1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍቃኒስታን ምርጫ ዉጤት ዉ ዝግብ እና አለም የአቀፉ ጦር ጥቃት

ሰኞ፣ ጳጉሜን 2 2001

በአንዳድ አካባቢዎች የምርጫ ጣቢዎች ጨርሶ-አልተከፈቱም ነበር።መራጭ አልነበረም።ለዚያ ምርጫ የተላኩት ኮሮጆዎች ግን ካርዛይ ስም-ፎቶ ላይ ምልክት በተደረገባቸዉ የምርጫ ካርዶች ተሞልተዉ ተመልሰዋል።

https://p.dw.com/p/JUSm
ምስል AP

07 09 09

የአፍቃኒስታኑ ፕሬዝዳንት ሐሚድ ካርዛይ ላለፉት ሥምንት አመታት የያዙትን ሥልጣን እንደያዙ የመቀጠል አለመቀጠላቸዉ ፋይዳ-ጉዳት ከአፍቃኖች አልፎ-ሃያሉን ዓለም ሲያነጋግር፥አፍቃኒስታን የሠፈረዉ የአለም ሐያላን ጦር፥ የዉጊያ ሥልት፥ የእስካሁን ዉጤቱ፥ የሚወስደዉ እርምጃ ሠላም ለማስፈን የሚኖረዉ ጉዳት-ጥቅም ያወዛግብ ይዟል።ጤና ይስጥልጥ እንደምን ዋላችሁ።የአፊቃኒስታን ምርጫ ዉጤት ዉዝግብ፤ አሸባሪ-ደፈጣ ተዋጊዎችን ለማጥፋት የዘመተዉ ጦር እርምጃ ያሳደረዉ ሥጋት ጥልቀት፥ የእንድምታዉ እንዴትነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ-አብራችሁኝ ቆዩ።

ሐሚድ ካርዛይ ብዙዎች እንደሚሉት፥ በገቢር እንደሚታየዉም ከአፍቃኒስታን ርዕሠ-ከተማ ከካቡል ከንቲባነት ብዙም የሰፋ የአስተዳድር መዋቅር፥ የተማከለ-መንግሥት፥ ሥልጣን በርግጥ የላቸዉም። ካርዛይ ከንቲባም ተባሉ እንደ ሕጋዊዉ አሰራር፥ በይፋ እንደሚታወቀዉ አጠራርም የአፍቃኒስታን እስላማዊት ሪፐብሊክ ፕሬዝዳት ሥልጣናቸዉን በዋዛ ይለቃሉ ብሎ ያሰበ-ከነበረ እሱ በርግጥ ተታሎ ነበር።

የዚያኑ ያክል ከሁለት ሳምንት በፊት በተደረገዉ ምርጫ ካርዛይን በግንባር ቀደምትነት የተፎካከሩት አብዱላሕ አብዱላሕ በቀደም እንዳሉት ከታሕሳስ 2001 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የጊዚያዊ መስተዳድር ሊቀመንበር፥የሽግግር ፕሬዝዳት እና ተመራጭ ፕሬዝዳት የሚል ማዕረግ የተቀያየራላቸዉ በሳል ፖለቲከኛ-በምርጫ አሸንፉ ቢባል አላምንም ባይ ማግኘት በከበደ ነበር።
«በትክክለኛ የምርጫ ሒደት ካርዛይ ማሸነፋቸዉን ትቀበላለሕ ወይ ተብዬ ካንድ ወር በፊት ተጠይቄ ቢሆን ኖሮ -መልሴ አዎ-የሚል በሆነ ነበር።ይሕ ምንም አያጠያይቅም።አኔና የአፍቃኒስታን ሕዝብ በመንግሥት የሚፈፀመዉን ለከት የለሽ የማጭበርበር ምግባር ካየን በሕዋላ አሁን ግን ካርዛይ አሽነፉ ቢባል አንቀበለዉም።ትክክለኛ የምርጫ ሒደት ያስፈልገናል።የምርጫዉ ሒደት ትክክለኛ ከሆነ ደግሞ እሳቸዉ (ካርዛይ) አያሸንፉም።»

እዉቁ የአፍቃኒስታን ፖለቲከኛ ሥልጣናቸዉን በዋዛ-እንደማይለቁ ቢታወቅም ዘመነ-ሥልጣናቸዉን ለማራዘም የፈፀሙና-የሚያፈፅሙትን እስከማስፈፀም ይደርሳሉ ብሎ መገመት ከባድ ነበር።ሰዉዬዉ ግን አደረጉት።በአንዳድ አካባቢዎች የምርጫ ጣቢዎች ጨርሶ-አልተከፈቱም ነበር።መራጭ አልነበረም።ለዚያ ምርጫ የተላኩት ኮሮጆዎች ግን ካርዛይ ስም-ፎቶ ላይ ምልክት በተደረገባቸዉ የምርጫ ካርዶች ተሞልተዉ ተመልሰዋል።

ኒዮርክ ታይምስ የተሰኘዉ የአሜሪካ ጋዜጣ የጠቀሳቸዉ አንድ አሜሪካዊ ዲፕሎማት እንዳሉት ካጠቃላዩ የምርጫ ጣቢያዎች አስራ-አምስት በመቶ-ያሕሉ ድምፅ አልተሰጠባቸዉም።ዝግ ነበሩ።አንዳድ አካባቢዎች በተለይ በምሥራቅና ደቡባዊ አፍቃኒስታን ስምንቶ መቶ ያሕል የምርጫ ጣቢያዎች የነበሩት ወረቀት ላይ ብቻ ነበር።

በተጨባጭ ሳይኖሩ-ወረቀት ላይ ለተመሰረቱት የምርጫ ጣቢያዎች፥ ኮሮጆ ተልኮ፥ የድምፅ መሲያጪያ ካርድ ተሞልቶባቸዉ ተመልሰዋል።የሉክዘምበርጉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዬን አሰልቦርን ትናንት እንዳሉት ደግሞ የአንድ መራጭ ድምፅ በሰማንያ የተባዛበትም ሥፍራ አለ።
«ባንድ መንደር ተመዝግበዉ የነበሩት መራጮች ሃያ-አምስት ነበሩ።በምርጫ ኮሮጆዉ ዉስት የተገኘዉ ግን ሃያ-ሺሕ የድምፅ መስጫ ካርድ ነዉ።ይሕ ሊሆን አይችልም።»

ሆነ።የካርዛይ መንግሥት የሚቆጣጠረዉ ብሔራዊዉ አስመራጭ ኮሚሽን የተቃዋሚዎችን ቅሬታ፥ የዉጪ ታዛቢዎች ሥሞታ መስማት የሚሻ አይመስልም።አፍቃኒስታን በበላይነት የሚቆጣጠረዉ ሐያል-አለምም የብርታኒያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ጎርዶን ብራዉን የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ትናንት እንዳሉት-የአፍቃኒስታንን ሠላምና ፀጥታ ለማስከበር ሌላ ጉባኤ መጥራትን እንጂ ለምርጫዉ ሒደት ዉጤቱ ፍትሐዊነት ብዙ የተጨነቀ አይመስልም።

«የወደፊቱ ተልዕኳችን በሚኖረዉ ገፅታ ላይ ለመነጋገር የሚቀጥለዉ የአፍቃኒስታ መንግሥትን፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥ ኔቶ እና ቁልፍ ሚና ያላቸዉ ሐገራት የሚሳተፉበት ጉባኤ መደረጉን እኛ ሁለታችንም እንደግፈዋለን።እና በነዚሕ በሰወስቱ መስኮች በፀጥታ፥በአስተዳደርና በልማት ያለዉን ለመገምገም፥የአፍቃኒስታን ሕዝብ፥ የጦር ሐይሉ፥ የፖሊስ ሠራዊቱ፥ የሲቪክ ማሕበረሰብ ተቋማቱ፥ ለወደፊቱ ላቅ ያለ አስተዋፅኦ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ለማጤን እና ሥልታችንን ገቢራዊ ለማድረግ በቂ ሐብት መኖሩን (ለማጥናት ጉባኤዉ ጠቃሚ ነዉ)።»

አፍቃኒስታን የሸመቁ አሸባሪ-ደፈጣ ተዋጊዎችን ለመዋጋት የወታደሮቹን ሕይወት-ደም አካል የሚገብረዉ፥ የሕዝቡን ሐብት የሚከሰክሰዉ፥ ለካርዛይ መንግሥት፥ ለምርጫዉ ሒደት፥ ቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር የሚያፈሰዉ አለም የእስከዛሬ አለማዉ በርግጥ ሠላምን ማስፈን፥ ዲሞክራሲ ብልፅግናን ማስረፅ ከነበረ አልሰራም።

የታሊባኖች ደፈጣ ተዋጊዎች ዉጊያ፥ የአጥፍቶ ጠፊዎቹ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ፥ አድማሱን እያሰፋ፥ የሚያደርሰዉ ጥፋት እያየለ ነዉ።ያለ ብዙ አደጋ ችግር አለፈ እየተባለ ብዙ የተነገረለት ምርጫ ከተደረገበት እለት እስከ ትናንት በተቆጠረዉ አስራ-ሰባት ቀናት ዉስጥ ብቻ የአፍቃኒስታንን የስለላ ድርጅት ምክትል ሐላፊን ጨምሮ አምስት መቶ ያሕል ሰዉ ተገድሏል። ካለፈዉ ጥር እስካሁን ብቻ አንድ መቶ ሰማንያ አራት የአሜሪካ፥ ከሃያ-የሚበልጡ የሌሎች ሐገራት ወታደሮች ተገድለዋል።

የታሊባን መወገድን ያኔ ለአብዛኛዉ አፍቃኒስታናዊ የጥሩ ዘመን ጅምር፥የነፃነት ብልጭታ፥ የዲሞክራሲ፥ የብልፅግና ትልቅ ተስፋ ነበር።ባለፉት ስምንት አመታት ከደፈጣ ተዋጊዎች ጥቃት ንረት፥ ከመንግሥት ጦር ግፍ-በደል፤ ከካራዛይ መንግሥት ብልሹ አስተዳደር፥ከአሜሪካ መራሹ-ጦር የስሕተት ጥቃት ሌላ ትንሽ ወይም ምንም ያየዉ ሕዝብ የዛሬ ፀሎት ምኞቱ የተስፋዉ እዉንነት አይደለም።-ዛሬን በሕይወት መዋል-ማደሩ እንጂ።

የካርዛይ መንግሥት ባለሥልጣናት፥ዘረፋና ማጭበርበር ጦሩና የፖሊስ ሐይሉ የሚፈፅሙት በደል-እንግልት፥ የዉጪዉ ሐይል በስሕተት እና በጥርጣሬ ግን በተደጋጋሚ የሚያደሱት ግድያና እስራት ሥራ አጥነትና ድሕነት ለሰላም፥ ዲሞክራሲ ብልፅግና ተስፋ አድርጎ የነበረዉን ሕዝብ እያሸማቀቅ-አቅም ያለዉን እያሸፈተ ከታሊባን እየቀየጠዉ ነዉ።

የአሜሪካ ጦር ሐይሎች የጥምር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞች ሊቀመንበር ጄኔራል ማይክል መለን ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት አብዛኞቹ የታሊባን ደፈጣ ተዋጊዎች ገቢ ለማግኘት ወይም ምርጫ በማጣት ሸማቂዉን ቡድን የተቀየጡ እንጂ በፊት እንደሚታመነዉ ሐይማኖት ወይም የርዕዮተ-አለም ተገዢዎች አይደሉም።
የፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ መስተዳድር ለአፍቃኒስታን የቀየሰዉ አዲስ ሥልት፥ የጦር አዛዦቹ ብልሐት ካጣብቂኝ ሳይወጣ፥ ለዲሞክራሲ ያለመዉ ምርጫ መጭበርበር፥ አለም አቀፉ ጦር የስሕተት ጥፋት መደጋገም የዚያን ሕዝብ መከራ ማብቂያ የለሽ አስመስሎታል።

ባለፈዉ ሰሜን አፍቃኒስታን ኩንዱዝ አካባቢ በሰፈረዉ የጀርመን እግረኛ ጦር አዛዦች ትዕዛዝ መሰረት የአሜሪካ የጦር አዉሮፕላኖች በጣሉት ቦምብ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል መባሉ ደግሞ የአለም አቀፉን ጦር የዘመቻ ቅንጅት አጠያያቂ አድርጎታል።ባለፈዉ አርብ ማንነታቸዉ በዉል ያልታወቁ ሰዎች ኩንዱስ አጠገብ የነበሩ ቦቴዎችን ዘርፈዉ ይነዳሉ።ባካባቢዉ የነበረዉ የጀርመን እግረኛ ጦር ቦቴዎቹን የሚነዱና ያሳፈሩት ሰዎች እንዲደበደቡ አየሜሪካን አየር ሐይል ይጠየቁ።

Afghanistan Verletzete in Kundus nach NATO Luftangriff
በኩንዱሱ ድብደባ ክሞት የተረፉትምስል AP

ተዕዛዝ ተፈፀመ በጀርመን ጦር ሐይል መግለጫ መሰረት ከሐምሳ-እስከ ሥልሳ፥ በአፍቃኒስታን ባለሥልጣናት ስሌት መሰረት ከአንድ መቶ-ሰላሳ-እስከ መቶ ሐምሳ የሚደርሱ ሰዎች አዲዮስ።
የጀርመኑ መከላከያ ሚስትር ፍራዝ ዮሴፍ-ዩንግ እንደሚሉት የተደሉት ሰዎች የታሊባን ደፈጣ ተዋጊዎች ናቸዉ።

«ለኛ የጦር አዛዦች ሁኔታዉ የታየዉ እነዚያ ቦቴዎችን ታሊባኖች የያዟቸዉ መሆኑ ነዉ።ይሕ ደግሞ ለኛ የጦር ሰፈርም ጭምር በጣም ግልፅ አደጋ ነበር።ታሊባኖች እንደሆነ ከተጣራ በሕዋላ የአየር ድብደባዉ ድጋፍ እንዲደረግ የተጠየቀዉ።»

የጀርመኑን መከላከያ ሚንስትር ማብራሪ የሰማዉ እንጂ ያመነዉ የለም።መራሔተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ራሳቸዉ ጉዳዩ ባስቸኳይ እንዲጣራ ጠይቀዋል።የአካባቢዉ ባለሥልጣናት እንዳረጋገጡት አብዛኞቹ ሟቾች ሰላማዊ ሰዎች ናቸዉ። የፈረንሳዩ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቤርናርድ ኩሽኔር ከሁለቱም ፈንጠር ብለዉ ድብደባዉ «ታላቅ ስሕተት» ብለዉታል።አቃኒስታን የሰፈረዉ አለም አቀፍ ጦር አዛዥ የአሜሪካዉ ጄኔራል ማክ ክርቲይስታል-ታማኝ እንሁን ይላሉ።

«እኛ በተቻለን መጠን ለአፍቃኒስታን ሕዝብ እና ለመላዉ አለም ሕዝብ ታማኝ ሆነን መገኘት ለኔ በጣም አስፈላጊ ነገር ነዉ።በርግጥ ማጣራቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁሉንም እዉነታዎች አናዉቃቸዉም፥ እኔም እራሴ አሁን እዉነታዎቹን በግልፅ አላዉቃቸዉም። ተገቢ ያልሆነ ማጠቃለያ ሰጥተን የምርመራዉን ሒደት ማወክም ተገቢ አይሆንም።ዛሬ ሆስፒታል ዉስጥ ካየሁት መገንዘብ የቻልኩት ግን እዚያ (በተደበደበዉ አካባቢ) የተጎዱ የተወሰኑ ሰላማዊ ሰዎች መኖራቸዉን ተገንዝቤያለሁ»

ከአለም-ሕዝብ፥ ከአፍቃኒስታን ሕዝብ ታማኝነት ማትረፍ የሚቻለዉ-በማለት አደለም ሆኖ በመገኘት እንጂ።ያልሰጠዉ ድምፅ እየታጨቀ፥ ባልመረጡዉ መሪ እየተገዛ፥ ካልፈለገዉ ጦርነት የሚማገድ ሕዝብ የሚያምን-የሚያድነዉን የሚያገኝበት ብልሐት-መጥናቱ፥ ዘመን መራቁ ነዉ-ሰቀቀኑ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

dw,Agenturen

ነጋሽ መሀመድ ፣ ሒሩት መለሰ