1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መንግስት የቦንድ ሽያጭ ጣጣ

Eshete Bekele ረቡዕ፣ ሰኔ 8 2008

የኢትዮጵያ መንግስት በዩናይትድ ስቴትስ ቦንድ ሸጦ የሰበሰበውን ወደ 6.5 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ተመላሽ እንዲያደርግ ውሳኔ ተላልፎበታል። ገንዘቡ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ሽያጭ አማካኝነት የተሰበሰበ ነበር።

https://p.dw.com/p/1J6uB
Ägypten Äthiopien Damm am Nil
ምስል William Lloyd-George/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ መንግስት የቦንድ ሽያጭ ጣጣ

የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ዝውውርና የንግድ ልውውጥ ጠባቂ ኮሚሽን (Security and Exchange Commission (SEC) ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአገሪቱን የአሠራር ሥርዓት በመጣስ ለሸጣቸው ቦንዶች ያገኘውን ገቢ ከነወለዱ እንዲመልስ ወስኗል። የኢትዮጵያ መንግሥት ተመላሽ የሚያደርገው ገንዘብ 6.5ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነው። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ.ም. እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ገቢ በዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ከተሞች ከሚገኙ 3,100ሰዎች $5.8ሚሊዮን ዶላር በቦንድ ሽያጭ አማካኝነት ማሰባሰቡን ኮሚሽኑ በድረ-ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የኢትዮጵያ ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በጉዳዩ ላይ መንግሥታቸው ከዩናይትድ ስቴትስ አቻው ጋር ለረጅም ጊዜ እንደመከረበት ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሽያጭ ያቀረባቸውን ቦንዶች በዋሽንግተን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ድረ-ገጽ እና በመንገድ ላይ ትዕይንቶች አስተዋውቋል። በጎርጎሮሳዊው የዘመን ቀመር ከ2011 እስከ 2013 ባሉት አመታት በተለያዩ ከተሞች ባካሄደው ቅስቀሳ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቃል የተገባውን የገንዘብ መጠንም ዘርዝሯል። በሬዲዮ እና የቴሌቭዥን ማስታወቂያዎችም በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውን ቦንድ እንዲገዙ ቀስቅሷል።

Äthiopien Minister Getachew Reda
ምስል DW/G. Tedla

ለሽያጭ የቀረቡት ቦንዶች ከ5-10 ባሉት አመታት ወለድ የሚከፈልባቸው ሲሆን የወለዱ መጠን ከ1.25በመቶ እስከ 2.0በመቶ ይደርሳል።

5.8ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ቦንዶች ከገዙት መካከል 64በመቶው የአሜሪካን ዜግነት ያላቸው መሆናቸውን ሴኩሪቲስ ኤንድ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን አስታውቋል። ቦንዶቹ የሚጎመሩበት ጊዜ ገና በመሆኑ ለማናቸውም ወለድ መክፈል አልተጀመረም።

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ቦንዶቹን ለሽያጭ ሲያቀርብ ተገቢውን ምዘገባ ባለመፈጸሙ የአገሪቱን የአሠራር ሥርዓቶች መጣሱን ኮሚሽኑ አስታውቋል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ መንግስት ቦንድ ለገዙ ሰዎች ተመላሽ ክፍያ $5,847,804ዶላር እና 601,050.87ዶላርወለድ በአጠቃላይ 6,448,854.87ዶላር እንዲከፍል ተወስኖበታል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ30 ቀናት ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ የፋይናንስ ተቋም እንዲከፍል የተወሰነውን የገንዘብ መጠን ተቀማጭ እንዲያደርግ የሴኩሪቲስ ኤንድ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን ትዕዛዝ አስተላልፏል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተቀመጠለት ቀነ ገደብ መሠረት ገንዘቡን ተቀማጭ ካላደረገ ተጨማሪ ወለድ ለመክፈል የሚገደድ ይሆናል። ኮሚሽኑ ትዕዛዙን ካስተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ ከአንድ አመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተቀማጭ የሚደረገው ገንዘብ ለሚመለከታቸው እንደ ድርሻቸው ተከፋይ መሆን እንዳለበት ኮሚሽኑ አስታውቋል። የኢትዮጵያ ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ መንግሥታቸው ኮሚሽኑ ያስተላለፈውን ውሳኔ ቦንዱን ከገዙ ወገኖች ጋር በሚደረግ ውይይት ተፈጻሚ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴት የገንዘብ ዝውውርና የንግድ ልውውጥ ጠባቂ ኮሚሽን ባለ ወረቶችን የመጠበቅ የገበያን ፍትኃዊነት እና ሥርዓት የመጠበቅና የመቆጣጠር ስልጣን የተሰጠው ተቋም ነው። ተቋሙ የተመሠረተውም በአገሪቱ ኮንግረስ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ በጥብቅና ሙያ የሚተዳደሩት የህግ ሰው ዶ/ር ፍጹም አቻምየለህ« ኮሚሽኑ እጁ ሰፊ ነው።» ሲሉ ይናገራሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔውን ተግባራዊ ካላደረገ ተቋሙ የከፋ እርምጃ ሊወስድ ይችላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። በእርሳቸው ገለጻ ኮሚሽኑ ውሳኔውን ወደ ማስፈጸም ሊገባ ይችላል።

ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ወይም (4.7ቢሊዮን ዶላር) ወጪ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገነባው የህዳሴ ግድብ አባይን ከሚጋሩ አገራት ጋር ዲፖሎማሲያዊ ውጥረት ፈጥሯል። ውጥረቱ አንዴ ሲከር ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲረግብ ቢስተዋልም ግንባታው አልተቋረጠም። አንዳንድ ጸሐፊዎች አባይን የመጋራት ነገር በተለይ በኢትዮጵያ እና ግብጽ መካከል «የውኃ ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል»ሲሉ ጽፈዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ፈጽሞ አልደራደርበትም የሚለው የህዳሴ ግድብ ግንባታ በአብዛኛው በአገር ውስጥ ወጪ እንደሚሸፈን አስታውቋል። አቶ ጌታቸው ረዳ ለግድቡ ግንባታ የሚያስፈልገውን ወጪ በማሰባሰቡ ረገድ ከአገር ውስጥ የተሰበሰበው ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ