1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

Merga Yonas Bula
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 4 2010

የኢትዮጵያ መንግሥትን በመቃወም ዩኒቨርስቲዎችን ጨምሮ በተለያዩ የትምሕርት ተቋማት፤ ከተሞች እና አካባቢዎች የሚደረገዉ ሠልፍ፤ አመፅ እና ስብሰባ  እንደቀጠለ ነዉ። የፀጥታ አስከባሪዎችም በተቃዋሚዎች ላይ በሚወስዱት የኃይል ርምጃ ሰዎች እየሞቱ፤ እየቆሰሉ እና እየታሰሩ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

https://p.dw.com/p/2pKB3
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Deutsch

Political crisis lead to SM blockade - MP3-Stereo

ተቃዉሞዉን ለመቆጣጠር መንግስት ከትላንት ጀምሮ ፌስቡክና ትዊተር የመሳሰሉትን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መዘጋቱም እየተዘገበ ነዉ።

በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግርያ ክልሎች የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ዉስጥ በተማሪዎች መካከል የተፈጠሩ ግጭቶች  ለብዙዎቹ ሕይወት ማለፍ ምክንያት መሆኑን የዓይን እማኞች ገልጸውልናል። በኦሮሚያ ክልል በመቱ፣ በኋላ፣ በአምቦና በጅማ ዩኒቨርሲቲዎች፥ በአማራ ክልል በወልድያ፣ በደብረማርቆስና ጎንደር ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም በትግራይ ክልል አዲግራትና አክሱም ዩኒቨርስቲዎች ግጭት የታየባቸው ናቸው።

እንደ ዓይን እማኞቹ፣ ከዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ ዉጭም መንገድ ላይ የሚደረጉ ተቃዉሞች ቀጥለዋል። በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሃረርጌ ከጨለንቆ ወጣ ብሎ በሚገኝ ሥፍራ፤ ታጣቂዎች ቢያንስ አንድ ሰዉ በመግደላቸዉ ሰበብ ተቃውሞውን ለማሰማት በወጣው ሰልፈኛ እና ሰልፈኛዉን ለመበተን በሞከረው የፌደራል ጦር ሠራዊት መካከል በተፈጠረ ግጭት ከአስር በላይ ሰልፈኞች ተገድለዋል።

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ ቀዉስን ለመቆጣጠር  ከትላንት ጀምሮ ፌስቡክና ትዊቴር የመሳሰሉት የማህበራዊ ሚዲያ አዉታሮች ዘግተዋል ሲሉ ተጠቃሚዎች ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ማህበራዊ ሚዲያ አዉታሮች መዘጋታቸዉ እዉነት ነዉ ይላሉ። ግን የvirtual private network /VPN/ በመጠቀም በPsiphon መተግበሪያዎችን /አፕሊኬሼኖች/ እንድሁም UC የተሰኘዉን ብራዉዘር በመጠቀም መረጃ እየተለዋወጡ መሆናቸዉን አክሎበታል።

ሁለቱም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የማህበራዊ ሚዲያ አዉታሮች መዘጋቱ አገሪቱ ያጋጠማትን የፖለቲካ ቀዉስ ለማብረድ የተወሰደ ርምጃ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ከብዙዎች መስማታቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ ይህ ርምጃ «ለረጅም ጊዜ የተቋጠረ ህዝብን ያለማዳመጥ ችግር ዉጤት ነዉ» የሚለዉ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ የማህበራዊ ሚዲያ አዉታሮችን መዝጋትና ተመሳሳይ ርምጃዎችን መዉሰድ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም፣ በአንጻሩ አገሪቱን የከፋ ችግር  ዉስጥ ይከታታል ሲል ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

ተቀዉሞዉ፣ እስራቱና ግድያዉ መቀጠሉን የሚያመለክቱ መረጃዎ እየደረሱን ይገኛሉ። ለምሳሌ ዛሬም በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ዉርጌሳ በተባለ  አካባቢ የፀጥታ አስከባሪዎች በወሰዱት ርምጃ የሰዉ ህወት ማለፉንም በዋትስአብ ቁጥራችን የተላከልን መረጃ ያመለክታል። በተመሳሳይም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ እንድሁም በምዕራብና በምስራቅ ሃራርጌ ዞኖች የመንገድ ላይ ተቃዉሞ መቀጠሉም ለመረዳት ተችለዋል።

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ