1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሕአዴግ እቅድና ተቃዋሚ ፓርቲዎች

ማክሰኞ፣ መስከረም 25 2003

በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማስተናበር ከኢትዮጵያ ትልቁ ተቃዋሚ ፓርቲ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ ባጭሩ) ግን በዉይይቱ ላይ እንዲሳተፍ አልተጋበዘም

https://p.dw.com/p/PV1F
ምስል AP

04 10 10

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የአምስት አመት የልማት እቅድ፥ የዉይይት ገብዣዉና ተቃዋሚ ፓርቲዎች።የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዲግ የዕድገትና «ትራስፎርሜሽን» በሚል አማርኛ-እንግሊዝኛ ቅይጥ ቋንቋ በሰየመዉ እቅዱ ላይ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ከተወሰኑት ጋር ለመወያየት ጋብዟል።የግብዣ-ዉይይቱ አላማ፥ የተጋበዙና ያልተጋበዙ ፓርቲዎች ማንነት፥ የመጋበዝ-አለመጋበዛቸዉ ምክንያት ያፍታ ዝግታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።
አዲስ የተመረጡት የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአዲሱ ዘመን አዲስ ሥራ-ስብሰባቸዉን ዛሬ ጀምረዋል።ከአንድ በስተቀር ሁሉንም የምክር ቤት መቀመጫዎች አባልና ደጋፊዎቹ የተቆጣጠሩት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢሕአዲግ) ለአምስት አመት የነደፈዉን የልማት እቅድ በምክር ቤቱ በቅርቡ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።በርካታ ተቃዋሚዎችና በተለይ በዉጪ የሚገኙ የኢኮኖሚ አዋቂዎች አጥብቀዉ የነቀፉት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን (የለዉጥ ብንለዉ ያስኬዳል) እቅድ በምክር ቤቱ ከመፅደቁ በፊት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በእቅዱ ላይ ለማወያየት ለነገ ሥብሰባ ጋብዟቸዋል።

አላማዉ፣-የኢሕአዴግ የዉጪና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሐላፊ አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸዉ እንዳሉት ሥለ እቅዱ ተቃዋሚዎች የሚሰጡትን አስተያየት ለማካተት ነዉ።

በዉይቱ ላይ እንዲሳተፉ ከተጋበዙት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ነዉ።የድርጅቱ የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ አቶ ያቆብ ልኬ እንደሚሉት የግብዣ ደብዳቤዉ አደናጋሪ ነዉ።ባያደናግር እንኳን-ድርጅቱ በዉይይቱ ላይ አይካፈልም።

በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማስተናበር ከኢትዮጵያ ትልቁ ተቃዋሚ ፓርቲ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ ባጭሩ) ግን በዉይይቱ ላይ እንዲሳተፍ አልተጋበዘም።ምክንያት-አንደገና አቶ ሴኩቱሬ።

የኦሮሞ ሕዝብ ብሔራዊ ፌደራላዊ ኮንግረስ መሪና የመድረክ ከፍተኛ ባለሥልጣን ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንደሚሉት ድርጅታቸዉ መጋበዝ አለመጋበዙ ትርጉም፥ እቅዱም ፋይዳ የለዉም።

በዚሕም ሰበብ መድረክ ተጋብዞ ቢሆን ኖሮ እንኳን-ፕሮፌሰር መረራ እንደሚሉት በዉይይቱ አይካፈልም ነበር።ከተጋበዙን መካካል ከመኢአድ በስተቀር ሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በነገዉ ዉይይት ላይ እንደሚካፈሉ ማረጋገጣቸዉን አቶ ሴኮቱሬ አስታዉቀዋል።
በዉይይቱ ላይ ይካፈላሉ ወይም ከቅድመ ሁኔታ ጋር ለመካፈል ፍቃደኛ ናቸዉ ከተባሉት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የተወሰኑትን በስልክ ለማነጋገር ያደረግነዉ ሙከራ አልተሳካልንም። የመድረክ ከፍተኛ ባለሥልጣን ፕሬፌሰር መረራ ጉዲና ግን የነገዉ ዉይይት «ኢሕአዴግ-ከኢሕአዴግ ጋር የሚያደርገዉ ነዉ» ባይ ናቸዉ።
በቅርቡ ናዝሬት ላይ የተደረገዉ የኢሕአዲግ አራተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ያፀደቀዉ የአምስት አመት የልማት እቅድ በጉባኤዉ ላይ እንደተወሳዉ የኢትዮጵያን መሠረታዊ ምጣኔ ሐብታዊ ችግሮችን የሚያስወግድ ነዉ።በተለይ ደግሞ እቅዱ ኢትዮጵያ በምግብ ራስዋን እንድትችል፥ አጠቃላይ የምጣኔ ሐብት እድገቷ በአመት በአማካይ እስከ አስራ-አምስት በመቶ ከፍ እንዲል የሚያደርግ እንደሆነ የኢሕአዲግ ባለሥልጣናትና ደጋፊዎቻቸዉ በሰፊዉ እየተናገሩ ነዉ።

መኢአድ ግን እቅዱን አይቀበለዉም።የድርጅቱ የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ አቶ ያቆብ ልኬ እንዳሉት ዝር ዝር ምክንያቱን ወደፊት ለሕዝብ ያሳዉቃል።ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ደግሞ ከዚሕም እልፍ ብለዉ እቅዱን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የዋለ በማለት አጣጥለዉ ነቅፈዉታል።

ገዢ-ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በልማት እቅዱ አይደለም ብሔራዊ መግባባት ከሚሉት መግባባት እንኳን አልደረሱም።የኢትጵያ የእድገትና የለዉጥ (ትራንስፎርሜሽን) የተሰኘዉ እቅድ-ግን በቅርቡ በምክር ቤቱ ፀድቆ የሐገሪቱ ሕጋዊ መርሕ ይሆናል።የገቢራዊነቱ እንዴትነትን በያኙ ግን ያዉ ጊዜ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።
ቃመ ሴኩቱሬ ጌታቸዉ፥ ፕ መረራ ጉዲና፥ ያቆብ ልኬ
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ