1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ዕድገትና የፊናንሱ ቀውስ ተጽዕኖ

ረቡዕ፣ የካቲት 25 2001

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ባለፈው አንድ አሠርተ-ዓመት ውስጥ በርከት ባሉ አገሮች ያልተቁዋረጠ ዕድገት ታይቷል። ይሁንና በወቅቱ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ሳቢያ ዕድገቱ እየተገታ ነው።

https://p.dw.com/p/H5av
የአፍሪቃ የነገ ተሥፋ
የአፍሪቃ የነገ ተሥፋ

ቀውሱ ዓለምአቀፍ የልማት ዕርዳታንና የመዋዕለ-ነዋይ ፍሰትን ለዘብ ሲያደርግ በጥሬ ዕቃ ዋጋ መልሶ መውደቅ የተነሣ ለምሳሌ በነዳጅ ዘይት ሃብት የታደሉ አገሮች ገቢ ማቆልቆል ይዟል። እርግጥ የአፍሪቃ የዕድገት ችግር በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ይባባስ እንጂ ይሄው ብቻ የወለደው አይደለም። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋምና ሌሎችም እንደሚያመለክቱት ሙስናንና የበጎ አስተዳደር ጉድለትን የመሳሰሉት ቤት-ሰራሽ ችግሮችም ዓቢይ አስተዋጽኦ አላቸው። በመጪው ሣምንት አጋማሽ በነዚሁ ነጥቦች ላይ ያተኮረ የአፍሪቃና የምዛሪው ተቁዋም ጉባዔ ታንዛኒያ ርዕሰ-ከተማ ዳር-ኤስ-ሣላም ላይ ይካሄዳል።

ከፍተኛ የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቁዋም የ IMF ና የአፍሪቃ ተጠሪዎች በሚቀጥለው ሣምንት ዳር-ኤስ-ሣላም ላይ ተሰብስበው በአፍሪቃ ዕድገት ላይ ይነጋገራሉ። ሁለት ቀናት የሚፈጀው ጉባዔ የተጠራው በታንዛኒያው ፕሬዚደንት በያካያ ኪክዌቴ፣ በምንዛሪው ተቁዋም አስተዳዳሪ በዶሚኒክ-ሽትራውስ-ካህንና በቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሕፊ በኮፊ አናን አነሳሽነት ነው። “ለውጥ፤ የአፍሪቃን የዕድገት ፈተና ለመወጣት ፍቱን ሽርክና” በሚል መርሆ በሚካሄደው ጉባዔ ላይ የአፍሪቃ የፊናንስ ሚኒስትሮችና የማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪዎች፤ የለጋሽ ወይም አበዳሪ ሃገራት ከፍተኛ ተጠሪዎች፤ የአካባቢና የዓለምአቀፉ የግል ኤኮኖሚ ዘርፍ ወኪሎች፤ እንዲሁም ታዋቂ ምሁራንና የሲቪል ሕብረተሰብ ተጠሪዎች ይሳተፋሉ።

የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቁዋም የአፍሪቃ ዘርፍ ሃላፊ የቀድሞይቱ የላይቤሪያ የፊናንስ ሚኒስትር አንቱዋኔት ሣዬህ እንደጠቀሱት የጉባዔው ዋና ዓላማ የክፍለ-ዓለሚቱን የቅርብ የዕድገት ስኬት መለስ ብሎ ማጤንና ትምሕርት መቅሰም፤ የወደፊት ዕርምጃንም ማረጋገጥ ነው።

“የታንዛኒያው ጉባዔ የታቀደው ሶሥት ሰፊ ጥያቄዎችን አንስቶ ለመወያየት ነው። የመጀመሪያው ከአፍሪቃ የለውጥ ስኬቶች ምን እንማራለን? የሚል ይሆናል። ሁለተኛው ጉባዔው በስፋት የሚያተኩርበት ጉዳይ እርግጥ የወቅቱ ዓለምአቀፍ ቀውስ ነው። የኤኮኖሚው ቀውስና ይሄው በአፍሪቃ ላይ ያለው ተጽዕኖ፤ እንዲሁም የአፍሪቃ ዕርምጃ መስመሩን ሳይስት እንዲቀጥል ማድረግ መቻሉን ይጠቀልላል። ሶሥተኛና የመጨረሻው ጉዳይ ደግሞ የምንዛሪው ተቁዋም ባለፉት ዓመታት ከአፍሪቃ ጋር ባዳበረው ትብብርና ይህንኑ ወደፊት በማጠናከሩ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ነው”

IMF-ን ጨምሮ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ኢንስቲቲዩቶች መረጃዎች መሠረት ብዙዎች ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኙ የአፍሪቃ አገሮች ከአሠርተ-ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛና የኤኮኖሚ ዕድገትና የገቢ ደረጃ መሻሻልን እስከ ቅርቡ ቀጣይ በሆነ መልክ አሳይተዋል። ተቺዎች ይሁንና በወቅቱ የሚጠበቀው ዕድገት ዝቅ ያለ፤ በአንጻሩም የኑሮ ውድነት ካለፈው 2008 ዓ.ም. ሲነጻጸር የላቅ እንደሚሆን በማስገንዘብ ቀጣይነት መኖሩን አይቀበሉትም። ይህ በተለይ ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኘውን የአፍሪቃ ክፍል የሚመለከት ነው።
አንዳንድ የኤኮኖሚ ጠበብት ለዚሁ የአፍሪቃ ክፍል የኤኮኖሚ ዕድገት መታሰር ውዝግቦችን፣ ሙስናንና የበጎ አስተዳደር እጦትን በዋና ምክንያትነት ይጠቅሳሉ። ለምሳሌ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎን በመሰለች በተፈጥሮ ጸጋ የካበተች አገር ኤኮኖሚዋን ለመነቃቃት የተደረዱት ጥረቶች ሁሉ በቅርቡ የአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ዓመጽ ሳቢያ መሰናክል ገጥሞት ቆይቷል። በዚምባብዌም የፖለቲካና የኤኮኖሚ ነውጽ ከሺህ በመቶ የሚበልጥ የኑሮ ውድነትን ነው ያስከተለው። ይህ ደግሞ በዓለም ላይ አቻ አይገኝለትም።

ሙስናና የሕዝብ ንብረት ምዝበራም በተለይ በሁለቱ ታላላቅ የአፍሪቃ ነዳጅ ዘይት አምራች አገሮች በናይጄሪያና በአንጎላ ከባድ ችግር የፈጠሩ ጉዳዮች ናቸው። አንጎላን እንደ ምሳሌ ብንወስድ ሙስና ዛሬ የማሕበራዊ ዕርምጃ መቅሰፍት ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው። መንግሥት በበኩሉ ችግሩን በከፍተኛ ሥልጣን ደረጃ ለመታገል በቂ የፖለቲካ ፍላጎት ኖሮት አይታይም። የአገሪቱ ፓርላማ ጸረ-ሙስና ኮሚሢዮን እንዲሰየም ያቀረበው ጥያቄ ተፈጻሚነት ሲያጣ የሕዝብ ንብረትን በመመዝበር ተከሰው “ዴ-ኮንታስ” በተሰኘ የፊናንስ ፍርድቤት ፊት የቀረቡ ፖለቲከኞች ዛሬም በሥልጣናቸው እንደቀጠሉ ነው።

የሆነው ሆኖ የአንጎላ መንግሥት በዚህም የነዳጅ ዘይት ዋጋ ባቆለቆለበት ከባድ ዓመት ከሰባት እስከ አሥር ከመቶ ዕድገት አይታጣም ባይ ነው። በተጨባጭ አገሪቱ በነዳጅ ዘይት የውጭ ንግድ ላይ በጣሙን ጥገኛ ስትሆን የዚሁ ዋጋ ደግሞ ባለፉት ወራት በግማሽ ያህል ነው የቀነሰው። ታዲያ የጀርመን ኤኮኖሚ የአፍሪቃ ማሕበር ባልደረባ አንድሬያስ ቬንስል ጉዳዩ ለአንጎላ ዕድገት ብርቱ መሰናክል እንደሚሆን ነው የሚያምኑት።

“ለያዝነው 2009 እና ለሚቀጥለው 2010 ዓ.ም. የሚቀርቡት የተለያዩ ትንበያዎች በጣሙን እርስበርስ የተራራቁ ናቸው። የአንጎላ መንግሥት በበኩሉ ይህም ሆኖ እስከ አሥር በመቶ ባለው ጣራ ከፍተኛውን የዕድገት መጠን ይጠብቃል። ሆኖም ግን በተለይ ከዓለምአቀፍ የምርምር ኢንስቲቲዩቶች በኩል ተሥፋ ሰጭ ያልሆነ ግምት ነው የሚቀርበው”

በነዚሁ ዕምነት ከሆነ አንጎላ ውስጥ በዚህ ዓመት አንዳች ዕድገት አይኖርም። አገሪቱ በነዳጅ ዘይትና በአልማዝ የውጭ ንግድ ላይ ሲበዛ ጥገኛ ስትሆን የነዳጁ ንግድ ብቻ የአገሪቱን አጠቃላይ ዓመታዊ ብሄራዊ ምርት የሚሸፍን ነው። እንግዲህ በአንድ በኩል የዋጋው መውደቅ በሌላም በነዳጅ ዘይት አምራችና ሻጭ አገሮች ድርጅት በኦፔክ የምርት መጠን ቅነሣ የተነሣ አንጎላ በሁለት ወገን ተጎጂ ነው የምትሆነው። በቀን ታወጣው ከነበረው ሁለት ሚሊዮን በርሚል ወደ አንድ ሚሊዮን ተኩል ገደብ ማለቱ ግዷ ነው። የናይጄሪያም ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይሆንም። ናይጄሪያን ካነሣን በሙስና ላይ መለስ እንበልና በተለይ በነዳጅ ዘይቱ ዘርፍ የተስፋፋው ይሄው ምዝበራ ምዕራብ አፍሪቃዊቱን አገርም ብዙ ነው ያከሰረው።

በከፍተኛ ባለሥልጣናት የምዝበራ ድርጊት የተነሣ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መጥፋቱ ነው የሚነገረው። ነገር ግን በአንጎላም ሆነ በናይጄሪያ የሙስናው ልክፍት ታውቆ የትግል ጥረት የተያዘ በመሆኑ ለወደፊቱ የተሥፋ ጭላንጭል መታየቱም አልቀረም። እርግጥ ጥረቱ ፍሬ እንዲሰጥ ሁለቱም አገሮች መዝባሪዎቹን ለመጋተር ዕርምጃቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል። የአፍሪቃንና የ IMF-ን ሽርክና ወይም ትብብር አስፈላጊነት በተመለከተ የምዕራብ አፍሪቃን የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ ኤኮዋስንና የደቡባዊውን አፍሪቃ የልማት ማሕበር ሣዴክን የመሳሰሉትን የክፍለ-ዓለሚቱን የአካባቢ የኤኮኖሚ ድርጅቶች ማጠናከሩ እንደሚበጅ የብዙዎች ዕምነት ነው።

የደቡባዊው አፍሪቃ የልማት ማሕበረሰብ ሣዴክ ብሪታኒያን፣ አሜሪካን፣ ጀርመንን፣ ቻይናንና ጃፓንን የመሳሰሉ ዋነኛ የንግድ ተሻራኪዎች ባሏት በደቡብ አፍሪቃ በመመራት በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ሩብ 85 በመቶውን የንግድ ልውውጥ ከቀረጥ ለማላቀቅ፤ በ 2012 ደግሞ መቶ በመቶ ነጻ ለማድረግ ከዓባል ሃገራቱ ጋር አንድ ውል ተፈራርሟል። ይህ ጥሩ ዜና ሊሆን ይችላል። ይሁንና አፍሪቃውያን የኤኮኖሚ ባለሙያዎች የቅርቡ የምግብና የነዳጅ ዋጋ ንረት በወቅቱም የመንግሥታቱን የበጀት ኪሣራ ወደ ላይ እየገፋው በመሆኑ ይሰጋሉ።
ከዚሁ ሌላ የአበዳሪ አገሮች ድጋፍም በዋጋው መናር ሂሣቡ ያደገውን የውጭ ምርት ወደ አገር ለማስገባት መንግሥታቱ የሚያፈሱትን ወጪ በሚሸፍን መጠን ከፍ አላለም። ይህ እርግጥ በአንዳንድ አገሮች የነዳጅ ዘይትና የምግብ ዋጋ ወረድ ቢልም ስጋቱ ባለበት የሚቀጥል ነው የሚሆነው። ታዲያ ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም በዚህ ረገድ አፍሪቃን ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው? የላይቤሪያዋ የፊናንስ ባለሙያ አንቱዋኔት ሣዬህ ተቁዋሙ አስፈላጊውን ዕርምጃ እየወሰደ ነው ይላሉ።

“IMF ላለፈው ዓመት የምግብና የነዳጅ ቀውስ ጥቂትም ቢሆን ከወዲሁ ምላሽ ሰጥቷል። ገና ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ተቁዋሙ የአፍሪቃን መንግሥታትና ሌሎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን አገሮች ለመደገፍ አዲስ ዕርምጃን አጽድቆ ነበር። በመጨረሻም አሁን ለአፍሪቃ የሚያደርገውን ቴክኒካዊ ዕርዳታ እጅጉን እያስፋፋ ነው”

በመጪው ሣምንት የዳር-ኤስ-ሣላም ጉባዔ የክፍለ-ዓለሚቱ በተለይም ከሣራ በስተደቡብ የሚገኙት አገሮች የኤኮኖሚ ዕድገት እንደገና ሰፊ መነጋገሪያ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። የአፍሪቃ መንግሥታትና የምንዛሪው ተቁዋም ለማንኛውም ለሚከሰት ያልተጠበቀ የማቆልቆል ሂደት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መቻል አለባቸው። ሌሎች የአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ፈተናዎች ሥረ-አጥነትና የእኩልነት እጦት ናቸው። እነዚሁም ለምሳሌ በደቡባዊው አፍሪቃ የጠነከረው HIV-AIDS በሚያስከትለው የኤኮኖሚ ዕድገት ማቆልቆል ሊባባሱ ይችላሉ። የኤኮኖሚው ማቆልቆል የመዋቅራዊ ዕድገት ድክመት፤ የማሕበራዊ አገልግሎት መጓደል ማለት ነው።

ይህም የምንዛሪው ተቁዋምና ለጋሽ መንግሥታት ዕርዳታ መስጠታቸውን በተፋጠነ ሁኔታ መጨመሩ እንኳ ቢቀር ባለበት መቀጠል ይኖርባቸዋል ማለት ነው። ይህም ለበጎ አስተዳደር፣ ለዴሞክራሲና ለጸረ ሙስና ትግል የሚደረግን ትግል ይጠቀልላል። የሕንድ ውቂያኖሷ ደሴት ሞሪሺየስና ቦትሱዋና በዚህ ረገድ ለተቀረው አፍሪቃ በአርአያነት ሊታዩ የሚችሉ ናቸው። ሁለቱ መንግሥታት ከነጻነት ወዲህ ሙስናን በመታገሉ፣ በጎ አስተዳደርንና ዴሞክራሲን በማራመዱ ረገድ ትጉህ ሆነው ቆይተዋል። የመጪውን ሣምንት የሁለት ቀናት ጉባዔ የምታስተናግደውን ታንዛኒያን በተመለከተ ይህን ለማለት አይቻልም።

ምንም እንኳ አገሪቱ ከኡጃማ ሶሻሊዝሟ ስንብት ካደረገች ከሃያ ዓመታት ወዲህ ዛሬ በለጋሽ መንግሥታት ዘንድ ተፈቃሪ ብትሆንም ዕርዳታው በጅቷል ማለቱ አዳጋች ነው። የውጭው ዕርዳታ የአገሪቱን ኤኮኖሚ በሚያዳብሩ ዘርፎች ላይ መፍሰሱን፣ ከዚህም ሌላ ድህነትን ለመቀነስ፤ እንዲሁም በሃብታምና በድሆች መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ መቻሉን የሚጠራጠሩ የአገሪቱ ጠበብት አልታጡም። በቅርቡ የተከሰተ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የቀድሞ ሚኒስትሮች የተዘፈቁበት ሙስና የፕሬዚደንት ኪክዌቴን አስተዳደር ጥላሸት ሲቀባው ታይቷል።