በፖሊሶች ሲያዝ እና በአንደኛው በደል ሲደርስበት የሚሳየው ቪዲዮ በማኅበራዊ መገናኛ ዘርፎች ከተሰራጨ በኋላ ነው።

በተለይ ባለፈው ሰኞ የእስራኤል የንግድ ማዕከል በሆነችው የቴል አቪቭ ከተማ የኢትዮጵያ አይሁዳውያን ከፖሊሶች ጋር ዳግም ተጋጭተው ቁጥራቸው ወደ 15 የሚጠጉ ሰልፈኞች በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።

«ጠበቃ» የተሰኘው በእስራኤል ለኢትዮጵያውያን ቤተ እስራኤላውያን መብትና እኩልነት የሚሰራው ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈንታሁን አሠፋ ዳዊት የታሰሩት ሰላማዊ ሰልፈኞች ቁጥራቸው 25 እንደነበር፤ ሆኖም ከሁለቱ በስተቀር ሌሎቹ መፈታታቸውን ዛሬ ተናግረዋል።

የእስራኤል ፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት ሚኪ ሮዘንፌል «ሰልፈኞቹ መጥፎ ባህርይ በማሳየታቸው ፖሊስ 15ቱን በቁጥጥር ስር አውሏል» ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

Israel Festnahmen bei Demonstration äthiopischstämmiger Israelis
ምስል Reuters/B. Ratner

በፖሊስ ታስረው የነበሩት ሠልፈኞች እስራኤል ውስጥ የሚደርስብንን በደል በዝምታ ማሳለፍ አንፈልግም፣ «ሀገሪቱ ጨቋኝ ናት» በማለት በተደጋጋሚ ሰልፎችን ያስተባብሩ የነበሩ ሰዎች እንደነበሩ አቶ ፈንታሁን ገልጠዋል። ታሳሪዎቹ በአብዛኛው ወጣቶች ሲሆኑ፤ ሴቶችም ወንዶችም ይገኙበት እንደነበር ተሰቅሷል።

ዓርብ ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ያስተላለፈው ውሳኔ ታምቆ የነበረው የኢትዮጵያ አይሁዳውያን ብሶት ዳግም እንዲፈነዳ እና ወደ ግጭት እንዲያመራ ሰበብ መሆኑን ተጠቅሷል። ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የኢትዮጵያ አይሁድ ወታደርን በመደብደብ የተከሰሰው ፖሊስ በወንጀል እንደማይጠየቅ ዓርብ ዕለት ይፋ ማድረጉ ብዙዎችን እንዳስቆጣ አቶ ፈንታሁን ተናግረዋል።

ካሁን በፊት የተደረጉ ሠላማዊ ሰልፎች ምንም አይነት መፍትኄ አለማስገኘታቸውም ለግጭቱ ሌላኛው መንስዔ ነው ሲሉ አቶ ፈንታሁን አሠፋ ዳዊት አክለዋል። ሆኖም ዛሬ ከሰአት በኋላ ከጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ጋር ተነጋግረው በውሳኔው ላይ እንደተወያዩ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያውያን ቤተ እሥራኤላውያን ወደ እስራኤል ከመጡበት ጊዜ አንስቶ የጠጠበቁትን እንዳላገኙ ይነገራል። ከብዙኃኑ ኅብረተሰብ ጋር የመቀላቀሉ ሁኔታ መራዘሙ፣ ብሎም ወጣቶች ለሥራ አጥነት እና ለዘረኝነት ጥቃት መጋለጣቸው ውጥረቱን እንዳባባሰው ይጠቀሳል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ

Israel Tel Aviv Protestaktion äthiopische Juden Ausschreitungen
ምስል Reuters/Baz Ratner