1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራን የኑክልየር መርሐ-ግብር ስምምነት ምላሽ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 8 2007

ከአሜሪካና አጋሮቿ ከኢራን ጋር የገቡትን ለአመታት የዘለቀ ፍጥጫ ቪየና- ኦስትሪያ ላይ በስምምነት ቋጭተው ለአዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ሲዘጋጁ እስራኤል አዲስ ወዳጅ አበጅታለች። ሳዑዲ አረቢያ እና የባህረ ሰላጤው አገራት። የኢራን የኑክልየር መርሐ-ግብርን አስመልክቶ የተፈረመው ስምምነት አይሁዳውያንንና አረቦችን አወዳጅቷል።

https://p.dw.com/p/1Fz7l
Atomverhandlungen mit Iran in Wien
ምስል picture alliance / landov

[No title]

ቪየና-ኦስትሪያ ላይ የልዕለ ኃያሏ አሜሪካን ተደራዳሪዎች ከሩሲያ፤ፈረንሳይ፤ቻይና፤ታላቋ ብሪታኒያ፤ጀርመንና የአውሮጳ ህብረት አቻዎቻቸው ጋር ያደረጉትን የኢራን የኑክልየር መርሐ-ግብር ስምምነት ሲያጠናቅቁ ከፊታቸው ላይ ታላቅ ፈገግታ ታይቶ ነበር። ስምምነቱ በመፈንቅለ--መንግስት ሙከራ፤እገታ፤ሽብርተኝነትና ማዕቀብ ቅርቃር ውስጥ የገባውን የአሜሪካና የኢራን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ አዲስ ጎዳና ሊወስድ ይችላል ተብሎለታል።ኢራንን ከኑክልየር ጦር መሳሪያ ባለቤትነት የሚከለክለው ይህ ስምምነት ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በስልጣን ዘመናቸው ካከናወኗቸው ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች አንዱ ቢባልም ከትችት አላመለጠም።

የባራክ ኦባማ ተቀናቃኝ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ቀዳሚ ናቸው። ለጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ይህ ስምምነት «ታላቅ ታሪካዊ ስህተት» ነው።

Iran Flagge
ምስል privat

«የኢራን እስላማዊ ወታደራዊ መንግስት የተጣሉበት ማዕቀቦች ሁሉ ስለሚነሱ የኔክሌር የጦር መሳሪያ ባለቤት መሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ የሚያገኘው በ100 ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ሽብርተኝነቱን እና ትንኮሳውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ያደርገዋል።»

ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ተቺዎች የመጫዎቻ ካርዳቸውን ተነጠቁ ሲሉ ተናግረዋል። ኔታንያሁና የሬፐብሊካን ፓርቲ አባላት ግን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስምምነቱ ከማጣጣል ወደ ኋላ አላሉም። የሬፐብሊካን ፓርቲ አባልና የአሜሪካን ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ጆን ቤነር ስምምነቱ «አደገኛ» ላሉት የኢራን መንግስት «የኑክልየር ጦር መሳሪያ ባለቤት ሊያደርግ የሚችል በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር የሚሰጥ» ሲሉ ተችተዋል።

አሜሪካና አምስቱ ሃያላን ሃገራት ከኢራን ጋር ለመስራት በመወሰናቸው ኔታንያሁ ከወደ ሳዑዲ አረቢያ፤ዮርዳኖስና የባህረ ሰላጤው ሃገራት ያልተገመተ አጋርነት አግኝተዋል እየተባለ ነው። ይህ ከሆነ የአረቦችና አይሁዳውያን አጋርነት ይህ በታሪክ የመጀመሪያ ሳይሆን አይቀርም። የባህረ ሰላጤው ሃገራትኢራን የተጣሉባት ማዕቀቦች ሲነሱላት በሶርያ፤ኢራቅና የመን የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት ታጠናክራለች የሚል ስጋት አላቸው ተብሏል።

የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ግን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትርም ይሁን ከባህረ ሰላጤው ሃገራት በተቃራኒ ስምምነቱ በቀጠናው ሰላም ያሰፍናል የሚል እምነት አላቸው።

«በዚህ ድርድር ውስጥ ለ 10 አመታት እንደዘለቀ ሰው መካከለኛው ምስራቅንና መላውን ዓለም የበለጠ የሚያረጋጋ ስምምነት ላይ በመድረሳችን ደስተኛ ነኝ።»

Netanjahu Israel Schiff Iran Raketen M 302
ምስል Jack Guez/AFP/Getty Images

ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ስምምነቱን በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አቅርበው መጽደቅ ይኖርበታል። ፕሬዝዳንቱ ገና ካሁኑ ስምምነቱ በሬፐብሊካኖች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝላቸው ማግባባት ጀምረዋል። ፕሬዝዳንቱ ከኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በዚህ ስምምነት ዋንኛ ትኩረታቸው ኢራን የኑክልየር የጦር መሳሪያ እንዳይኖራት ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ስምምነት መሰረት ኢራን የተጣሉባት ማዕቀቦች በሂደት የሚነሱላት ይሆናል። በተለይ በስምምነቱ የቀረቡትን መሰረታዊ መርሆዎች ካከበረች በኃይልና የገንዘብ ተቋሞቿ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች በዚህ ዓመት ሊነሱ ይችላሉ።ኢራን የተስማማችባቸውን ነጥቦች ከጣሰች ግን ማዕቀቦቹ መመለሳቸው አይቀርም። አገሪቱ ከአቶሚክ ጋር የተገናኙ ተተኳሾችም ይሁን ፈንጂዎች ማምረት ባይፈቀድላትም ቴክኖሎጂውን በአነስተኛ መጠን ለሰላማዊ ግልጋሎት የምትጠቀምበት እድል ይኖራል ተብሏል።

ኢራናውያን ለድጋፍ አደባባይ የወጡለትን ስምምነት ፕሬዝዳንቱ ሃሳን ሩኻኒ ለአገሪቱ የአዲስ ምዕራፍ ብስራት ብለውታል።ፕሬዝዳንቱ አገራቸው ከምዕራባውያን ልዕለ ሃያላን ጋር የተፈራረመችው ስምምነት ለዓመታት የዘለቀውን ኢ-ፍትሃዊነት፤ስህተትና ውንጀላ ያስቀራል ብለዋል። ሃሳን ሩኻኒ ስምምነቱን ሁለቱም ወገኖች ተግባራዊ ሊያደርጉት እንደሚገባም አሳስበዋል።

«ይህ የሁለትዮሽ ስምምነት ነው። በዚህም መሰረት ወደ መጨረሻው ስምምነት ተሸጋግረናል። የስምምነቱ አተገባበር ከሁለቱም ወገን ነው። እነሱ ለስምምነቱ ታማኝ ከሆኑ እኛም እኛም ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ እንሆናለን


እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ