1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲያተኩር ተጠየቀ 

ሰኞ፣ ጥር 27 2011

በኢትዮጵያ የተጀመረውን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት የመንግሥት አመራሮችም ሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ከብሔር ተኮር አጀንዳዎች ይልቅ ብሔራዊ መግባባትን በሚፈጥሩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ተገለጸ። ይህ የተነገረዉ በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ ላይ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3Cgjs
Deutschland Treffen der äthiopischen Diaspora in Frankfurt am Main
ምስል DW/E. Fekade

ከጀርመን ዩኒቨርሲቲዎች በተጋበዙ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል

በኢትዮጵያ የተጀመረውን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት የመንግሥት አመራሮችም ሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ከብሔር ተኮር አጀንዳዎች ይልቅ ብሔራዊ መግባባትን በሚፈጥሩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ተገለጸ። በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ ባለፈው ቅዳሜ በፍራንክፈርት ከተማ ባዘጋጀው ሕዝባዊ ሥብሰባ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጥናት ያቀረቡ ከጀርመን ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ ኢትዮጵያውያን የአካዳሚክስ ምሁራን ለውጡ እውን ሊሆን የሚችለው ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ያለልዩነት በተለይም ወጣቱን አካታች የሆኑ ከድህነት አረንቋ የሚያላቅቁት ፖሊሲዎች ተቀርጸው ተግባራዊ ሲሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል። በሌሎች አገራት ተሞክረው ስኬታማ የሆኑት የፍትሕ የእውነት እና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽኖች በኢትዮጵያም ገቢራዊ እንዲሆኑ የጠየቀው ሕዝባዊ ጉባኤው የሕዳሴው ግድብ የሕልውና መሰረት የሆነውና 60 በመቶ ያህል የአባይ ወንዝ ውሃ ምንጭ እንደሆነ የሚታመነው የጣና ኃይቅ የተፈጥሮ ምህዳር እምቦጭ በተባለ አረም የመጠቃቱ ጉዳይ በማዕከላዊ መንግሥት ብሔራዊ አጀንዳ ሆኖ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈለግለትም ጠይቋል። 
በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይት እና ትብብር መድረክ ባለፈው ቅዳሜ ያዘጋጀው የፍራንክፈርቱ ሕዝባዊ ሥብሰባ ትኩረት ካደረገባቸው ዓበይት ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያ የሚካሄደው አገራዊ ለውጥ እና ተግዳሮቶቹ የብሔር ተኮር ፖለቲካ ተስፋ እና ስጋቶች የፍትህ እውነት እና ዕርቅ አስፈላጊነት ለብሔራዊ መግባባት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ከጀርመን ዩኒቨርሲቲዎች
በተጋበዙ ኢትዮጵያውያን የዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች እንዲሁም በተፊፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች አማካኝነት የቀረቡ ጥናቶች ይገኙበታል። የትብብር መድረኩ ዋና ጸሃፊ አቶ ጥበቡ ኃይሉ እንዲህ ዓይነቱ ሕዝባዊ ውይይት የዲያስፖራው ማህበረሰብ አገራዊ ለውጡን ለማጠናከር የድርሻውን እንዲወጣ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ሲሉ ገልጸውልናል ።
ቀድሞ በአዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩት እና በአሁኑ ወቅት በዶቸ ባንክ የአፍሪቃ አማካሪ እንዲሁም በየና ዩኒቨርሲቲ ኢኒስቲውትሽናል ኢኮኖሚክስ በፒ.ኤችዲ ፕሮግራም ትምህርታቸውን የሚከታተሉት አቶ መስፍን ሙሉጌታ በውይይቱ  ላይ ባቀረቡት ጥናት በኢትዮጵያ አገራዊ ለውጡ በጥቂት ግለሰቦች እና ቡድኖች ጥረት ብቻ የመጣ ሳይሆን መላው የአገሪቱ ዜጎች ለዓመታት በከፈሉት የሕይወት መስዋዕትነት የተገኘ ድል መሆኑን በማስታወስ ለውጡን ዘላቂ ለማድረግ እና ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖረው ለማስቻል ሁሉንም ሕዝብ ያለልዩነት  እንዲሁም በአገሪቱ 95 በመቶ ያህል ከድህነት ወለል በታች የሚገኙትን አካል ጉዳተኞች ጭምር አካታች የሆኑ ኑሮዋቸውን የሚለውጡ  እና ከጉስቁልና የሚያላቅቋቸው ፖሊሲዎች ሊቀረጹ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በቅርቡ ኢትዮጵያ ደርሰው የተመለሱት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ በምህጻሩ ኢ ሓፓ ከፍተኛ አመራር እና የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ የአውሮፓ ሃላፊ አቶ ጀሚል መሐመድም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ተስፋ እና ስጋቱን በተመለከተ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል ። ከቀጣዩ ብሔራዊ ምርጫ በፊት አስተማማኝ ሰላም እና መረጋጋት በአገሪቱ መስፈን ይኖርበታል የሚል እምነት እንዳላቸው በመግለጽ አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ዲያስፖራው የበኩሉን እገዛ እንዲያበረክትም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ቋንቋ እና ጎሳን መሰረት ያደረገ የብሔር ፖለቲካ ለማንም የማይጠቅም የዓለማችን ሥጋት መሆኑም በጥናት አቅራቢዎቹ በስፋትየተወሳ ጉዳይ ነበር ።በዘር እና የመደብ ጭቆና ሽፋን ወደ ስልጣን የሚመጡ የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝ ቡድኖች እና ግለሰቦች በስልጣን ዘመናቸው ሰብአዊ መብት ሲጥሱ እና ሌብነት ሲፈጽሙ ቆይተው በሕዝባዊ አመጽ ከአመራርነት ሲወገዱ ብሔራቸው ጉያ በመደበቅ ከፍርድ እና ተጠያቂነት ለማምለጥ የሚሞክሩበት ሕግ አልባ የመጨቆኛ መሳሪያ አድርገውታል የሚል ትችትም በውይይቱ ላይ ተሰንዝሯል። በተጨማሪም እውነተኛ አገራዊ ለውጥ ከታሰበ ብሎም የትራንስፎርሜሽን እና የልማት ዕቅዱን ስኬት ለማፋጠን ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ሲሰራበት የቆየው በመንግሥት የአመራር ሚና የሥልጣን ድልድል በብሄር ኮታ ተዋጽዖ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ መስፈርቱ ዕውቀት ብቃት እና ችሎታን ያማከለ ሊሆን እንደሚገባም ተመልክቷል። በጎተ ዩኒቨርሲቲ አንግሎፎን አርት ባህል እና ሚድያ ጥናት ተቋም የድህረ ምረቃ ተማሪ የሆነው ወጣት ሳሙኤል ፍቅረስላሴም በዩጎዝላቪያን ሩዋንዳን ደቡብ አፍሪካ እና በሌሎችም አገራት የተከሰቱ ብሄር ተኮር የፖለቲካ ግጭቶች ያስከተሉትን  መጠነሰፊ ጉዳት በማብራራት አገራቱ ደም አፋሳሹን ግጭት በሰላም ለማብቃት በደል የደረሰባቸው ሰዎች የሕሊና ፈውስ እንዲያገኙ ብሎም የመጣው ለውጥ ሕዝባዊ ድጋፍ ኖሮት እንዲቀጥል መሰረት ለማስያዝ የተከተሏቸው የሕግ የእውነት እና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽኖች ሚና ለኢትዮጵያም እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ያስረዳል።
አቶ አንቅሳዊ ምስጋና በጎተ ዩኒቨርሲቲ በፍልሥፍና የትምህርት ዘርፍ  የማስተርስ ፕሮግራም ተማሪ ናቸው ። የግሪኩ "ኤቶስ" ወይም "ብሄር" የሚለው ቃል አፈጣጠሩ አሁን ፖለቲከኞች ቋንቋ እና የዘር ሃረግን መሰረት አድርገው እንደሚጠቀሙበት ሌሎችን የማህበረሰብ ክፍሎች አግላይ የሆነ እሳቤ ላይ ተመስርቶ ሳይሆን የግለሰቦችን ባህሪ እና የአንድ የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን የአኗኗር ዘይቤ ለመግለጽ እንደነበር በጥናታቸው በማስታወስ ለብዙ ሺህ ዘመናት አንዱ ከሌላው ጋር ተጋብቶ እና ተዋልዶን የኖረ ማህበረሰብ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የዚህ እና የዚያ ብሄር እያሉ የጥፋት ነጋሪትን መጎሰም ከዘመኑ ጋር የማይሄድ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ነው ብለዋል።
 ሌላው የፍራንክፈርቱ ሕዝባዊ ውይይት የትኩረት አጀንዳ በእምቦጭ አረም የተወረረውን የጣና ኃይቅ ብዝኃ ሕይወት እንዲሁም የቅዱስ ላሊበላ ወቅር አብያተ ክርስትያናትን ከጥፋት ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ በውጭ የሚኖሩ በተለይም በጀርመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ሚና የተመለከተ ጉዳይ ነበር።  60 በመቶ ያህል የአባይ ውሃ መገኛ መሆኑ የሚታወቀው የጣና ሃይቅ አገሪቱን ወደላቀ ልማት እና እድገት ያሸጋግራታል ተብሎ ተስፋ ለተጣለበት የህዳሴው ግድብ ዕውን መሆንም ትልቅ ሚና እንዳለውም ይታመናል ። ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ የሆኑ ደስቶች እና ከ 13ተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተቆረቆሩ ጥንታዊ ገዳማትን ጨምሮ በውስጡ በያዘው ሰፊ ሥነ ምህዳራዊ ሃብት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው አገራት ጭምር የተፈጥሮ ጸጋ እና በረከት የሆነው የጣና ኃይቅ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ እምቦጭ በተባለ አረም የመወረሩ ጉዳይ ዜጎችን በእጅጉ አሳስቧል። በሃይቁ ውስጥ በሚገኙት እንደ ዘጌ ባሉ የቱሪስት መስህብ ደሴቶች ለአደጋ የተጋለጡትን ጥንታውያኑ ክብራን ኪዳነምህረት እና አባ እንጦንስ ገዳም ሌሎችንም ታሪካዊ መስህቦች ለመታደግ ሁሉም ወገን እንዲረባረብም ጥሪ ቀርቧል።
የሃረሩ ሃረማያ ሃይቅ ጥናት እና ምርምር በሚል ቢሮክራሲ ውሃው እንደደረቀ ያስታወሱት የውይይቱ ተካፋዮች ጣናን ጭምሮ በደቡብ ዝዋይ ሃይቅ እና በሌሎችም የአገሪቱ የውሃ አካሎች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶችን ለመከላከል በፌደራል መንግሥት ደረጃ ብሔራዊ አጀንዳ ሆኖ ዘላቂነት ያለው ሰፊ ዘመቻ እንዲደረግ ጠይቀዋል። በፍራንክፈርት የተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴም እስካሁን ሃይቁን ለመታደግ አሜሪካ በተቋቋመው " በዓለማቀፍ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማህበር ግበረ ኃይል " አስተባባሪነት
ኢትዮጵያውያን ከ 150 ሺህ ዶላር በላይ በማዋጣት ሁለት ከፍተኛ ጉልበት ያላቸው የማጨጃ ማሽኖች መላካቸውን አስታውሶ ከትብብር መድረኩ ጋር በመቀናጀት በቀጣይ ጣናንም ሆነ እንደ ቅዱስ ላሊበላ ያሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና የተቸራቸው ታሪካዊ ቅርሶቻችንን ከጥፋት ለመታደግ ሕዝቡን በማስተባበር የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያበረክትም ይፋ አድርጓል።
ዲያስፖራው በአገር ልማት እና ግንባታ የበኩሉን ድጋፍ ለማበርከት የተግባር እንቅስቃሴ መጀመሩም በሕዝባዊ ውይይቱ ላይ ተውስቷል። በቀጣዮቹ ወራት ራሳቸውን ጠቅመው ለበርካታ የአገሪቱ ዜጎች የስራ እድልን የሚፈጥሩ ልማቶችን ለመጀመር እንዲሁም ለተማሪዎች የሚጠቅሙ ልዩልዩ የማስተማሪ መጽሃፍቶችን አሰባስበው አገርቤት ለመላክ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ያበሰሩት የትብብር መድረኩ አባላት ሌሎችም ወገኖች የእነሱን አርአያ እንዲከተሉ ጥሪ አስተላልፈዋል። በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይት እና ትብብር መድረክ ባዘጋጀው የፍራንክፈርቱ ሕዝባዊ ሥብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ ዲያስፖራው በኢትዮጵያ ማህበራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎውን እንዲያጎለብትተና አገሪቱ የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ለመቅረፍ በውጭ የሚኖረው ማህበረሰብ በቀን አንድ ዶላር ለአገሩ እንዲለግስ ላቀረቡትን ተደጋጋሚ ጥሪ ተገቢውን ምላሽ መስጠት በሚቻልበት ስልትም ላይ መክሯል። በዓለም ዙሪያ ከ 3ሚልዮን የሚልቁ በጀርመን ደግሞ ከ 20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውን መኖራቸውን ያስታወሰብ ይኸው ጉባኤ የገንዘብ መዋጮውን ለማሰባሰብ በተቋቋመው የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ እስካሁን አምስት ሺህ ያህል ሰዎች ብቻ ለጥሪው ምላሽ መስጠታቸው በቂ አለሞኑን በመገንዘብ የሕብረተሰባችንን ሕይወት ለመለወጥ እና ለአገር ግንባታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተጠናከረ ድጋፍ በማድረግ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቋል።

Deutschland Treffen der äthiopischen Diaspora in Frankfurt am Main
ምስል DW/E. Fekade

እንዳልካቸው ፈቃደ

ኂሩት መለሰ