1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የአፍሪቃ የምርት አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የመከረው የሐዋሳ ስብሰባ

ረቡዕ፣ ጥር 15 2011

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በአፍሪካ አዲስ የምርት አቅርቦት ሰንሰለት ለመዘርጋት ያስችላል የተባለ የውውይት መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡ በውውይት መድረኩ ላይ የአህጉሪቱ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በአፍሪካ ያለውን የንግድና ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ለማሳደግ ይረዳሉ ያሏቸውን ምክረ ሀሳቦች አቅርበዋል፡፡

https://p.dw.com/p/3C3tj
Afrikanische Lieferkette
ምስል DW/Amharic

የአፍሪቃ የንግድ ትስስር

አፍሪካ ላለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመት በምጣኔ ሀብት ረገድ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት ተስኗት ቆይታለች፡፡ ለመዋቅሩ ተግባራዊ አለመሆን በተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች የተለያዩ ምክንያቶች ሲጠቀሱ ይደመጣል ፡፡ በአፍሪካዊያን መካከል የምጣኔ ሀብት መስተጋብር አለመኖር ከምክንያቶቹ መካከል በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ስኬታማ ስራዎችን ለማከናወን እርስ በእርሳቸው ያላቸው ስትራቴጂያዊ ግንኙነትም እጅግ ደካማ እንደሆነ ነው የሚነገረው ፡፡ 

ይሁንእንጂ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት በአፍሪካ ህብረት የተነደፈውና በትግበራ ላይ የሚገኘው አጀንዳ ሁለት ሺህ ስልሳ ሦስት በአጉሪቱ የምጣኔ ሀብታዊው ትስስርን ለመፍጠር ሰፊ ትኩረት የሰጠ ይመስላል፡፡ ለትስስሩ ተግባራዊነትም በአጉሪቱ የምርት አቅርቦት ሰንሰለትን በሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችለውን እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ ሀዋሳ ላይ የተሰባሰቡት የአህጉሪቱ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በዚሁ የምርት አቅርቦት ሰንሰለት አተገባበር ዙሪያ መክረዋል፡፡ በአፍሪካ ህብረት የግዥ፣ የጉዞና የንብረት ኮሚሽነር የሆኑት ወይዘሮ ካሪን ቱሬ / በአፍሪካ የምርት አቅርቦት ሠንሰለትን ለመዘርጋት መነሻ የሆኑ ምክንያቶቸና ጠቀሜታውን ይገልጻሉ፡፡ 

«የዚህ ሀሳብ መነሻ በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነውን የምርት አቅርቦት ሰንሰለት ሥረዓትን በማዘጋጀት ወደ ተግባር መቀየር ነው፡፡ በዚህ የምርት አቅርቦት ሠንሰለት የትግበራ ሂደት ውስጥ ከህብረቱ ባለፈ የአፍሪካ ልማት ባንክ ጭምር ተሳትፎ እያደረገበት ይገኛል፡፡ እንዲሁም የአፍሪካ ማህበረሰብን የሚወክሉ የክፍለ አህጉራት ድርጅቶችም የዚህ እቅድ በጎ ተጽኖ ያርፍባቸዋል ብለን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም የድርጅቶቹ አመራሮችና ተወካዮች በምርት አቅርቦት ሰንሰለት ሥርዓት እቅድና አተገባበር ዙሪያ ባዘጋጀነው መድረክ ላይ በስፋት መክረዋል፡፡ አሁን የአኛ ትልቁ ሚና የምርት አቅርቦት ሰንሰለት አንዲጠናከር የሚያስችለውን ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ ነው ፡፡ ይህም ህብረቱ የበለፀገችና ሰላም የሰፈነባት አፍሪካን ለመገንባት የነደፈውን ራዕይ ለማሳካት የራሳችንን ድርሻ የምናበረክትበትን ሁኔታ ይፈጥርልናል» 

በእርግጥ አጀንዳ ሁለት ሺህ ስልሳ ሶስት አፍሪካን በፖሊሲ፣ በገንዘብና በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር / የበለጸገችና ያደገች አፍሪካን እውን ለማድረግ አልሞ ስለመነሳቱ ይነገርለታል፡፡ 
ይሁንእንጂ ራዕዩን ተግራዊ ለማድረግና በአህጉሪቱ ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሀብት ዕድገት ለማስመዝገብ / በአገራት መካከል ያለውን የእርስ በእርስ ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ በመድረኩ ተሳታፊዎች ተጠቁሟል፡፡ 
በአፍሪካ ህብረት የግዥ፣ የጉዞና የንብረት ኮሚሽነሯ ወይዘሮ ካሪን ቱሬ በተሳታፊዎቹ የቀረበው ሀሳብ ለህብረቱም ሆነ ለአባል አገራቱ ጠቃሚ ግበዓት ነው ይላሉ ፡፡ 
በተለይም የምርት አቅርቦት ሰንሰለቱን በጠንካራ መሠረት ላይ ለመጣል የፋይናንስ ተቋማትና የክፍለ አህጉር ድርጅቶች ቁልፍ ባለድርሻ አካላት በመሆን የሂደቱ ተሳታፊ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ 

Afrikanische Lieferkette
ምስል DW/Amharic

«ለአፍሪካ ብልፅግና እንደ ቁልፉ ምሶሶ ተደርጎ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተቀመጠው ዕቅድ አጀንዳ ሁለት ሺህ ስልሳ ሶስት የተባለው ራዕይ ነው፡፡ አጀንዳ ሁለት ሺህ ስልሳ ሶስት በአፍሪካ የማህበራዊ እና የምጣኔ ሀብታዊ ሽግግር ለመፍጠር የተነደፈ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ነው፡፡ ዕቅዱ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በሁለት ሺህ አሥራ ሦስት የተጀመረ ሲሆን ለሚቀጥሉት ሃምሳ ዓመታት ማለትም እስከ ሁለት ሺህ ስልሳ ሦስት ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል፡፡ 

በአህጉሪቱ የሚተገበረው የምርት አቅርቦት ሰንሰለት ሥረዓት ለዚህ ዕቅድ መሳካት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን ፡፡ ሥረዓቱ በተለይም በአህጉሪቱ ጥራት ያለው የምርት እና የአገልግሎት አቅርቦቶችን በሚገባ ለማስዳደርና ለማቀላጠፍ አንደሚያስችል ይታሰባል፡፡ ከሁሉም በላይ በህብረቱ በተነደፈው አጀንዳ ሁለት ሺህ ስልሳ ሦስት ውስጥ የተካተቱ ሰባት ዋና ዋና ግቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ዋነው ነገር ግን በምርት አቅርቦት ሰንሰለት ሥረዓት አማካኝነት የሚዘጋጁ የልማት ዕቅዶች የአህጉሪቱን ህዝቦች ፍላጎት መሠረት ያደረጉ እንዲሆኑ አቅጣጫን የሚጠቁም መሆኑ ላይ ነው ፡፡ 
በተለይም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች ፤ ሕጻናትና ወጣቶች በሥረዓቱ ውስጥ በመታቀፍ እንዴት ወደ ተሻለ ኑሮ ማደግ እንደሚችሉ ያመላክታል ተብሎ ይገመታል።  
በአፍሪካ የምጣኔ ሀብት አለመዳበር በምክነያትነት ከሚጠቀሱት መካከል አገራት የሚፈጽሙት የምርት ሽያጭና የግዢ አቅርቦት አለመመጣጠን ሌላው ችግር መሆኑን የዘርፉ ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡ 
 በውይይት መድረኩ የተሳተፉትና በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ሀይለሚካኤል / በበርካታ የአፍሪካ አገራት እየተካሄደ የሚገኘው የምርት ሽያጭና የግዢ አቅርቦት በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ነው ይላሉ፡፡ 
 ይህም የአጉሪቱ ሸቀጦች የምርት ጥራትና የዋጋ ደረጃን መሠረት ባደረገው የአለም ገበያ በስፋት ለመግባት የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ እንዳደረገው ነው አቶ ተስፋዬ የሚናገሩት፡፡ 
 በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ የዳበረ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ለመፍጠር የተለያዩ የፖሊሲ አማራጮች ተግባራዊ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ ከአማራጭ የፖሊሲ ዝግጅቶች መካካል የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ይገኝበታል፡፡ ሥምምነቱ በአፍሪካ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት በማሳለጥ የህዝቦችን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ተብሎ ታምኖበታል፡፡  እስካሁን አብዛኞቹ የህብረቱ አባል አገራት ነጻ የንግድ ቀጠናውን ለመመስረት የሚያስችላቸውን ሰነድ ተቀብለው በፊርማቸው አጽድቀውታል፡፡ 

Afrikanische Lieferkette
ምስል DW/Amharic

ወይዘሮ ካሪን ቱሬ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ተጠና ስምምነት በአህጉሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት እንደመልካም ጅማሮ ሊቆጠር ይችላል ይላሉ፡፡ 
 ይሁንእንጂ በአፍሪካ የግብርና እና የአንዱስትሪ ምርቶች ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጥቅምና ጉዳት / በሂደት እየለዩ መጓዝ ይገባል ሲሉ ወይዘሮ ካሪን «በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ሥረዓትን ተግባራዊ ለማድረግ በሂደት ላይ ትገኛለች፡፡ እርግጥ ነው ሥምምነቱ በአፍሪካ አገራት መካከል ነጻ የሸቀጦች ዝውውር እንዲኖር ይፈቅዳል፡፡ የዚህ ስምምነት ተግባራዊ መሆን ቀደምሲል በገቢና በወጪ ምርቶች ላይ ሲሰራበት የቆየው የግብር ተመን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሽቆለቁል እንደሚችል ይታመናል፡፡ ይህ ሂደት ታዲያ በአፍሪካ አምራች እንዱስትሪዎች ላይ ሊኖረው የሚችለውን በጎ ወይም አሉታዊ ተፅኖ በማጥናት ምክረ ሀሳብ ማቅረብ ይኖርብናል» ሲሉ ይመክራሉ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
እሸቴ በቀለ