1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራን ምርጫ ዉዝግብና የኻሚኔይ ንግግር

ዓርብ፣ ሰኔ 12 2001

የበላይ መሪ አያቶላሕ ኻሜይኔ «ሥሕተት» ያሉት ጥፋት ሊፈፀም እንደሚችል በርግጥ አልካዱም።ይሁንና የአስራ-አንድ ሚሊዮን ያሕል ሕዝብ ድምፅ ለማጭበርበር የሚመች ቀዳዳ ግን በኢራን የምርጫ ሕግ የለም ባይ ናቸዉ

https://p.dw.com/p/IUqr
ኻሜኔይምስል picture alliance / landov

የኢራን የበላይ መሪ ዓሊ ኻሜኔይ ባለፈዉ ሳምንት የተደረገዉን ምርጫ ዉጤት በመቃወም የሚካሔደዉ ያደባባይ ሰልፍ እንዲያበቃ ጠየቁ።ኻሜኔይ አወዛጋቢዉ ምርጫ ከተደረገ ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ለሐገሪቱ ሕዝብ ባደረጉት ንግግር በምርጫዉ አሸንፈዋል ለተባሉት ለፕሬዝዳት ማሕሙድ አሕመዲነጃድ ድጋፋቸዉን ሠጥተዋል።የምርጫዉን ሒደት በበላይነት የሚቆጣጠረዉ የሐገሪቱ ከፍተኛ የሕግ ምክር ቤት ከተሰጠዉ ድምፅ የተወሰነዉን በድጋሚ እንደሚቆጥር ትናንት አስታዉቆ ነበር።የተቃዉሞ ሠልፉ ዛሬ ጋብ ብሎ ነዉ-የዋለዉ።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ።

በእስላማዊቷ ሪፐብሊክ የሰልጣን ተዋረድ ከፍተኛዉን ሥልጣን የያዙት አያቶላሕ ዓሊ ኻሜኔይ ለዘብተኛ ከሚባሉት የተቃዋሚ ሐይላት መሪዎች ይልቅ አክራሪ ፖለቲካዊ መርሕ የሚከተሉትን ፕሬዝዳት ማሕሙድ አሕመዲነጃድን ይደግፋሉ ሲባሉ ነበር።ዛሬ በርግጥ አደረጉት።አሉም «ምርጫ በእስላማዊቷ ሪፐብሊክ ሊጭበረብር አይችልም።»

«እስላማዊቷ ሪፐብሊክ አታታልልም።የሐገራችን የምርጫ ሕግ ማታለልም ሆነ ማጭበርበር እንዲፈፀም አይፈቅድም።በርጫ ሥርአታችን ማታለል ሊፈፀም አይቻልም።ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት ነዉ።አስራ-አንድ ሚሊዮን ድምፅ ሊጭበረበር አይችልም።»

በምርጫዉ የፕሬዝዳት አሕመዲነጃድ ዋነኛ ተፎካካሪ የነበሩት ሁሴይን ሞሳቪን ጨምሮ ለፕሬዝዳትነት ተወዳድረዉ የነበሩት ባለፈዉ አርብ የተደረገዉ ምርጫ ቢያንስ ስድስት መቶ አርባ ሥፍራ ተጭበርብሯል ባይ ናቸዉ።የምርጫዉ ዉጤት ባለፈዉ ቅዳሜ ከታወጀ ወዲሕ ለተቃዉሞ ሠልፍ አደባባይ የወጣዉ በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብም ይሕንን የተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ሐሳብ ይጋራል።

የበላይ መሪ አያቶላሕ ኻሜይኔ «ሥሕተት» ያሉት ጥፋት ሊፈፀም እንደሚችል በርግጥ አልካዱም።ይሁንና የአስራ-አንድ ሚሊዮን ያሕል ሕዝብ ድምፅ ለማጭበርበር የሚመች ቀዳዳ ግን በኢራን የምርጫ ሕግ የለም ባይ ናቸዉ።ያም ሆኖ የአብዮታዊ ላዕላይ ጠባቂ ምክር ቤት የተሰኘዉ የኢራን የሕግ ጉዳዮች ወሳኝ አካል ኾሜኔይ «ስሕተት» ያሉት ችግር ለማጣራት መወሰኑን እንደሚደግፉት አስታዉቀዋል።

የምክር ቤቱ ቃል አቀባይ አባስ አሊ ካድኻሞዳኢይ ተቃዋሚዎቹ ያቀረቡትን ቅሬታ ምክር ቤቱ መምርመሩን አስታዉቀዋል።በቃል አቀባዩ መግለጫ መሠረት የምክር ቤቱ የመጨረሻ ዉሳኔም ነገ ይፋ ይሆናል።

«በምርጫዉ ሒደት ማጭበርበር ተፈፅሟል የሚለዉ ቅሬታ ሁለቴ በተደረገ ስብሰባ ተመርምሯል። ቅዳሜ የአብዮታዊዉ አስከባሪ አካል ከፍተኛ አባላት በድጋሚ ተሰብስበዉ የመጨረሻዉን ዉሳኔያቸዉን ያስታዉቃሉ።»
አያቶላሕ ኻሜኔይ ቅሬታ የቀረበበት ድምፅ ተፎካካሪ እጭዎች በሙሉ በሚገኙበት እንዲቆጠር ወይም እንዲጣራ ዛሬ ባደረጉት ንግግራቸዉ ጠይቀዋል።የኢራን ሕዝብ ግን አሉ አቶላሕ ፕሬዝዳቱን መርጧል።የምርጫዉ ዉጤት የሚገኘዉ ደግሞ ከድምፅ መስጪያ ሳጥን እንጂ ከአዉራ መንገድ አይደለም።
ኻሜኔይ ንግግር ከማድረጋቸዉ በፊት የምርጫዉን ዉጤት በመቃወም ካለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ ጀምሮ አደባባይ የወጣዉን ሕዝብ በግንባር ቀደምትነት የሚያስተባብሩት ሁሴይን ሞሳቪ ደጋፊዎቻቸዉ ዛሬ ሠልፍ እንዳይወጡ ጠይቀዉ ነበር።ከአደባባይ ሠልፉ ይልቅ ሕዝቡ በተቃዉሞ ሠልፍ መሐል የተገደሉ ወገኖቹን በየመሳጂዱ በመፀለይ እንዲያስታዉሳቸዉ-ሞሳቪ ጠይቀዋል።በዚሕም ርዕሠ-ከተማ ቴሕራን ዛሬ ተረጋግታ ነዉ የዋለችዉ።

በተቃሞ ሠልፈኞችና በፀጥታ አስከባሪዎች መካካል በተደረገ ግጭት በትንሹ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል።በመቶ የሚቆጠሩ ደግሞ ታስረዋል።አያቶላሕ ኻሜኔይ ከእንግዲሕ በተቃዉሞ ሠልፍ ሰበብ ለሚፈጠረዉ ደም መፋሰስ የሰልፉ አስተባባሪዎች ሐላፊነቱን እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል።


ሞሳቪ በተደጋጋሚ እንዳስታወቁት ተቃዉሟቸዉ በምርጫዉ አሕመዲነጃድ አሽነፉ መባሉን እንጂ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክን ሥርዓት አይደለም።የስርዓቱ የበላይ አያቶላሕ ኻሚኔይ አቋማቸዉን ካስታወቁ፥ ማስጠንቀቂያዉን ካሰሙ በሕዋላ ግን የሞሳቪ ቅሬታ-ተቃዉሞ በማን ላይ እንደሚሆን ቢያንስ እስካ ዛሬ ግልፅ አይደለም።

ነጋሽ መሐመድ/አርያም ተክሌ