1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከመጋቢት እስከ መጋቢት ፤ ልዩ ዝግጅት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 24 2011

የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ስልጣን ከተረከቡ አንድ ዓመት ሆናቸዉ። የቀድሞዉ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ መንበራቸዉን ለአዲስ ተተኪዉ ያስረከቡበት እና ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ቃለ መኃላ የፈፀሙበት አንደኛ ዓመት፤ የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ 365 ቀናት።

https://p.dw.com/p/3G7Dv
Äthiopien Vereidigung Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AA/M. W. Hailu

መጋቢት 24፣ 2011 ዓ.ም ማክሰኞ «ልዩ ዝግጅት»

መጋቢት 24 2010።  አንድ ዓመት ደፈነ። ኢትዮጵያ ነገስታት አንዱ ሌላዉን ገድሎ፣አስገብሮ አለያም ወርሶ ሥልጣን ሲለዋወጡባት ለዘመናት ኖራለች።ብልጣ ብልጦች በሴራ-ሻጥር፣ ወይም በመፈንቅለ መንግስት፣ አብዮተኞች በአመፅ፣ አማፂያን በፊት ለፊት ዉጊያ ቀዳሚዎቻቸዉን እየገደሉ፣ እያሰሩ ወይም እያባረሩ ቤተ-መንግሥቶቿን ሲቆጣጠሩባት ዐመታት እየቆጠረች ታሪክ አስዘግባለች። አምና የዛሬን ዕለት በረጅም ታሪኳ ላይ አዲስ ታሪክ አከለች።የፖለቲካ ፓርቲ ሳይሆን መሪዎች ተቃቅፈዉ፣ተሳስመዉ ሥልጣን ተረካከቡ።ዶክተር ዐብይ አሕመድ-የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚንስትር።ከዜናዉ ቀጥሎ የዛሬዉ ስርጭታችን ሙሉ ጊዜዉን ዐመት የደፈዉን ለዉጥ ስኬት-ጉድለት በወፍ በረር ይዘክርበታል።
«ብዙዎች» የኢትዮጵያን የዘመናት በጣሙን የ27 ዐመቱን የፖለቲካ-ምጣኔ ሐብታዊ-ፍትሐዊ  ሒደትን የቀያየረ» ብለዉታል።ለዉጡ ሥጋትም አልተለየዉም። ፖለቲከኞች፣ የፖለቲካ ተንታኞች፣የቀድሞና ያሁን እስረኞች፣የጎሳ ግጭት ሠለቦች፣ከስደት ተመላሾች፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችንና የአዉሮጳ ሕብረት ዲፕሎማቶችን አነጋግረናል።ከዚሕ ከቦን፣ ከአዲስ አበባ፣ከጌድዮ፣ ከባሕርዳር፣ ከጂጂጋ፣ከመቀሌ ከዋሽግተን ዲሲና ከብራስልስ ያጠናቅረናቸዉን ዘገቦች አሉን። 

Äthiopien ethnische Minderheit der Gedio
ምስል DW/Shewngizaw Wegayehu Aramdie

የጌድኦ ቀዉስ
የፖለቲካ ተንታኞች «በአቋራጭ ለመጠቀም» ያሏቸዉ ወገኖች ይሁኑ፣ «ተረኛ ባለስልጣናት ነን» ባዮች፣ የቀድሞዉ ሥርዓት አራማጆች ወይም «ፅንፈኛ» ብሔረተኞች በየአካባቢዉ በቀሰቀሱት ግጭት አብዛኛዋ ኢትዮጵያ ስትታበጥ ነዉ-ዓመት የደፈነችዉ።ግጭቱ አስከፊ ሰብአዊ ድቀት ካስከተሉባቸዉ አካባቢዎች አንዱ ደቡብ ኢትዮጵያ የጌድኦ ዞን ነዉ።በግጭቱ የተፈናቀሉ አንድ አባት ለሐዋሳዋዉ ወኪላችን ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ እንደነገሩት ለዉጡ  «ለጌዲኦ ሕዝብ ነዉጥ ነዉ።»

Äthiopien Vereidigung Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture alliance/AP Photo/M. Ayene

 
ፖለቲከኞች አስተያየት
የርዳታ ድርጅቶችና መንግሥት  ዘግይተዉም ቢሆን ለጌድዮ ሕዝብ ደርሰዋል።የጌዲዮን ወይም የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብን ባጠቃላይ እንወክላለን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችስ ዘመድ፣ወዳጅ፣ ሐብት ንብረቱን ያጣዉን ሕዝብ አፅናናንተዉት ይሆን።ደም አፋሳሹ ግጭት ሲሆን እንዳይነሳ ቀድሞዉ፣ ካልሆነ፣ ከሆነ በኋላ -ዘግይተዉ ሌላ ግጭት እንዳይደገም ያደረጉት መኖር-አለመኖሩን በርግጥ አናዉቅም።የነገረን ሥለሌለ አልሰማንም።ፀኃይ ጫኔ ያነጋገረቻቸዉ የገዢና የተቃዋሚ ፓርቲ ሹማምንት ግን አዲስ አበባ ሆነዉ ዐንድ ዓመት የደፈነዉን ለዉጥ ስኬት-ጉድለት ለመተንተን ግን አልሰነፉም።

የአሜሪካዉ ስደተኛ

የጌድኦዉ አባት «ነዉጥ» ያሉት ለዉጥ ዩናይትድ ስቴትስ ለሚኖሩት ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ብስራት ነዉ።ግን ይጠይቃሉ ስደተኛዉ «ኢትዮጵያ እንዳንገባ ያደረጉን ሰዎች እኛ ባለመግባታችን ምን እንደተጠቀሙ? አሁን ደግሞ ስለገባን ምን ምን እንደተጎዱ ቢነግሩኝ ደስ ይለኛል።» እያሉ። ከ16 ዓመታት ስደት በኋላ፣ የዛሬ ዓመት የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን የጨበጡት የዶክተር ዐቢይ አህመድ «ወደሀገራችሁ ግቡ» ጥሪ አነቃቅቷቸው ኢትዮጵያ ደርሰው ያስተዋሉትን ለዋሽንግተኑ ዘጋቢያችን አጋርተውታል። 

ለዉጡና አማራ
አምና እስከ መጋቢት፣ ዉስጥ ዉስጡን ለለዉጥ ይታገላሉ፣ ወይም የሕዝብን የአደባባይ ተቃዉሞ ይደግፋሉ ከሚባሉት የገዢዉ ፓርቲ የኢሕአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል ከኦሮሚያ የአቶ ለማ መገርሳ፣ ከአማራ ደግሞ የአቶ ገዱ እንዳርጋቸዉ ስም ተደጋግሞ ይጠቀስ ነበር።ለዉጡ ዓመት ሳይደፍን ግን አቶ ገዱ የርዕሠ-መስተዳድርነቱን ሥልጣን ለሌላ አስረክበዉ እስከመቼ እንደሁ በዉል ላልተነገረ ጊዜ ከፖለቲካዉ ገለል ያሉ ይመስላል።የባሕር ዳሩ ወኪላችን ዓለም መኮንን ያነጋገራቸዉ የከተማይቱ ነዋሪዎች ግን በገዢ ፓርቲያቸዉ ዉስጥ የተደረገዉ ሹም ሽር ብዙ ያሳሰባቸዉ አይመስልም።

Äthiopien Vertriebene
ምስል Tizalegn Tesfaye

አሶሳና ምዕራብ ወለጋ
አማራ መስተዳድር ምዕራብ ጎንደር፣ ራያ፣ ወልቃይት ጠገዴና ሌላም ሥፍራ በግጭት፣ ዉዝግብ፣ ሰታበጡ ነበር።የኃይማኖት ተቋማት ሳይቀሩ በእሳት ጋይተዋል።አማራን በሚጎራበቱት በምዕራብ ኦሮሚያና በበኒ ሻንጉል አዋኝ ድንበሮች የተደረገዉ ግጭት፣ግድያና ቁርቁስ ያደረሰዉ ጉዳት በጣም ከባድ ነበር።በመቶ የሚቆጠሩ ተገድለዋል።በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል።ግጭቱ አሁን ረገብ ቢልም ሙሉ ሠላም ሠፍኗል ማለት ግን አይቻልም።የምዕራብ ወለጋዉ ነዋሪ የአካባቢዉን የፀጥታ ችግር ለማስወገድ መንግስት እንዲጥር ሲያሳስቡ፣ የአሶሳዉ ነዋሪ ደግሞ ዐብይን «የፈጣሪ ሥጦታ ይሏቸዋል።

Abiye Ahmed in Addis Ababa
ምስል Reuters/Stinger

የሶማሌ የለዉጥ ጉዞ 
የሶማሌ-ኦሮሚያ መስተዳድሮች አዋሳኝ ድንበሮች ከለዉጡ ዋዜማ ጀምረዉ ለተከታታይ ወራት ሠላም እንደራቃቸዉ ነበር።በግጭቱ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።በሚሊዮን የሚቆጠር ተፈናቅሏል።በነገራችን ላይ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ መንግስት በሰብአዊ መብት ጥሰት ከስሶ ካሰራቸዉ ባለሥልጣናት ብቸኛዉ ርዕሠ መስተዳድር የቀድሞዉ የሶማሌ ርዕሠ መስተዳድር ናቸዉ።አብዲ ዑመር መሐመድ።ጂጂጋ ከትናንት ጀምሮ የገዢ ፓርቲዋን አዳዲስ ሹማምንት ለጉባኤ ሰብስብላች። 

የፍትሕ ሥርዓቱ
የአማራ ገዢ ፓርቲ የቀድሞዉ ብአዴን ያሁኑ አዴፓ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ከሚኖሩበት አዲስ አበባ ባሕርዳር ተወስደዉ ሲታሰሩ፣ ሲከሰሱ፣ የሶማሌዉ ርዕሠ መስተዳድር አብዲ ዑመር መሐመድ ግን ከሚኖሩበት ጂጂጋ አዲስ አበባ ተወስደዉ አዲስ አበባ እየተዳኙ ነዉ።ፍትሕ ተጠየቅ-ወይም ሎጂክ አያዉቅ ይሆን?አወቀም አላወቀ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ መንግስት ባለፈዉ አንድ ዓመት የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ያደረገዉ ጥረት ብዙ ተደንቋል።የፍርድ ቤቶችን፣ የፖሊስና የወሕኒ ቤቶችን አሰራርና አደረጃጃት ፍትሐዊ ለማድረግ እየጣረም ነዉ።የኢትዮጵያ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት የሚሠራዉን ሥራ ለሕዝብና ለመገናኛ ዘዴዎች ፈጥኖ በማሳወቅም ከጠቅላይ ሚንስቴር ዐብይ አሕመድ የካቤኔ መስሪያ ቤቶች ሁሉ የተሻለዉ መስሪያ ቤት ነዉ።የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሠለሞን ሙጪ አጭር ዘገባ አለዉ።
                        
ኤርትራና ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት በብረት ጡንቻ የገዛዉ ህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) ባለፈዉ አንድ ዓመት ስሙ ብዙም በጥሩ ሲነሳ አይነሳም።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከኤርትራ ጋር ያደረጉት የሠላም ስምምነት ግን ከየትኛዉም የኢትዮጵያ መስተዳድር ይበልጥ የሚጠቅመዉ ትግራይን መሆኑ ብዙ አላጠያየቀም።የመቀሌዉ ወኪላችን ሚሊዮን ገብረ ስላሴ አጭር ዘገባ አለዉ።

Äthiopien Vereidigung Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AA/M. W. Hailu

አዉሮጳ
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የጀመሩትን ለዉጥ ምዕራባዉያን መንግስት በከፍተኛ ጉጉት እየተከታተሉት ነዉ።ድጋፍ አድናቆታቸዉን አልነፈጉትምም።በተለይ የአዉሮጳ ሕብረትና አባላቱ ለዉጡ ሠላም፣ዴሞክራሲ፣ ፍትሕና ብልፅግና እንዲያመጣ አስፈላጊ ያሉትን ድጋፍ ለማድረግ ቃል እየገቡ ነዉ።የብራስልሱ ወኪላችን ገበያዉ ንጉሴ እንደዘገበዉ በተለይ ኢትዮጵያና ኤርትራ ያደረጉት ስምምነት አዉሮጶችን በጣም አስደስቷል።                                          
 

ዶቼ ቬለ«DW»