1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ቀዉስ፣የሱዳንና የምዕራባዉያን ወዳጅነት

ሰኞ፣ ነሐሴ 24 2013

ከካርቱም እስከ ኮርዶፋን፣ ከዳርፉር እስከ ብሉ ናይል ያሉ የሱዳን ፖለቲከኞች ልዩነታቸዉን ለማጥበብ ይደራደራሉ።ኢትዮጵያዉያን ፖለቲከኞች ባንፃሩ ምክንያቱ ምንም ሆነ ማን አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለማጥፋት ተከታዮቻቸዉን ያዋጋሉ።ሕዝብ ያስፈጃሉ፣ያሰድዱ ያፈናቅላሉ፣ የደሐ ጥሪት ያወድማሉ።

https://p.dw.com/p/3zhDW
Afrikanische Union Gipfeltreffen
ምስል Manasse Wondamu Haalu/AA/picture alliance

ሱዳን ለምዕራባዉያን እንደ አማራጭ እየታየች ይሆን?

የኢትዮጵያ የጎሳና የፖለቲካ ግጭት-ጦርነት ሲግም፣ ከግድብ ግንባታ እስከ ግዛት ይገባኛል የሚደርሰዉ የኢትዮጵያና የሱዳን ዉዝግብ እየናረ-ግጭትም እያስከተለ ነዉ።የኢትዮጵያና የምዕራባዉያን ወዳጅነት ሲሻክር የሱዳንና የእስራኤል፣የሱዳንና የዓረቦች፣ከሁሉም በላይ የሱዳንና የምዕራቦች ወዳጅነት እየደራ፣እየተጠናከረ፣ እየደረጀም ነዉ።የኢትዮጵያ መዳከም ለሱዳን መጠናከር ሰበብ ይሆን-ይሆን? 
የሱዳን የጦር-እና የሲቢል ፖለቲከኞችን የቀየጠዉ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ከተመሰረተ ባለፈዉ ሳምንት ሁለተኛ ዓመቱን ደፈነ።ዛሬ በተለይ በምዕራባዉያን ዘንድ እንደ የሠላም-መሠረት፣የፍትሕ ጥንስስ የዴሞክራሲ ሽግግር አብነት የሚቆጠረዉ ምክር ቤት የተቋቋመዉ ከኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ እስከ ዕዉቁ ዲፕሎማት ማሕሙድ ዲሪር ባደረጉት ጥረት ጭምር ነዉ።ትናንት በርግጥ ዛሬ አይደለም።
የዚያኑ ያክል ምናልባት ታሪክ ራሱን ይደገማል እንዲባል ሆኖ የዓመታት ሒደት ያሻገተዉን እዉነት ለመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ከፋሺት ኢጣሊያ ነፃ ለመዉጣት ባደረጉት ትግል፣ የተሰደዱ ንጉሰ ነገስቷ አርበኞችን ያደራጁ፣ያስተባበሩ፣ የብሪታንያዎችን ድጋፍና ርዳታ ያገኙትም በሱዳን በኩል ነበር።
ስደተኛዉ አፄ ኃይለስላሴ ሉዓላዊት፣ ነፃና የተረጋጋች ኢትዮጵያን መሥርተዉ የአፍሪቃ መሪነቷን ካረጋገጡ በኋላ በ1970ዎቹ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሱዳኖች ደቡብ-ሰሜን ብለዉ ሲገዳደሉ አስታራቂ የሆኑት አፄ ኃይለ ስላሴ ነበሩ።
ሶሻሊስታዊዉን ርዕዮተ ዓለም የሚከተለዉ ደርግ የኢትዮጵያን የገዢነት ስልጣን ከያዘ በኋላ የካርቱም ና የአዲስ አበባ ገዢዎች ሲሻቸዉ፣ «አኽዋን አኽዋን ኢትዮጵያ ወ ሱዳንን» እያዘፈኑ፣ ሲፈልጋቸዉ አንዳቸዉ የሌላቸዉን ጠላት እየደገፉ የኢትዮጵያን የያኔ ሰሜን፣ የሱዳንን የያኔ ደቡብ ግዛቶች ባወደመዉ ጦርነት በቅርብ  ተሳትፈዋል።በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ምዕራባዉያን መንግስታትም የሶቭየት ሕብረት «ተቀፅላ» ይሉት የነበረዉን የደርግን መንግሥት ለማዳከም ሱዳንን እንደ ጥሩ፣ምቹና ስልታዊ መሳሪያ ተጠቅመዉባታል።
ግንቦት 1989 በመፈንቅለ መንግስት የካርቱም ቤተ መንግስትን የተቆጣጠሩት የያኔዉ ኮሎኔል ዑመር ሐሰን አልበሽር አምባገነን፣ ጨቋኝ፣ኋላ ደግሞ  በተለይ ለምዕራባዉያን በማዕቀብ የተቀጡ፣በዓለም ፍርድ ቤት የሚታደኑ ወንጀለኛ ናቸዉ።አልበሽር ሥልጣን በያዙ በሁለተኛ ዓመቱ ግንቦት ኢትዮጵያ እሁለት ተገምሳ፣ አዲስ አበባና አስመራ ላይ ሁለት መንግስታት እሲከመሰረት ድረስ ግን ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት፣ የካርቱሙ አምባገነን የዋሽግተን-ሪያድ፣የለንደን ፓሪስ፣ የካይሮ-ብራስልስ ቀኝ ዕጅ ነበሩ። 
                                       
ደርግን የተኩት የአዲስ አባባ ገዢዎች የዋሽግተን-ብራስልሶች ታማኝ ተባባሪ፣ የአፍሪቃ ቀንድ ጠንካራ መሪነታቸዉን ለማረጋገጥ ጊዜ አልገፈጀባቸዉም ነበር።የፖለቲካ ተንታኝ ረዳት ፕሮፌሰር ሙከረም ሚፍታሕ እንደሚሉት ሕወሓት መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት በሐገሪቱ ሕዝብ ዘንድ የነበረዉ ተቀባይነት እስከቀነሰበት ጊዜ ድረስ የምዕራባዉያን ድጋፍ አልተለየዉም።
ባንፃሩ ምዕራባዉያን፣ አዲስ አበቦችን ከዕቅፋቸዉ ካስገቡ በኋላ ካርቱሞችን ገለል-ገሸሽ፣ አልፈዉ ተርፈዉ ቆጣ፣ቀጣ፣ ቆንጠጥ ያደርጉ፣ በአሸባሪነት ይወነጅሉ፣ ከስልጣን ለማስወገድና ለማሰርም ያሴሩባቸዉ ገቡ።
ከ2019 ወዲሕ ግን፣ ዶክተር ሙከረም ሚፍታሕ እንደሚሉት ፣ሱዳን ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በለዉጥ ሒደት ላይ ብትሆንም የዋሽግተን ብራስልስ መንግሥታት ካርቱሞችን ጠጋ፣አቀፍ፣ ኢትዮጵያን ገሸሽ-ገፍተርም እያደረጓት ነዉ።ዶክተር መከረም እንደሚሉት ለምዕራቦች የዉጪ መርሕ ወይም ፖሊስ ለዉጥ ዋና ምክንያት የሆነዉ ግን የሱዳን መሪዎች፣ ከኢትዮጵያ በተሻለ ልዩነታቸዉን ለማጥበብ በመደራደር፣ መወያየትና መስማማታቸዉ፣ ኢትዮጵያ በመድከሟ እንጂ ሱዳን የተሻለ ስልታዊ ጠቀሜታ ስላላት ወይም ምዕራባዉያን ስለሚወላዉሉ አይደለም።
አቶ ዩሱፍም በዚሕ ይስማማሉ።ከካርቱም እስከ ኮርዶፋን፣ ከዳርፉር እስከ ብሉ ናይል ያሉ የሱዳን ፖለቲከኞች ልዩነታቸዉን ለማጥበብ ይደራደራሉ።ኢትዮጵያዉያን ፖለቲከኞች ባንፃሩ ምክንያቱ ምንም ሆነ ማን አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለማጥፋት ተከታዮቻቸዉን ያዋጋሉ።ሕዝብ ያስፈጃሉ፣ያሰድዱ ያፈናቅላሉ፣ የደሐ ጥሪት ያወድማሉ።
ኢትዮጵያ መዳከም ለካርቱሞችም የልብ ልብ ሰጥቶ ወይም አስግቶ አወዛጋቢ የድንበር ግዛትን እንድትቆጣጠር፣ በሕዳሴ ግድብ ሰበብ ከካይሮ ጋር እንድትለጠፍ ምክንያት ሆኗል።አቶ ዩሱፍ ያሲን በ1980ዎቹ ማብቂያ ካርቱምን የመጎብኘት ዕድል አጋጥሟቸዉ ነበር።
                                        
የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ያዉም ድፍን ኢትዮጵያን የሚመራ የገዢ ፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣናት የሆኑት የጂጂጋና የሠመራ ፖለቲከኞች ጠብ ደግሞ ግራ ከማጋባትም አልፎ ብዙዎች እንደሚያምኑት  የባለስልጣናቱ የፖለቲካ ብስለትና ብቃት በጎሰኝነት የታጠረ፣ አንዳዶች እንደሚጠረጥሩት ከዉጪ ለሚገኝ ጥቅም ያደሩ መሆናቸዉን የሚያረጋግጥ እንዳይሆን ያስጋል።
የአፍሪቃ ቀንድን ለማረጋጋት ካካባቢዉ ትልቅ ሚና ሊኖራቸዉ የሚችለዉ አንድም ኢትዮጵያ ሁለትም ሱዳን መሆናቸዉ አያጠያይቅም።ሁለቱ መንግስታት እንደ ኢትዮጵያ በየዉሳጣቸዉ ዓለያም ካለፈዉ ታሕሳስ ጀምሮ እንደምናየዉ አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ጋር በየሰበብ አስባቡ የሚጋጩ ከሆኑ ከሩቅ የሚታዘበዉ ኃያል ዓለም የተሻለ መረጋጋት ያለባትን ሱዳንን ቢመርጥ ብዙ ምክንያት አለዉ።ደግሞም መብቱ ነዉ።
ምርጫዉ ግን የኢትዮጵያ አለመረጋጋት የፈጠረዉ፣ ምናልባትም ከጊዚያዊነት ባለፍ ለአፍሪቃ ቀንድ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት መቻሉን ዶክተር ሙከረም ይጠራጠራሉ።
                            
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በምዕራባዉያን ለመመረጥ ወይም ከሌላዉ ለመብለጥ ሳይሆን እራሳቸዉ ለሚኖሩባት ሐገርና ለሚመሩት ወይም እንመራሐለን ለሚሉት ሕዝብ ሠላምና ደሕንነት ካሰፈኑ ፈላጊያቸዉ ብዙ፣ተፈላጊነታቸዉ ዘላቂ፣ እርካታቸዉም ከፍተኛ ነዉ።እንደገና አቶ ዩሱፍ።
                                        
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ ባለፈዉ ግንቦት እንዳሉት ሱዳን ከ30 ዓመታት በኋላ ዳግም «ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ» የሚባለዉን የምዕራቡን ዓለም ተቀይጣለች።የፓሪስ ክለብ የሚባለዉ ስብሰብ የሚያስተናብራቸዉ ሐገራት ሱዳን ላይ ካለቸዉ ዕዳ ከ19 ቢሊዮን ዶላር የሚበልጠዉን ለመሰረዝ ወስነዋል።የዓለም ገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ እንዳስታወቁት ደግሞ ሱዳን ባጠቃላይ 50 ቢሊዮን ዶላር ግድም ዕዳ ይሰረዝላታል።ሌላ ብድር እየተሰጣትም ነዉ።ይሕ ማለት ግን ኢትዮጵያን ማግለል ነዉ ብሎ ማሰብ ሊያሳስት ይችላል።

Frankreich Emmanuel Macron und Abdalla Hamdok
ምስል Ludovic Marin/AFP
Grenzstreit zwischen Äthiopien und Sudan I Metema Stadt
ምስል Alemenew Mekonnen/DW
Karte Äthiopien Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre DE

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ