1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስታዊዉ ቀዉስ

ሰኞ፣ ሰኔ 8 2012

የአብዛኛዉን ኢትዮጵያዊ ድጋፍ፣ ሠላም ለማስፈን የጀመሩት ጥረት ለኖበል ሽልማት ያደረሰ ዓለም አቀፍ ይሁንታ ማግኘቱ ግን ሐቅ ነዉ።ጥሩም።ጥሩዉ ሐቅ፣ ሕግ እያሻረ ቀዳሚዎቻቸዉ ወደ ተጓዙበት ቁልቁለት እንዳይገፋቸዉ ነዉ  ጥርጣሬ ሥጋት ፍርሐቱ።

https://p.dw.com/p/3doXG
Premierminister Dr. Abiy Ahmed
ምስል PM Abiy Ahmed Ali Office

የኢትዮጵያ የፌደሬሽን ምክር ቤት ዉሳኔና ቀዉሱ


የረጅም ዘመን የጦር ሜዳ ዉጊያ፣ የየፖለቲካ ዲፕሎማሲ፣ ሐገር የመምራት ኃላፊነት፣ እድሜም ብዙ እንዳስተማራቸዉ የሚጠበቁት የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ መሪዎች ጥንታዊ፣ታሪካዊቱን ግዛት መድረሻ አልቦ እየጋለቧት ነዉ።ሐቻምና ይሔኔ ካዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ጋር ብርጭቆ ለማጋጭት ከየሆቴል-ቤተ መንግስቱ አዳሮሾች ሲርመሰመሱ የነበሩት፣ ከአስመራ፣ አዉሮጳ-አሜሪካ ተንደርድረዉ አዲስ አበባ የገቡትም ተቃዋሚዎች አሁን ጠቅላይ ሚንስትሩን ይተቹ፣ ያወገዙም ይዘዋል።የሕዝብ ተቃዉሞ፣የሕወሐቶች የግዴታ-ይሁንታ፣ የተቃዋሚዎች ግፊት ከትልቁ ስልጣን ያበቃቸዉ ዐብይ አሕመድ ግን አክሊሉን እንጂ ሚካኤልን አንዳይደሉ፣ እንደ መለስ እንጂ እንደ ኃይለማርያም እንደማይሹ እያስመሰከሩ ነዉ። በሚወዱት ሕዝባቸዉ ትግል፤ ከሚወዱት ፓርቲያቸዉ የተሰጣቸዉን የሚወዱትን ሥልጣን ለተጨማሪ ዘመን አራዘሙ።እርማጃ፣ግሊቢያ፤ ዉግዘቱ ኢትዮጵያና ሕዝቧን እንዴትና  ወዴት ያጉዛቸዉ ይሆን ነዉ የከእንግዲሁ ጥያቄ?
                                           
የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራሉ ሳሞራ ዩኒስ ባለፈዉ ሳምንት በሰጡት ቃለ መጠይቅ 42 ዓመታት እንደ ፖለቲከኛ የታገሉ፣ እንደ ሸማቂ የተዋጉ፣ እንደ ጦር አዛዥ ያዋጉ፣ ለባለ አራት ኮኮብ ጄኔራልነት ማዕረግ የበቁበትንም ሥልጣን የለቀቁትን ተመልሰዉ ለመያዝ አይደለም።
«ከመከላያ ሚኒስቴርን የለቀቅሁት ተመልሼ ለመግባት አይደለም» በሳቸዉ አገላለፅ።እንደ ጄኔራሉ ሁሉ፣በዘመናይቱ ኢትዮጵያ የሕወሓት መሪዎችን ያክል በጦር ሜዳ ዉጊያ፣በርዕዮተ ዓለም ሙግት፣ሐገር በመምራት ኃላፊነት፣ በእድሜም ጭምር የበሰለ ወይም በሳል ተብሎ የሚገመት ፖለቲከኛ ማግኘት ሲበዛ ከባድ ነዉ።
ከአርባ ዓመት በላይ የበሰሉት የሕወሓት መሪዎች እራሳቸዉ ለመለመሉ፣ላስተማሩ፣ለሾሙ-ለሸሏሟቸዉ ተከታዮቻቸዉ (የቀድሞ እንበለዉ) የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም የአራት ኪሎ ቤተ-መንግስትን ሲያስረክቡ ጄኔራሉ እንዳሉት «ተመልሰዉ ለመግባት» አስበዉ ነዉ-ብሎ ያሰበ በርግጥ አልነበረም።

Willkommen für den Friedensnobelpreisträger Dr. Abiy Ahmed
ምስል DW/S. Muchi

ከመጋቢት 2010 ጀምሮ ቀስበቀስ መቀሌ ላይ የከተሙት የሕወሓት መሪዎች ግን ከፌደራሉ መንግስት ጋር የገጠሙት እሰጥ አገባ፣ ለዘመናት የዳበረ ልምድ፣ብስለት፣ አርቆ አሳቢነት፣ የዕድሜ አንቱታን ሳይሆን  የለቀቁትን ቤተ-መንግስት መልሰዉ ለመቆጣጠር ያለሙ፣በ1960ዎቹ ማብቂያ ጫካ ሲገቡ በነበሩበት እሳቤ የሚነዱ መምሰሉ ነዉ ቀቢፀ ተስፋዉ።
የሕወሓት መሪዎች የድርድር ዉይይታቸዉ ዉጤት ምንም ሆነ-ምን፣ «ነፃ አዉጪ» በነበሩበት ዘመን ደም ከተቃቧቸዉ ከኢሕአፓ፣ ከኢዲዩ፣ከኢሕዴን፣ከኦነግ እና ከሌሎች አቻዎቻቸዉ ጋር መደራደራቸዉን የትግል-ገድል ታሪካቸዉ አካል አድርገዉ የማይተርኩበት ጊዜ የለም።«ፋሺስት» ከሚሉት ደርግ ጋር መደራደራቸዉንም እናዉቃለን።ሥልጣን ከያዙ በኋላ መቶ ሺዎችን በማገዱበት ጦርነት መሐልና ማግሥት ከሻዕቢያ መሪዎች ጋር ከዋጋዱጉ እስከ አልጀርስ እየተመላለሱ ተነጋግረዋል።
ዛሬ እራሳቸዉ ካሳደጉ፣ከኮተኮቱ፣ ካሰለጠኑ ወይም ካሰየጠኗቸዉ ጋር ለመደራደር የሕዝብ ጥሪን፣ የቀሳዉስት-ሼኮች ተማፅእኖን፣የዲፕሎማቶችን ምክር አሻፈረኝ ብለዉ የሚገዙትን ክልል ሕዝብ ለብቻዉ የሚያሮጡበት ምክንያት በርግጥ ግራ ነዉ።የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በቅርቡ ባወጣዉ መግለጫ የፌደራሉን መንግሥት መሪዎች «ግል ገል አምባ ገነን» በማለት አዉግዟቸዋል።የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤነታቸዉን ባለፈዉ ሳምንት የለቀቁት የሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ኸይሪያ ኢብራሒምም «አምባገነናዊ ሥርዓት» እየተመሠረተ ነዉ ብለዋል።
የፌደራሉ መንግስት እርምጃና ዉሳኔ ስሕተት፣ ጥፋት፣ ምናልባትም ሕወሓት እንዳለዉ «ግልገል አምባገነንነት»  ሊሆን ይችላል።ስሕተት፣ ጥፋቱ  ለሕወሓት እርምጃ የትክክለኛነት ማረጋገጪያ (ጀስቲፌኬሽን) ይሆናል ብሎ ማሰብ ግን በርግጥ ጅልነት ነዉ።

የትግራይ ምክር ቤት የፌደራሉ መንግስት ምክር ቤቶችን ዉሳኔ በመቃረን በትግራይ ክልል ከመስከረም በፊት ምርጫ ለማድረግ ወስኗል።የምርጫዉ ሒደት፣የአፈፃፀሙ እንዴትነት፣ የአስመራጩ ማንነት ገና ብዙ ያነጋግራል።
የሕወሓት መሪዎች በተደጋጋሚ እንደሚወቅሱት፣በተናጥል ምርጫ የጠሩትም ሕገ-መንግሥቱን ለማስከበር ነዉ።ሕወሓቶች የወሰኑና ሊያደርጉ ያቀዱት ራሱ ሕገ-መንግሥቱን የሚያከብር መሆን አለመሆኑ ማጠያያቁ እንጂ  እንቆቅልሹ።በኪል-ብሪታንኒያ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምሕር ዶክተር አወል ቃሲም አሎ።
                                                
የትግራይና የፌደራሉ መንግስት ገዢዎች የተካረረ ሽኩቻ፣የፕሮፓጋንዳ ጦርነትና ዘመቻ የሕገ-መንግስት መጣስ መከበር ብቻ አይደለም።ከመነሻችን እንዳልነዉ ባንድ ቆጥ ሁለት «አዉራ» የመሆን አባዜ፣ አለያም የጥቅም ግጭት ነዉ።ዶክተር አወል እንደሚሉት በመቀሌና አዲስ አበቦች የጋመዉን ፖለቲካዊ ትኩሳት ካላረገቡት ዉጤቱ ለማንም አይበጅም።
መጋቢት 1991፣ የኢትዮጵያ ጦር ባድመን ከኤርትራ ጠላቱ የማስለቀቁን ድል ለኢትጵያዉያን የሚያበስረዉን መግለጫ አንብቤ ከስቱዲዮ ስወጣ፣ ኢትዮጵያ ራዲዮ ቅጥር ግቢ ከነበሩ ሁለት የኢሕአዴግ መካከለኛ ባለልጣናት ጋር ላፍታ የመነጋገር እድል አግኝቼ ነበር።
በድል፣ ብስራት ወሬዉ መሐል ኢሕአዴግን ከሚቃወመዉ ሕዝብ የአብዛኛዉ የተቃዉሞ ምክንያት ኢሕዴግ ኤርትራን በማስገንጠሉ እንደሆነ፤ ጦርነቱ ሲፈነዳ ግን ኢትዮጵያዉያን ከኢሕአዴግ ጎን መሰለፋቸዉን፤ድሉም የሕዝብ ርብርብ ዉጤት መሆኑን እንዳቅሚቲ ጠቃቅሼ፤ ኢሕአዴግ የኢትጵያን ሕዝብ መካስ፤ ከሕዝቡ ጋር መታረቅም አለበት ዓይነት ሐሳብ ሰጠሁ።
በርግጥም፤ ምክንያቱ የገዢዎቹ ፕሮፓጋንዳ፣ ሐገር የመደፈሯ ቁጭት፣ለኤርትራ ገዢዎች የነበረዉ ጥላቻ ይሆን-አይሆንምም ይሆል።ኢትዮጵያዊዉ ግን ከጎዴ እስከ ፓዌ፣ከለደን እስከ ጂዳ፣ ከኮሎኝ እስከ ዋሽግተን ፍየሉን-ከግመል፣ ብሩን ኮዶላር፣ ቀለበቱን ከጣቱ-ሐብሉን ካንገቱ እያወለቀ ለጦሩ ድጋፍ ዘርግፍቶታል።ባድመ ድረስ ተጉዞ ታማኝ ደጀንነቱን አስመስክሮም ነበር።
 በድፍረቴ፣ወይም በየዋሕነቴ የተደመመ የሚመስለዉ አንዱ ሹም «መንግስቱ ኃይለማርም እንኮ አምባገነን የሆነዉ ከሶማሊያዉ ጦርነት ድል በኋላ ነዉ።» አለኝ።መሪዎች፣ የሚያስራቸዉ የፓርቲ ዲስፒሊን ወይም መርሕ ከሌለ፣ ሕዝቡን ከጎናችን ያሰለፍነዉ እኛ፣ድሉም የአመራር ችሎታችን ዉጤት ነዉ ሊሉ፣ ምናልባትም አምባ ገነን ይሆኑም ይሆናል እያለ ተስፋዬን ደፍጥጦ በስጋቱ አሰጋኝ።
አላበለም።ብዙም ሳንቆይ፣ በየራሳችን ምክንያት እኔም ሐገሬን እሱም ስልጣኑን ለቀቀ ወይም ተባረረ።ያሰጋኝ ስጋቱ እዉን መሆኑን ከያለንበት መሰከርንም።21 ዓመቱ።የሕወሓት መሪዎች ያኔ ጦር ሜዳ ያዘመቱት ወታደርን በ21ኛ ዓመታቸዉ ዘንድሮ  በግልገል አምባገነንነት እየወነጀሏቸዉ ነዉ።ፈረንሳዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ ረኔ ላፎር የመቀሌዎች «የግልገል አምባገነት» ዉግዘት ከመሰማቱ ከወር በፊት ባሳተመዉ መጣጥፉ ጠቅላይ ሚንስትሩ «ጠንካራ ሰዉ» የመሆን ፍላጎታቸዉን ደብቀዉ አያዉቁም ይላል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ባዲስ መልክ ያደራጁት ፓርቲ የሚቆጣጠረዉ የፌደሬሽን ምክር ቤት የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትን ምክንያት አድርጎ የምርጫዉን ጊዜ፣ የጠቅላይ ሚንስትሩን መንግሥት፣ የየምክር ቤቶች ሥልጣንንም ማራዘሙን ብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃዉመዉታል።
አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራዊ አንድነት ፓርቲ የፌደሬሽን ምክር ቤት ዉሳኔን «የሁለት ዓመቱ የለዉጥ ሒደት መክሸፍ የመጨረሻ ማሕተም» ብሎታል።የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዝደንት ሙሉጌታ አበበም የፌደሬሽን ምክር ቤት ዉሳኔን «ክፍተት አለዉ» በማለት ተቃዉመዉታል።
የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር አብዱቃድር አደምም ለተቃዉሟቸዉ ከጠቀሷቸዉ ምክንያቶች አንዱ ሒደቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አላሳተፈም የሚል ነዉ።ሌላዉ የኮሮና ተሕዋሲ «ስጋት» አለመሆኑን የሚወስነዉ ወገን  ሥልጣኑን አጓጉል ሊያራዝምበት ይችላል የሚል-ከምክንያትም ያለፈ ስጋት ነዉ።
የተቃዋሚ ፖለቲከኞቹ ዉግዘት፣ ቅሬታና ሥጋት፣ የሕወሃትን «የግልገል አምባገነንነት»ዉንጀላን ወይም የላፎርን «ጠንካራ ሰዉ» የመሆን ጥርጣሬ ያጠናክር ይሆን? ብሎገር በፍቃዱ ኃይሉ ከዉንጀላ፣ ዉገዘት፣ቅሬታዉ ይልቅ ሥጋቱን፣ ከሥጋቱም በላይ የላፎርን ግምት የሚጋራ ይመስላል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ባለዉ ቅዳሜ ባሰራጩት መግለጫ ከተቃዋሚዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸዉን አስታዉቀዋል።ይሁንና የሚሹትን ካስወሰኑ በኋላ ያቀረቡት ጥሪ የሚሰነዘርባቸዉን ዉንጀላ፣ ዉግዘት፣ ሥጋትና ቅሬታና ወይም የፖለቲካ ተንታኞችን ጥርጣሬ ሊያስወግድ አይችልም።እንዲያዉም የፌደሬሽኑ ምክር ቤት ዉሳኔን የመንግስታቸዉ ዴሞክራሲያዊነት ማረጋገጪያ አድርገዉ ማቅረባቸዉ ጥሪዉን ካንገት ከመጣ ምክንያትነት ይልቅ ካንገት የተሰነዘረ ማጀቢያ አስመስሎታል። 
ጠቅላይ ሚንስትሩ የዲሞክራሲያዊነት ማረጋገጪያ ያደረጉትን  የፌደሬሽን ምክር ቤት ዉሳኔና የሕግ አተረጓምም-የሕግ ፕሮፌሰር ዶክተር አዉል ቃሲም አሎ እንደሚሉት «አሳሳቢ» ነዉ
የተቃዉሞ፣ ትችት ወቀሳ ወደ አምባገነንነት የማጓዙ ስጋትም ዉሳኔዉ የመንግስትን ስልጣን አለመገደቡ ነዉ።የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትም የሚቆምበትን ጊዜ የሚያዉቅ የለም።የፌደሬሽን ምክር ቤት የማይታወቀዉን-ከሚታወቀዉ ጋር አለማጣጣሙን ዶክተር አወል «አሳዛኝ» ብለዉታል። 

Äthiopien nach TPLF Meeting
ምስል DW/M. Haileselassie
Keria Ibrahim ehemalige Sprecherin Ethiopia's House of Federation
ምስል DW/M. Hailesialssie

 የሮማ ቄሳሮች ጠላታቸዉን ባስገበሩ ቁጥር በየአደባባዩ  የገድል፣ድላቸዉን ታላቅነት፣ የጅግነታቸዉን ወደርየለሽነት፤የሚያወድሰዉን ሕዝባቸዉን በሰረገላ እየተዘዋወሩ ይመለከቱ ነበር አሉ።ብዙዎቹ ቄሳሮች በየሰረገላቸዉ ከሚያስከትሏቸዉ አጃቢዎች ቢያንስ አንዱ በእድሜና እዉቀት የሰበለ አዛዉንት አማካሪ ነዉ።
አማካሪዉ ስሜት የፈነቀለዉ ሕዝብ ለቄሳሩ ከሚያንቆረቁረዉ ሙገሳ አድናቆት ይልቅ በቄሳሩ ጠላቶች ላይ የሚያዥጉደጉደዉን ስድብ እርግማን እያዳመጠ ለቄሳሩ በጆሮዉ «እርስዎም ጥሩ ካልሰሩ ነገ ይኸ ርግማን ይገጥመዎታል» እያለ ይመክራል ይላሉ የሚዉቁ።
ጠቅላይ ሚንስር ዐብይ እንደ ቄሳሮቹ በሳል መካሪ፣ እንደ መለስ ጠንካራ የፖለቲካ መርሕ ወይም ዲስፒሊን ይኑር-አይኑራቸዉ አናዉቅም።የበሳሎችን ምክር ፣የፓርቲ መርሕን መጣስ አለመጣሳቸዉም አልተረጋገጠም።መንግስታቸዉ የሚመራበት ሕግ ግን አለ።ሕጉን በትክክል ለምን አልተረጎሙትም ነዉ-ጥያቄዉ? ስልጣን በያዙበት ሰሞን የገቡት ቃል የአብዛኛዉን ኢትዮጵያዊ ድጋፍ፣ ሠላም ለማስፈን የጀመሩት ጥረት ለኖበል ሽልማት ያደረሰ ዓለም አቀፍ ይሁንታ ማግኘቱ ግን ሐቅ ነዉ።ጥሩም።ጥሩዉ ሐቅ፣ ሕግ እያሻረ ቀዳሚዎቻቸዉ ወደ ተጓዙበት ቁልቁለት እንዳይገፋቸዉ ነዉ  ጥርጣሬ ሥጋት ፍርሐቱ።

Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Demonstration mit Anhängern
ምስል Reuters

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ