1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መንግስት የበዓል አከባበር መርሐ-ግብር

ሐሙስ፣ ነሐሴ 25 2009

የኢትዮጵያ መንግስት የ2010 ዓ.ም አዲስ ዓመት ለመቀበል ልዩ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በፌደራል እና የአዲስ አበባ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽሀፈት ቤቶች አዘጋጅነት የተሰናዳው ይሄው ዝግጅት ለ10 ቀናት ይቆያል፡፡ በአንጻሩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመንግስት መስሪያ ቤቶች “ድል ያለ ድግስ ከመደገስ“ እንዲታቀቡ መመሪያ አስተላልፎ ነበር፡፡

https://p.dw.com/p/2jAQD
Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

የአዲስ ዓመት አቀባበል በ10 ቀናት ዝግጅት ይከበራል

የኢትዮጵያ መንግስት ያዘጋጀው የ2010 ዓ.ም አዲስ ዓመት በዓል “መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ተገልጿል፡፡ የበዓሉ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ዛሬ ፕሬዝዳንት  ሙላቱ ተሾመ በተገኙበት በሸራተን አዲስ ተካሂዷል፡፡ አዘጋጆቹ ከነገ ጀምሮ እስከ አዲስ ዓመት ዋዜማ ድረስ ላሉት እያንዳንዱ ቀናት ስያሜ ሰጥተዋቸዋል፡፡ ከፍቅር እስከ ሰላም፣ ከንባብ እስከ መከባበር፣ ከአንድነት እስከ ሀገር ፍቅር ያሉ ሀሳቦች በልዩ ቀን እንዲታሰቡ ቀን ተቆርጦላቸዋል። 

ነገ ነሐሴ 26 በ“ፍቅር ቀን” ነዉ-የተሰየመው፡፡ በዕለቱ የአዲስ አበባ ከንቲባ የአቶ ድሪባ ኩማ ፊርማ ያረፈበት ፖስት ካርድ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ለከፍተኛ ባለስልጣናት ይበረከታል ተብሏል፡፡ ፖስት ካርድ እና አበባ ማበርከቱ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደሚደረግም የድርጊት መርኃ ግብሩ ያመለክታል፡፡ ፍቅርን መግለጫ-ነዉ። በነሐሴ የመጨረሻ ቀን የሚከበረው “የንባብ ቀን” መቶ ህጻናትን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ፊት የማቅረብ እቅድ አለው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህጻናቱ ከተመረጠ መጽሐፍ ላይ አንድ አንቀጽ ያነቡላቸዋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ 

ከስምንት ቀን በኋላ ጳጉሜ ሶስት ደግሞ በመላው ኢትዮጵያ ለአምስት ደቂቃ ስራ አይኖርም፡፡ “መጓጓዣዎች በያሉበት እንቅስቃሴ ያቆማሉ፤ ከብሔራዊ መዝሙር ውጭ ምንም ዓይነት ድምጽ አይሰማም፡፡” ይህ አዘጋጆቹ “የሃገር ፍቅር ቀን” ሲሉ በሰየሙት ዕለት ከሚከናወን ዝርዝር ተግባር የተወሰደ ነው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ የሚጓዘው የ10 ቀናት ዝግጅት የሚጠናቀቀው ጳጉሜ 5 ቀን 2009 ዓ.ም ከሚሊኒየም አዳራሽ በሚሰናዳ የኪነ ጥበብ ዝግጅት እንደሆነ የድርጊት መርሃ ግብር መግለጫ ይዘረዝራል፡፡ በዕለቱ እኩለ ሌት ላይ የአዲስ አበባን ሰማይ በርችት ለማሸብረቅም ታቅዷል፡፡ 

Äthiopien Addis Abeba Blumen Symbol Neujahr
ምስል DW/E.Egziabher

የአዲስ ዓመት አቀባበል ስነ ስርዓቱን ማዘጋጀት ያስፈለገው ከኢትዮጵያ የሚሊኒየም ክብረ በዓል ወዲህ የተገኙ ስኬቶችን ለመዘከር  እንደሆነ ከመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ የበዓሉ መርሃ ግብር በመንግስት በይፋ ከመገለጹ በፊት ሾልኮ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የወጣ ሲሆን መነጋገሪያም ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይበልጥኑ ያነጋገረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች “በህዝብ ገንዘብ ድል ያለ ድግስ እንዳይደግሱ እና ወጪያቸውን እንዲቆጥቡ” መመሪያ ካስተላለፈ ወር እንኳ ሳይሞላው ቀናት የሚፈጅ በዓል ሊደረግ ነው መባሉ ነው፡፡

የዶይቼ ቬለ አድማጮች እና የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተከታታዮች ይህንኑ የተመለከቱ አስተያየታቸውን አጋርተውናል፡፡ ከደቡብ ክልል ከዳውሮ ዞን ተርጫ አስተያየታቸውን በዋትስ አፕ ቁጥራችን የላኩልን ዘካርያስ ኃይለሚካኤል ይህ የሚያሳየው “መመሪያዎች ከፍተኛ አመራሮችን እንደማይመለከት ነው” ብለዋል፡፡ 

“በጣም የሚገርም ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ስንሰማ የመንግስት ወጪዎችን ለመቀነስ በርካታ አስራሮችን እንደዘረጋ ገልጾልናል፡፡ ይሄ ነገር ግን ተግባራዊ የሚደረገው በዝቅተኛ የስልጣን ሰዎች እንጂ በባለስልጣናት ላይ እንዳልሆነ ማረጋገጥ ችለናል፡፡ ከዚህ በዓል አከባበር የምንረዳረው ይሄንን ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ረሃብ እኮ ብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦቻችን እኮ በረሃብ እያለቁ ነው ያሉት፡፡ በሶማሌ፣ ደቡብ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር ብትሄድ፣ በየቦታው ረሃብ ሆኗል፡፡ ምናለ በሸራተን አዲስ እዚያ የሚዝናኑበት ገንዘብ በረሃብ ለሚያልቀው ህዝባችን ስንዴ ገዝተው ቢያከፋፍሉ ጥሩ ነበር፡፡ ያው የመንግስታችን ውጤት ይሄው ነው” ይላሉ አቶ ዘካርያስ፡፡ 

BdT Feuerwerk für die Queen
ምስል AP

ስማቸውን ያልገለጹ ሌላ አድማጭ መንግስት በዓሉን ለማክበር የተነሳው “የህዝብን ትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር ነው” ብለው ያምናሉ፡፡ “አሁን ፖለቲካዊ ትኩረት ለማግኘት እና ህዝቡ ላይ እየተፈጠረ ያለውን ጥሩ ያልሆነ ስሜትን ወደ ራሳቸው መስመር ውስጥ ለማስገባት ያለመ እና ያቀደ ነው፡፡ ይሄ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ ግን አሁን በጣም የሚያሳዝነው በዚህ ወቅት ላይ ተሁኖ ህዝቡ በጣም በብዙ ነገሮች ፣ በኑሮ ውድነት፣ ከስራ ማጣት፣ ግብር ከሚችለው በላይ ከተጫነበት ጫና አንጻር በጣም ብዙ ሮሮ በሚያስማበት ጊዜ እንደዚህ አይነት ወጪዎች ወጥተው የእነርሱን የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ ለማራመድ ሲባል የሰሩት ሴራ እና ሴራቸው ነው” ብለዋል፡፡ 

እንዳለማው አበራ በዶይቸ ቬለ ፌስ ቡክ ገጽ በሰጡት አስተያየት በዓሉ “በተጨባጭ እርምጃዎች ከታገዘ ጥሩ ነው” ይላሉ፡፡ ተጨባጭ እርምጃዎች ካሏቸው ውስጥ “የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ በተቃውሞ ፖለቲካ ላይ የተጣለውን ገደብ ማንሳት እና የፕሬስ ነፃነትን ማክበር” እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ከተደረገ “እውነትም አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ ማለት እንችላለን” ብለዋል፡፡

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸዉ የመንግስት ባለሥልጣናትን በስልክ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ብንሞክርም ልናገኛቸዉ አልቻልንም።

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ