1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ምርጫ ውጤት ማነጋገር መቀጠሉ

ረቡዕ፣ ሰኔ 17 2007

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ( ኢ ሕ አ ዴ ግ) እና አጋር ድርጅቶቹ ባለፈው ግንቦት የተካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ ማሸነፋቸው ማንንም አላስገረመም።

https://p.dw.com/p/1Fmuy
Äthiopien Wahlen 2015
ምስል DW/E. Bekele

[No title]

ብሔራዊው የምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው ውጤት እንዳሳየው፣ ኢ ሕ አ ዴ ግ እና ተባባሪዎቹ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉትን 547 መንበሮች በሙሉ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት በተቃዋሚ ፓርቲ አባልና በግል ፖለቲከኛ ተይዘዉ የነበሩ ሁለት መቀመጫ ጭምር ጠቅልለዋል። ለዚህ ድል ያበቃቸውም መንግሥት አስገኘሁት የሚለው የኤኮኖሚ እድገት ነው።

ባለፈዉ ግንቦት 16 2007 ዓም የተደረገዉ የኢትዮጵያ ምርጫ ውጤት ካሁን ቀደሞቹ የተለየ ይሆናል ብሎ የጠበቀ ሰው አልነበረም። ውጤቱ ገዢው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር - ኢሕአዴግ እና አጋር ድርጅቶቹ ከአምስት ዓመት በፊት ካስመዘገቡት 99,6% የመራጭ ድምፅ ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን ነበር ብዙዎች ታዛቢዎች የገመቱት። ይሁንና፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሰኞ ይፋ ያደረገውን ኢ ሕ አ ዴ ግ እና ተባባሪዎቹ 547ቱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በሙሉ፣ በተቃዋሚ ተይዞ የነበረውን ሳይቀር የጠቀለለበትን የ5ኛውን አጠቃላይ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት ብዙዎች ለማመን እጅግ ነው ያዳገታቸው። የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫውን ውጤት ኢዴሞክራሲያዊ እና አሳፋሪ ሲሉ አጣጥለውታል።

Äthiopien Wahlen 2015
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

2004 ዓም ወዲህ ኢትዮጵያን የሚመሩት ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የፖለቲካውን ስርዓት ክፍትና ሁሉን አሳታፊ እንደሚያደርጉ ቃል ቢገቡም፣ በለንደን የሚገኘው «ቻተም ሀውስ» የተሰኘው የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ጄሰን ሞስሊ እንደሚሉት፣ ገሀዱ ተቃራኒ ነው።

« የምርጫው ምህዳር ክፍት እና ገደብ ያላረፈበትን ነፃ ፉክክር የሚያበረታታ አይደለም። የተቃዋሚው ወገን ስለዚሁ ቅር የሚያሰኝ ጉዳይ ከመንግሥት ጋር መነጋገር አለበት። »

እርግጥ፣ ምርጫው ስነ ስርዓቱን ጠብቆ በሰላማዊ መንገድ ቢካሄድም፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕጩዎች ብዙ እንቅፋት እንደተደቀነባችው ነው ተንታኙ የገለጹት። መንግሥት ምርጫው ከመደረጉ በፊት በነበሩት ጊዚያት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላትን እና የማይመቹትን ትችት የሚያቀርቡ ጋዜጠኞችን አስሮዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እና ባጠቃላይ ለፖለቲካው ተሀድሶ ሳይሆን ለልማቱ ቅድሚያ እንደሰጠ በአዲስ አበባ የሚገኘው የጀርመናውያኑ የፍሪድሪኽ ኤበርት ፖለቲካ ተቋም ኃላፊ ክራመ ሽቴርሞዘ አመልክተዋል።

Logo Friedrich-Ebert-Stiftung

« መንግሥት ትኩረቱን በኤኮኖሚያዊው ልማት ላይ ማሳረፉን እና የፖለቲካው ተሀድሶ በመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንደማይገኝ በተደጋጋሚ አስታውቋል። »

ክራመ ሽቴርሞዘ እንደሚሉት፣ ይህ የመንግሥቱ ትኩረት የሀገሪቱ ኤኮኖሚ ባለፉት ዓመታት ያሳየው በዘጠኝ እና በ12 ከመቶ መካከል ያሳየው እድገት አረጋግጦዋል።

« የኤኮኖሚያዊው ልማት ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ ግዙፍ እድገት አሳይቷል፣ ብዙው የህብረተሰብ ክፍልም ይህን ኤኮኖሚያዊ እድገት በከተሞች ብቻ ሳይሆን በክልሎችም የተስፋፋው የግንባታ እንቅስቃሴ ያስገኘውን የተሳካ ውጤት በግልጽ አይቶታል። ይህ ግን የሕዝቡ ፍላጎት በጠቅላላ ተሟልቷል ማለት አይደለም። »

ገዢው ፓርቲ የሀገሪቱን ልማት በማሳደጉ ረገድ ያስገኘው እድገት ምርጫውን ብግልጽ ላሸነፈበት ድርጊት ማረጋጋጫ መሆኑን የመንግሥቱ ቃል አቀባይ የምርጫው ውጤት እንደታ ይፋ ከሆነ በኃኋላ ተናግረው ነበር፣ የ«ቻተም ሀውስ» ተንታኝ ጄሰን ሞስሊ ግን ስኬቱ ያን ያህል በምርጫው ውጤት ላይ ሚና መጫወቱን እንደሚጠራጠሩት በመግለጽ አባባሉን የተጋነነ ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

« እርግጥ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በኤኮኖሚው ዘርፍ ላይ አስገራሚ ተሀድሶ በማድረግ ላይ ነው። መሠረተ ልማቱን አሻሽሎዋል፣ ለምሳሌ የኮሬንቲ አቅርቦቱከፍ ብሏል፣የስልኩ መስመር ተስፋፍቷል፣ እነዚህ ጉዳዮች ሁሉ በጣም አስፈላጊ ናቸው፣ ግን ለብዙ ሰዎች ይህ ነው የሚባል የተጨበጠ ፈጣን ለውጥ አያመጡም። ይህ የተደረገው መሻሻል በብዙኃኑ ዜጎች ዘንድ የሚታይ ለውጥ አስገኝቶ የምርጫውን ውጤት መለወጥ መቻሉ አጠራጣሪ ነው። »

የጀርመናውያኑ የፍሪድሪኽ ኤበርት ፖለቲካ ተቋም ኃላፊ ክራመ ሽቴርሞዘ እንደሚሉት፣ የኤኮኖሚውን እድገት በምርጫው ላገኘው መቶ ከመቶ ድል እንደምክንያት ያቀረበው የኢትዮጵያ መንግሥት በሥልጣን ለመቆየት ከፈለገ ይህንኑ እድገት ሁሌ ማስቀጠል ይኖርበታል።

ማድሌነ ማየር/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለስ