1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሬቻዉ አደጋ እንዲጣራ ተጠየቀ

ዓርብ፣ ኅዳር 23 2009

በኢትዮጵያ ቢሾፍቱ ከተማ ሊከበር በነበረዉ የኢሬቻ በዓል ላይ መንግሥት በወሰደዉ ርምጃ ሕይወታቸዉ የጠፋዉ ቁጥርና የአደጋዉ ምክንያት ተጣርቶ ምላሽ አልተሰጠም ሲል የጀርመኑ ገዜልሻፍት ፉዩር በድሮህተ ፎልከር የተሰኘዉ ለተጨቆኑ ሕዝቦች የቆመዉ ድርጅት ትናንት ባወጣዉ ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/2Te95
Äthiopien Unruhen
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የድርጅቱ የአፍሪቃ ክፍል ተወካይ ዑልሪሽ ዴሊዩስ እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በበዓሉ ላይ ሰዎች የሞቱበትን ሁኔታና  የሟቾችን ቁጥር አዉቆ ሆነ ብሎ መደበቅ ይፈልጋል ፤ ብለዋል።  ሁኔታዉ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ሲሉም ጠይቀዋል።   

በጀርመንኛ መጠርያዉ «ገዜልሻፍት ፉዩር በድሮህተ ፎልከር» የተሰኘዉ ለተጨቆኑ ሕዝቦች የቆመዉ ድርጅት ትናንት ባወጣዉ መግለጫ በርካታ ሰዎች ለሞቱበት አደጋ ዛሬም  ምንም አይነት ምላሽ ባለማግኘቱ ሕዝብ በመንግሥት ባለስልጣናት ላይ የቀረዉን የመጨረሻ እምነት እያጣ ነዉ ሲል ባወጣዉ መግለጫ አስታዉቋል። አደጋዉ በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ድርጅቱ አሳስቦአል። ለተጨቆኑ ሕዝቦች የቆመዉ  ድርጅት የአፍሪቃ ክፍል ተጠሪ ዑልሪሽ ዴሊዩስ በኢሬቻ በዓል ላይ መንግሥት ከገለፀዉ ከ 56 ሰዎች በላይ ሳይሞቱ አልቀረም ይላሉ።

«አንድ ገለልተኛ የዓለም አቀፍ መርማሪ ተቋም እንዲኖር እንፈልጋለን ። በኢሬቻ በዓል ላይ የተፈጠረዉ ክስተትና የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ እስካሁን በወጣዉ መረጃ የተለያየ ነዉ። በዚህ ክስተት ላይ ምናልባትም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይሞቱ  አልቀረም። ይህን ሁሉ ማጣራት ያስፈልጋል ይህ ካልተጣራ ግን መንግሥት በነዋሪዉ ተዓማኒነትን ያጣል። በኢትዮጵያም ምንም አይነት ሰላም አይመጣም። ይህ ደግሞ በኦሮምያ ብቻ ሳይሆን ፤ በመላ ሃገሪቱ ነዉ። ምክንያቱም ባለስልጣናቱ ስለተከሰተዉ ነገር አዉቀዉ ማኅበረሰቡን እየዋሹ በመሆኑ ነዉ ።»

መንግሥት በዚህ አደጋ 56 ሰዎች ሞተዋል በማለት ሦስት የኃዘን ቀን ደንግጎ ጉዳዩን በዚህ ያብቃ ቢመስልም ፤   ለኛ ግን ጉዳዩ አላበቃም። ይህ ሁሉ መጣራትና ይፋ መሆን ይኖርበታል ሲሉ ዴልዩስ አክለዋል።  

ትናንት ይፋ በሆነዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ጉዳዩን ዳግም ለኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚያሳስቡ እንዲሁም ለጀርመን ብሎም ለአዉሮጳ መንግሥታት ማሳወቅ እንደሚፈልጉ የገለፁት የድርጅቱ የአፍሪቃ ተጠሪ የሟች ቤተሰቦች አሁንም የዘመዶቻቸዉን የአሟሟት እንዴትነት ከሁለት ወራት በኋላ ዛሬም መልስ እየጠበቁ መሆናቸዉን ገልፀዋል። በሌላ በኩል መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ፖሊሶችን በማሰልጠን ለኢትዮጵያ እገዛ እንደሚያደርጉ ስለገቡት ቃል   ዑልሬሽ ዴልዩስ የሚከተለዉን አስተያየት ሰጥተዋል።    

« የጀርመን መንግሥት የኢትዮጵያን ሁኔታ በጥንቃቄ እየተመለከተዉ መሆኑን አይተናል። ለምሳሌ የጀርመን መንግሥት በአሁኑ ወቅት በጀርመን የመኖርያ ፈቃድ ያላገኙና ወደመጡበት መመለስ ያለባቸዉ ዜጎች ለመመለስ ከኢትዮጵያና ከመንግሥቱ ጋር ዉል መፈፀም ይቻል አይቻል እያጤነ ነዉ። በኢትዮጵያ ያለዉ ወቅታዊዉ የሰብዓዊ መብት ይዞታ አሳሳቢ መሆኑ የሚታወቅ ነዉ። በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያለዉ አመኔታ  ከማንኛዉም ጊዜ እያሽቆለቆለ መጥቶአል። እና በበኩላችን ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ለባለስልጣናት ግልፅ እያደረግንነዉ ምክንያቱም ፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በይፋ የተነገረዉ ሁሉ እዉነታ ማለት እንዳልሆነ ግልጽ እያደረግን ነዉ»     

Ulrich Delius GfbV-Kampagne zum Klimawandel 14. 12. 2006
ምስል presse/GfbV

እንድያም ሆኖ ከጀርመን በኩል በኢትዮጵያ የተደላደለና የተስተካከል የፖለቲካ ሁኔታ እንዲኖርና ሰላም እንዲሰፍን  ፍላጎት እንዳለ ዑልሬሽ ዴሊዩስ ሳይገልፁ አላለፉም። በሃገሪቱ ሰላም መስፈኑ ደግሞ ከኦሮምያ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም የሚሰደደዱትን ሰዎች መጠን ይቀንሳል ሲሉ ተናግረዋል። እንዲያም ሆኖ በሃገሪቱ የሞቱና የጠፉ ሰዎች እንዴትነት መልስ ሊሰጠዉ ይገባል ሲሉ ዳግም አሳስበዋል።

«በኦሮምያ የሚገኙ ማኅበረሰቦች በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩና የጠፉ፤ ቤተዘመዶቻቸዉ የት እንደደረሱ ለማወቅ የመንግሥት ባለስልጣናትን መልስ እየጠበቁ ነዉ። የጠፉት ሰዎች ሞተዉ ነዉ ? ለሞቱት ሰዎች ተጠያቂዉስ ማን ነዉ እያሉ ነዉ። ይህ ደግሞ ሕግን መሠረት ያደረገ ጥያቄ ነዉ»

ከአዉሮጳ ጉብኝት በኋላ ከትናንት በስትያ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ አዲስ አበባ ዉስጥ የተያዙት  ስለተያዙት የኦሮሞ ፌዴራሲስት ኮንግረስ መሪ ዶክተር መረራ ጉዲና ጉዳይ እንዳሳሰባቸዉ የተናገሩት ዑልሪሽ ዴሊዩስ የአዉሮጳ ሕብረት ስለ ፖለቲከኛዉ መታሰር  በተመለከተ ተቃዉሞዉን ማሰማት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።  መንግሥትን በመቃወም ምንም አይነት ፖለቲካዊ አስተያየትን መስጠት የማይቻል ከሆነ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ምንም አይነት የጋራ ሥራም የፍልሰት ጥቃቄዎችን በጋራ ማንሳት እንደማይቻል ተናግረዋል።  

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ