1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ መንግስታት የዘነጉት የስደት ቀውስ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 20 2007

ዜናዎቹ ሁሉ የሜድትራኒያን ባህር ዳርቻን አሰቃቂ አደጋና ሞት ያረዳሉ። በየቴሌቪዝኑ መስመርና ጋዜጦች የምንመለከታቸው ምስሎች ነፍሳቸውን ለማዳን የነፍስ አድን ጀልባዎች ላይ የተንጠለጠሉ አፍሪቃውያን፣ ከውሃ ላይ የሚንሳፈፉ አስከሬኖች፣ በድካምና እንግልት ከጣልያን የባህር ዳርቻዎች የደረሱ ስደተኞች ሆነዋል።

https://p.dw.com/p/1FGTj
Libyen Migranten im Abu Salim Zentrum
ምስል picture-alliance/dpa

በአውሮጳ የሚኖሩ አፍሪቃውያን ይህን ሲመለከቱ ምን ይሰማቸዋል? የሜድትራኒያን ባህር ወይም ላምፔዱሳ የሚሉትን ስሞች ስሰማ ሰውነቴ ይንቀጠቀጣል። ሐዘን ይገባኛል። ምክንያቱም በቅርቡ በተከሰቱ አደጋዎች በአውሮጳ የባህር ዳርቻዎች የሚቀበሩት አፍሪቃውያን የእኔ ሰዎች ናቸውና ነው።

ምን አልባት እንደ አፍሪቃዊ በአውሮጳ ላይ እንድቆጣ ትጠብቁ ይሆናል። እንደ እራሷ እንደ አውሮጳ! እኔ ግን የአፍሪቃ መንግስታት የሚገባውን ባለመሥራታቸው ተናድጃለሁ። በጣም አስገራሚ ሆኖ ያገኘሁት ደግሞ አውሮጳን ጨምሮ ለዚህ ቀውስ መፍትሄ ፍለጋ የሚንቀሳቀሱ አካላት የአፍሪቃ መንግስታት አንድ አካል ተደርገው አለመቆጠራቸውን ሳስተዉል ነው። አውሮጳውያን ለዚህ ችግር መፍትሄ ማበጀት እንዳለባቸው ስደተኞቹ የሚቀመጡባቸውን ቦታዎችም ምቹ ማድረግ እንደሚፈልጉ ሲናገሩ ይደመጣል። ይሁንና መፍትሄውን ለማግኘት የአፍሪቃ መንግስታት ያግዙናል የሚል ተስፋ ያላቸው አይመስልም። ምናልባት የአውሮጳ ህብረት መሪዎች የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ንኮሳዛና ድላምኒ ዙማ የስደት ቀውስ አንዱ የመወያያ ጉዳይ በነበረበት የሁለትዮሽ ጉባኤ ላይ ለንግግር መጋበዝ በቂ ነው ብለው ሳያስቡ አይቀሩም። በፍጹም። ችግሩን ለመፍታት መንገዱ ይህ አይደለም። አፍሪቃውያን የአውሮጳን ከንፈር መጠጣ አይሹም። አፍሪቃውያን ችግሩን ፊት ለፊት መጋፈጥ አለባቸው።

Gipfel Afrikanische Union AU in Addis Abeba 2015
ምስል picture alliance/dpa/Gcis

አውሮጳ ከአፍሪቃ ቀውስና ርካሽ የሰው ጉልበት ተጠቃሚ ነች። የአውሮጳ ዓሣ አስጋሪዎች በአፍሪቃ የባህር ክልል እንዳሻቸው ይሆናሉ፤ በአፍሪቃ ምድር የሚመረቱት ካካዎ፤ ፍራፍሬ፤ አትክልት እና አበባ ወደ አውሮጳና የቀረው ዓለም ይጫናሉ። ይሁንና የአፍሪቃን ምርትየሚሸምተው ዓለም አፍሪቃውያን አብረው እንዲመጡ አይፈልግም።

አውሮጳ በስደተኞች ቀውስ ላይ መምከር የጀመረችው እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን የአፍሪቃ መንግስታት ግን እስካሁን አንድ ስብሰባ ብቻ ነው ያካሄዱት። እኔ እንደ አንድ ግለሰብ በየስብሰባው ከቀረቡት የመፍትሄ ሃሳቦች አንዳቸውም ተግባራዊ አለመደረጋቸው ያሳስበኛል።

ይህን ችግር መፍትሄ የሚያስፈልገው ከሆነ አፍሪቃ እንደ ራሷ ችግር ልትወስደውና ሊያሳስባት ይገባል ብዬ አስባለሁ። አፍሪቃዊ በመሆኔ በአፍሪቃ መንግስታት አፍራለሁ። ይህ ጉዳይ በብዙ የአፍሪቃ ህብረትና የክፍለ አህጉራዊ ድርጅቶች ስብሰባዎች የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ሊሆን ይገባዋል። ዋነኛው ፈተና አፍሪቃውያን ስለ አውሮጳ ያላቸውን አተያይ መቀየር ነው። አውሮጳ ለአፍሪቃውያን ገነት አይደለችም። የምድር ላይ ሲዖል እንጂ!

በአውሮጳ በቀን ሶስት ዶላር ብቻ የሚከፈላቸው፤ አደገኛ ሥራዎችን የሚሰሩ ወይም በወሲብ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ አፍሪቃውያንን አግኝቻለሁ። በአውሮጳ ያለው አኗኗራቸው ጥለውት ከመጡት ሕይወታቸው የከፋ ነው።

Mission Mare Nostrum Italien Flüchtlinge Rettung Mittelmeer 2014
ምስል picture-alliance/dpa/Giuseppe Lami

አውሮጳ ዛሬም አፍሪቃውያን የሚገፉባት ምድር ናት። ለትምህርት ጣሊያን በነበርኩበት ጊዜ ወንዶች ጠጋ ብለው ለአንድ ምሽት ስንት እንደማስከፍል ይጠይቁኝ ነበር። አፍሪቃውያን «አውሮጳ ችግራችንን ሁሉ ይፈታል።» ብለው የሚያስቡትን ማቆም እንዳለባቸው መናገር እፈልጋለሁ። እዚህም መጨረሻችሁ ከጎሰቆለዉ መንደር ሊሆን ይችላል። አሁን በሰማይ የማይጨበጥ ቤተ-መንግስት ከመገንባት ይልቅ በየአገራቸው ለሁሉም የሚበጅ መንገድ የሚያበጁበት ጊዜ ነው።

አሱምፕታ ላቱስ/እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ