1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ህብረት ጉባኤና የመፍትሄ ሃሳቡ

ቅዳሜ፣ ጥር 24 2006

ለሁለት ቀናት የዘለቀዉና አርብ ምሽት የተጠቃለለዉ የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ፤ በአህጉሪቱ ዉስጥ በሚታዩት አንዳንድ የፀጥታ ችግሮች ላይ የበለጠ ትኩረት ይዞ ታይተዋል። 54 አባል መንግስታትን ያቀፈዉ የአፍሪቃ ህብረት አርብ የተጠናቀቀዉ 22ኛዉ የመሬዎች ጉባኤ፤ ከከዚህ ቀደሙ በምን ይለያል?

https://p.dw.com/p/1B1FE
Afrika - Beginn des Gipfels der Afrikanische Union
ምስል picture-alliance/dpa

22 ተኛዉ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ፤ የዓለማቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት በአባል ሃገራቱ መሪዎች ላይ የሚጥለዉን ክስ ለመቃወም በአንድ ድምፅ እንዲቆም አሳሰበ።

አርብ ምሽት የተጠቃለለዉ የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ፤ ዋንኛ የመነጋገርያ አጀንዳ ግብርና እና የምግብ ዋስትና የሚል ቢሆንም በአህጉሪቱ የሚታዩት አንዳንድ የፀጥታ ችግሮች የበለጠ ትኩረት ይዘዉ ታይተዋል። ህብረቱ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ እዮቤልዩ በዓል በሚያከብርበት ወቅት፤ ተዘዋዋሪዉን የሊቀመንበርነት ስልጣን ይዛ የነበረችዉ እና ላለፉት 50 ዓመታት የአህጉራዊዉ ድርጅት ዋና መቀመጫ ኢትዮጵያም፤ የሊቀመንበርነት ስልጣኑን ለሞሪታንያ አስተላልፋለች። 54 አባል መንግስታትን ያቀፈዉ የአፍሪቃ ህብረት አርብ የተጠናቀቀዉ 22ኛዉ የመሬዎች ጉባኤ፤ ከከዚህ ቀደሙ በምን ይለያል? የፀጥታ ጥናት ተቋም በእንግሊዘኛ ምህፃሩ ISS ተንታኝ አቶ ሃሌሉያ ሉሌ እንደሚሉት፤ የአፍሪቃ ህብረት ዉስጥ በሃምሳ ዓመት የሰራቸዉን ሥራዎችም ገምግሞአል።

በሌላ በኩል በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክና በደቡብ ሱዳን የተባባሰው ግጭት፤ ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት የጉባኤው ትኩረት ሁለቱ ሃገራት ላይ እንዲሆን አድርጓል። በጉባኤዉ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ንግግር ያደረጉት የአፍሪቃ ህብረት ከሚሽን ሊቀመንበር ንኮሳዛና ድላማኒ ዙማ በሁለቱ ሃገራት የሚካሄዱ ግጭቶች ሰለባ በሆኑ ህዝቦች በተለይም ህፃናትና ሴቶች በደረሰባቸው ችግር የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀዋል። አህጉራዊዉ የመሪዎች ጉባኤ በአንዳንድ ሀገራት የሚታዩትን ብጥብጦች አንስቶ መወያየቱ በአህጉሪቱ ያሉትን ሰብዓዊ ቀዉሶችን ለማስወገድ ያደረገዉ እርምጃ ተስፋ ሰጭ ይሆን?
አንዳንድ ታዛቢዎች የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ፤ ከመሪዎች የመገናኛ እና የመታያ መድረክነት ባለፈ ለአህጉሪቱ የሚያመጣዉ ይህነዉ የሚባል ፋይዳ የለም ተገናኝተዉም የሚፈጽሙት አንዳችም ተግባር የለም ሲሉ ይተቻሉ። አቶ ሃሌሉያ ሉሌ እንደሚሉት ከሆነ ግን ህብረቱ በርግጥ እንደተጠበቀዉ በርካታ ስራዎችን ባይፈፅምም፤ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ያከናወናቸዉ ተግባራት ጥቂት የሚባል አይደለም።
እንደሚታወቀዉ የዓለማቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት በምህጻሩ ICC አባል የሆኑ አንዳንድ የአፍሪቃ ሀገራት ከድርጅቱ አባልነት መዉጣትን ይሻሉ፤ በሌላ በኬል የአፍሪቃ ህብረት የራሱ የሚለዉ የወንጀል መርማሪ ፍርድ ቤት አቋቁሞአል። ታድያ ይህ ፍርድ ቤት በአህጉሪቱ ባለስልጣናት ተሰሩ የተባሉትን ወንጀሎች በመፈተሽ፤ እንዲሁም ፍትሃዊ ሆኖ በመስራት ረገድ ምን ያህል ታዓማኒ ይሆን?
ምንም እንኳን ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ቡድኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ቢፈፅሙም፤ አመፁ እንደቀጠለ ነው። የደቡብ ሱዳኑ ጦርነት ሸምጋይ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን በምህፃሩ ኢጋድ የደቡብ ሱዳኑ የተኩስ አቁም ስምምነትን ተግባራዊነት የሚቆጣጠር ቡድን ለማሳማራት ማቀዱን በጉባኤዉ መጠቃለያ አርብ ዕለት አስታዉቆአል። የኢጋድ አባል ሃገራት መሪዎች ከአዲስ አበባው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ሁኔታውን የሚያጣራ የመጀመሪያ ቡድን በ 48 ሰዓታት ውስጥ በደቡብ ሱዳን እንዲሰማራም ጥሪ አቅርበዋል። የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር የሆነችዉ ኢትዮጵያ ይላሉ አቶ ሃሌሉያ ሉሌ በመቀጠል በህብረቱ 50ኛ ዓመት ተዘዋዋሪነት ሊቀመንበርነትን በያዘችበት ወቅት ቀላል ስራ አልጠበቃትም ነበር።

AU Gipfel in Addis Ababa 2013
ምስል Getachew Tedla HG
AU-Gipfel in Addis Abeba, Äthiopien, 30.01.2014 Uhuru Kenyatta
ምስል Reuters

አዲስ አበባ ላይ በተካሄደዉ በ22 ተኛው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ 34 የአፍሪቃ መሪዎች መገኘታቸዉ ተነግሯል ። የሁለት ቀናት የመሪዎች ጉባኤ ከተጠናቀቀ በኋላ ዛሬ ቅዳሜ የአፍሪቃ መሪዎችና ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች የሚገኙበት ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ለዘመተው የአፍሪቃ ህብረት ኃይል ገንዘብ ለማሰባሰብ ቃል የሚገባበት ጉባኤ እንደሚካሄድ የአፍሪቃ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ሃላፊ ኤል ጋሲም ዋኔ ማስታውቃቸዉ ይታወቃል። የፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ አቶ ሃሌሉያ ሉሌ ለሰጡን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን።

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ