1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሕአዴግ «መተካካት» ና እንድምታዉ

ማክሰኞ፣ መስከረም 4 2003

ለዉጡ የወደፊቱን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ባንድ-ወይም በሌላ መልኩ መንካቱ አያጠራጥርም።ለዶክተር አረጋዊ በርሔ ግን ለዉጡ የቁልቁሊት ነዉ።

https://p.dw.com/p/PB65
«መተካካት»ምስል AP Photo
የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አባል ድርጅቶች ያደረጉና የሚያደርጉትን የአመራር ለዉጥ «መተካካት» ብለዉታል።የኢሕአዲግ መሪ፥አባል ደጋፊዎች እንደሚሉት ለዉጡ የየድርጅቶቹን በተናጥል፥ የግንባሩን በጥቅል አመራር በወጣቶች፥ የመተካቱ እቅድ ጅምር ነዉ።በገቢር የሆነ እና የሚሆ ነዉ ግን-በርግጥ አነጋጋሪ ነዉ። «መተካካቱ» እና እንድምታዉ የአዲሱ አመት-የመጀመሪያ ርዕሳችን፥ የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) መስራችና የቀድሞ ከፍተኛ መሪ ዶክተር አረጋዊ በርሔ ደግሞ የዛሬ እንግዳችን ናቸዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።

ዶክተር አረጋዊ በርሔ እንዳልነዉ ከሕዝባዊ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) መስራቾች አንዱ ናቸዉ።የድርጅቱ በጣሙን የጦሩ መሪም ነበሩ።አሁን ሥለ ኢሕአዲግ መሪዎች ማንነት፥ ሥለ ምግባር አለማቸዉ፥ ሥለ «መተካካቱ» እንዴትነት እና እድምታዉ ባጭሩ ሊነግሩን ነዉ።ግን የእሳቸዉ ፖለቲካዊ ማንነትና ዳራ ምንድነዉ? ከሕወሐት የተገለሉበት ሠበብ-ምክንያትስ።-«የአመራር ድክመት» ወይም አሁን እንደሚባለዉ «መተካካት» ሲባሉ ይስቃሉ።እና ምክንያት የሚሉትን ምክንያት ይናገራሉ።
               
ያኔ-ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ አይደለም በሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይም ዉስጥ ብዙም በማይታወቁበት ዘመን (በዶክተር) አረጋዊና በተባባሪዎቻቸዉ ላይ የተወሰደዉ አይነት እርምጃ-ዛሬም እየተፈፀመ ነዉ-ይላሉ።
              
ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) መሪዎች «ሊተካኩ» ከትናንት ጀምረዉ ጉባኤ ላይ ናቸዉ።የኢሕአዲግ ዋነኛ መስራች-ዘዋሪ ፓርቲም-ሕወሐት ነዉ።የሕወሐትም-የኢሐዴግም ሊቀመንበር በርግጥ አልተተኩም። ከሥራ-አስፈፃሚዉ የተወሰኑትን ግን በሌሎች ተለዉጠዋል።ለዉጡ የወደፊቱን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ባንድ-ወይም በሌላ መልኩ መንካቱ አያጠራጥርም።ለዶክተር አረጋዊ በርሔ ግን ለዉጡ የቁልቁሊት ነዉ።
                     

የመተካካቱ ሒደት የሕወሐት መስራችና የቀድሞ መሪ አቶ ስብሐት ነጋን ከፓርቲዉ አመራር በጡረታ አፈናጥሯል።ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ-የዉጪ ጉዳይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን የያዙት አቶ ስዩም መስፍን፥ የሕወሐት መስራችና የፌደራል ጉዳይ ሚንስትር አቶ አባይ ፀሐይዬ፥ እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በነበሩበት ዘመን ከነዋሪዉ መልካም ስም አትርፈዉ የነበሩት አቶ አርከበ ዕቁባይን ከስራ-አስፈፃሚነት ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዝቅ አድርጓል።

ሌሎችን ደግሞ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት አሰናብቷል።ዶክተር አረጋዊ-የዚሕን ለዉጥ ምክንያት ግላዊ ወይም ቤተሰባዊ-ጥቅም እና ፍፁም አዎ-ባዮችን መሰብሰቢያ ያደርጉታል።
                  
የሕወሐት መሪ-አልተተኩም።የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) መሪ አቶ አዲሱ ለገሠ ግን በአቶ ደመቀ መኮንን (የትምሕርት ሚኒስትሩ) ተተክተዋል።ከብአዴን ነባር መሪዎች አቶ ተፈራ ዋልዋላ-ሥም ከድርጅቱ የሥራ-አስፈፃሚ፥ ከማዕከላዊ ኮሚቴዉም ዝር ዝር ዉስጥ የለም።የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራዊያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) መሪ አቶ አባዱላ ገመዳ ደግሞ በአቶ አለማየሁ አቶምሳ ተተክተዋል።ዶክተር አረጋዊ ሥለ ሁለቱ ድርጅቶች እና ሥለ መተካካቱ ሁለት ነገሮችን ያነሳሉ።
                         
ኢትዮጵያን ላለፉት ሃያ-አመታት የመሩት ሐይላት ሥልጣናቸዉ ቀስ በቀስ ዘመኑ የሚጠይቀዉን እዉቀት፥ አቅምና ብቃት ላላቸዉ ወጣቶች እንደሚያስረክቡ መናገር ከጀመሩ-ሰወስት አመት አለፈ።ከአራቱ የኢሕአዴግ ድርጅቶች ሰወስቱ ባለፈዉ ሳምንት ይፋ ያደረጉት ለዉጥም የዚያ ሥልጣን የማስረከቡ ሒደት ጅምር መሆኑን አስታዉቀዋል።ዶክተር አረጋዊ በተጨባጭ የታየዉ ሌላ ነዉ ባይ ናቸዉ።
                    
ዘመኑ-አዲስ ነዉ።2003 ።ምክር ቤቱም አዲስ ነዉ።ኢሕአዲግ ብቻ።መሪዎቹ የአመራር መርሕ፥ ሥልት፥ ብልሐታቸዉ ግን «አረጌ» ባይባል እንኳን አዲስ ሊባል አለመቻሉ ነዉ-የትናንት ዛሬዉ አንድነት።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያስመን።
Interv.Mit Dr.Aregawi Berhe
Negash Mohammed