1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍቃኒስታን ጉባኤና የጀርመን ዕቅድ

ረቡዕ፣ ጥር 19 2002

ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ለየተዋጊዉ እንዲከፈል የሚሹትን የገንዘብ መጠን አላስታወቁም።እቅዳቸዉ ግን በሌሎቹ የነገ ጉባኤተኞች ይደገፋል ብለዉ ሳያምኑ አልቀሩም

https://p.dw.com/p/LiDB
የጀርመን ወታደሮች-አፍቃኒስታንምስል AP

በአፍቃኒስታን የወደፊት እጣ-ፈንታ ላይ የሚመክር አለም አቀፍ ጉባኤ ነገ ለንደን ዉስጥ ይጀመራል።የጀርመን መንግሥት ከጉባኤዉ በፊት ትናንት ወደ ከስምንት መቶ በላይ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ አፍቃኒስታን ለማዝመት አቅዷል።ጀርመን ፈተና ለገጠመዉ ለአፍቃኒስታን ተልዕኮዋ አዲስ ሥልት እያፈላለገችም ነዉ።ተጨማሪ ሠራዊት ከማዝመት ሌላ የአፍቃኒስታን ፀጥታ አስከባሪዎችን ሥልጠና ማሻሻል እና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ ባለፈዉ ሳምንት ያቀረቡት ሐሳብ የሐገሪቱን ፖለቲከኞች እያነጋገረ ነዉ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ለዘብተኛ ታሊባኖች ዉጊያ እንዲያቆሙ ገንዘብ ይከፈላቸዉ የሚለዉ ሐሳባቸዉ የዶቼ ቬለዉ ዘጋቢ ኡቨ ሔስለር እንደተከታተለዉ የተለያየ ስሜት ነዉ-የፈጠረዉ።ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል

«ለዘብተኛ» የሚባሉት የታሊባን ደፈጣ ተዋጊዎች ዉጊያ አቆመዉ ሠላማዊዉን ሕዝብ «እንዲቀየጡ» ገንዘብ የሚከፍላቸዉ ልዩ ተቋም ይመስረት የሚለዉ ሐሳብ ከለንደኑ ጉባኤ አብይ ርዕሶች አንዱ ነዉ።ሐሳቡን ከሚደግፉት የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ አንዱ ናቸዉ።

አፍቃኒስታን የሠፈረዉ አለም አቀፍ የአፍቃኒስታን አረጋጊ ሐይል (ISAF-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) ባልደረቦች ግን አንድ አባባል አላቸዉ።የታሊባንን ተዋጊ መከራየት ትችለለሕ-መግዛት ግን እእ-የሚል።-አይነት።ቬስተርቬለ ባንፃሩ የማይቻል የሚመስለዉ ይቻላል አይነት ባይ ናቸዉ።

«መርሐ-ግብሩ የሚያተኩረዉ ርዕየተ-አለማዊ እምነት ባላቸዉ አክራሪ አሸባሪዎችን ላይ አይደለም። የሽምቅ ዉጊያዉን በመቀላቀላቸዉ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያገኙትን ተከታዮችን እንጂ።የኛ የመዉጪያ መርሐ-ግብር እነዚሕ ማሕበረሰቡን ዳግም እንዲቀየጡ ማድረግ ነዉ።»

Deutschland Bundestag Haushalt Guido Westerwelle
ዉ ጉ ቬስተርቬለምስል picture alliance / dpa

ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ለየተዋጊዉ እንዲከፈል የሚሹትን የገንዘብ መጠን አላስታወቁም።እቅዳቸዉ ግን በሌሎቹ የነገ ጉባኤተኞች ይደገፋል ብለዉ ሳያምኑ አልቀሩም።አብዛኞቹ የጀርመን ጋዜጦች ግን በየርዕሠ-አንቀፆቻቸዉ ከታሊባን ደፈጣ ተዋጊዎች ይልቅ የአፍቃኒስታን ፖሊሶችና ወታደሮች በሙስና የተዘፈቁ ናቸዉ በማለት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉን ሐሳብ ክፉኛ ነዉ-የተቹት።

የዋነኛዉ ተቃዋሚ የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ (SPD) አባላትም ሐሳቡን በጥርታሬ ነዉ-የተመለከቱት።የፓርቲዉ መሪ ሲግማር ጋብርኤል እንዳሉት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ሊያስጨንቃቸዉ የሚገባዉ የጀርመን ወታደሮች ከአፍቃኒስታን የሚወጡበት ሥልት እንጂ የታሊባን ደፈጣ ተዋጊዎች የመዉጪያ መርሐ-ግብር ሊሆን አይገባም።

«እኛ ማሰብ የሚገባን በሚመጣዉ አመት ከሚጀመረዉ የአሜሪካ ወታደሮችን የማስወጣቱን እቅድ ልንጋራ ሥለምንችልበት ነዉ።ከዚሕ ለመድረስ ግን የወታደራዊዉን እርምጃ እንደ አማራጭ ማየቱን አቁመን የአፍቃኒስታንን የፖሊስና የፀጥታ አባላት በማሰልጠኑ ላይ ይበልጥ ማተኮር አለብን።»

ያም ሆኖ የቬስተርቬለ ሐሳብ የመራሔተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ድጋፍ ሳያገኝ አልቀረም። መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት ገንዘብ የሚከፍል ተቋም ይመሥረት የሚለዉ ሐሳብ የጀርመን መንግሥት ለለንደኑ ጉባኤ ከሚያቀርባቸዉ ርዕሶች አንዱ ነዉ።ጀርመን ከዚሕም በተጨማሪ ወደ አፍቃኒስታን ተጨማሪ ወታደሮች ለማዝመትም አቅዳለች።

የበርሊኑ የፖለቲካና የሳይንስ ጥናት ተቋም ሲታ ማአስ እንደሚሉት ጀርመን ለአፍቃኒስታን የምታወጣዉ ተጨማሪ ገንዘብ (ከጦሩ ይልቅ) በልማቱ ተጨባጭ ዉጤት ለሚያመጣ የልማት መስክ መዋል አለበት ባይ ናቸዉ።

«እኔ የምመከረዉ ጀርመን ለአፍቃኒስታን የምታወጣዉ ገንዘብ የደሐዉን የአፍቃኒስታን ሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል በሚረዱ የምጣኔ ሐብት መስኮች ላይ መዋል አለበት እያልኩ ነዉ።ለታሊባን ተከታዮች የተሻለ የሥልጠና፥ የትምሕርና፥ የሥራ እድል መፍጠር እና ከዚሁ ጋር አክራሪ ታሊባኖች እንዳይበቀሏቸዉ መከላከል ብሩሕ ተስፋ ይፈጥርላቸዋል።»

Taliban in Afghanistan
የታሊባን ተዋጊዎችምስል dpa

መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት ዩናይትድ ስቴትስ፥ ጃፓን እና ብሪታንያም የአፍቃኒስታን መንግሥት የ«ሰላምና እንደገና የመቀየጥ ገንዘብ» ያለዉን አይነት ታሊባኖችን የመደጎሚያ ተቋም ለመመስረት ማቀዳቸዉን እየተዘገቡ።በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለመስጠት ቃል ይገባሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ዑቨ ሄስለር

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ