1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ/የአውሮጳ ኅብረት ትብብር

ቅዳሜ፣ ግንቦት 17 2011

የአውሮጳ ኅብረት መሪዎች ከግንቦት 15-18 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የአውሮጳ ምክር ቤት ምርጫ ያከናውናሉ። ወደ 350 ሚሊዮን ግድም ሰዎች 751 የምክር ቤት አባላትን መምረጥ ይችላሉ። የምክር ቤቱ አባላት ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት የአውሮጳን መጻዒ ይወስናሉ። ምርጫው ታዲያ ከአውሮጳ ውጪም በልዩ ኹኔታ ይታያል። ለምሳሌ በአፍሪቃ።  እንዴት? 

https://p.dw.com/p/3J31M
UK EU-Wahlen
ምስል picture-alliance/empics/J. Barlow

ምጣኔ ሐብታዊ ትብብሩ የ2ቱንም ጥቅም ሊያስጠብቅ ይገባል

የአውሮጳ ኅብረት መሪዎች ከግንቦት 15 ቀን እስከ ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ  የአውሮጳ ምክር ቤት ምርጫ ያከናውናሉ። ወደ 350 ሚሊዮን ግድም ሰዎች 751 የምክር ቤት አባላትን መምረጥ ይችላሉ። የምክር ቤቱ አባላት ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት የአውሮጳን መጻዒ ይወስናሉ። ፍልሰት እና የጸጥታ ኹናቴ የአውሮጳ ኅብረትን የተጋረጡ ከባድ ተግዳሮቶች ናቸው። ምርጫው ታዲያ ከአውሮጳ ውጪም በልዩ ኹኔታ ይታያል። ለምሳሌ በአፍሪቃ።  እንዴት? 

ፍልሰት የአውሮጳ ኅብረትን አኹንም ድረስ በብርቱ የሚገዳደር ጉዳይ ነው። ፍልሰተኞችን በየሀገሮቻቸው ተከፋፍሎ በስደተኝነት የማስፈሩ ጉዳይም የአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራትን በየጊዜው ማጨቃጨቊ ቀጥሏል። ባለፉት ዐሥርተ-ዓመታት ከሰሐራ በታች ወደ አውሮጳ የሚፈልሱ አፍሪቃውያን ቊጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው። እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ2016 ብቻ ከ170,000  በላይ ስደተኞች በሰሜን አፍሪቃ አቋርጠው ጣሊያን መድረሳቸውን የጣሊያን የሀገር ውስጥ ሚንሥትር ዐስታውቋል።   

«የአፍሪቃ የድህነት መጠን ከቅርበት አንጻር አውሮጳ ላይ ተጽዕኖ ያሳርፋል። በሁለቱ አኅጉራት ቅርቡ መዳረሻ 13 ኪሎ ሜትር ቢጠጋ ነው። ስለዚህ ናይጀሪያ ውስጥ ችግር ቢከሰት፤ ወይ ደግሞ ሩዋንዳ ውስጥ፤ አለያም ሶማሊያ፤ ዳፋው ሁልጊዜም ለአውሮጳ ይተርፋል።»

Mittelmeer Rettung von Flüchtlingen durch Sea-Watch 3
ምስል picture-alliance/ROPI/Sea Watch/N. Jaussi

ዶክተር ዲኮ ዑመር ራዳ ናይጀሪያ ውስጥ የሚገኘው አነስተኛ እና መካከለኛ ልማት ተቋም ኃላፊ ናቸው። የአውሮጳ ኅብረት አፍሪቃ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲያብብ እና ምጣኔ ሐብቱም እንዲጎለብት የበለጠ መሥራት እንዳለባቸው በጽኑ ያምናሉ። ብልጽግናው እየጎመራ በሄደ ቊጥር የተሻለ ሕይወት ለመምራት ወደ ሌሎች ሥፍራዎች የሚፈልሱ ስደተኞች ይቀንሳሉ ይላሉ።

«አውሮጳ አፍሪቃን እንድትተባበር እንሻለን። እንክብካቤ ያስፈልገናል። እጃችንን ይዘው ሊደግፉን ይገባል። እንዴት ሊተባበሩን እንደሚችሉ ለመመልከት ሞክሩ። መልካም አስተዳደርን በተመለከተ ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ እንዲሸሹ የሚደረጉ ገንዘቦች ቦታ እንዳያገኙ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህን ገንዘቦች ወደ አፍሪቃ ለመመለስ መሞከር ይገባቸዋል። ለአብነት ያኽል ከናይጀሪያ እጅግ ብዙ የሙስና ገንዘብ አውሮጳ ባንኮች ውስጥ ተደብቆ ይገኛል። የአውሮጳ ሃገራት ያን ገንዘብ ወደ አፍሪቃ ለመመለስ አሻፈረኝ ነው የሚሉት።»

ሚካኤል ጋለር የአውሮጳ ሕዝባዊ ፓርቲን በመወከል የአውሮጳ ምክር ቤት አባል ናቸው።  በአፍሪቃ ከሰሐራ በታች 77 ከመቶው ነዋሪ ዕድሜው ከ35 ዓመት በታች ነው።  ሚካኤል ጋለር ያ ከአፍሪቃ ጋር ወደፊት ኹነኛ ሽርክ ለማበጀት ይረዳል ባይ ናቸው።

«እጅግ አቅም ያላት ጎረቤት አኅጉር ናት። እናም የአፍሪቃ ምሑራን፣ ወጣቶች እና የሲቪሉ ማኅበረሰብ በበርካታ ሃገራት ይህንን ጉዳይ ደጋግመው ሲያንጸባርቊ ተመልክቻለሁ። ሕዝቡ ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ ቦታ ላይ ነው ያለው። እኛም ልማቱ እንዲሳካ ከህዝቡ ጎን ኾነን ይህን አፍሪቃዊ አጀንዳ ባለመታከት መደገፍ አለብን። ይኽ ነው የማይባል የእውቀት ክምችት እና በቂ ፍላጎት በአፍሪቃ ሲቪሉ ማኅበረሰብ እና ወጣቱ ዘንድ እንዳለ አምናለሁ፤ ስለዚህ ቀረብ ብለን ያን መደገፍ ይገባናል።»

Senegal Präsidentschaftswahlen | Dakar
ምስል DW/B. Barry

አውሮጳ ይኽን እምቅ አቅም በተደጋጋሚ ለመጠቀም ሞክራለች። አንዳንድ የአውሮጳ ሃገራት አፍሪቃ ውስጥ ተቋማት ላላቸው ሰዎች የሞያ ሥልጠና አገልግሎት ይሰጣሉ። ቢያቬኑ አንጒዊ የጀርመንናውያን እና አፍሪቃውያን ጥምረት የኾነው (SME) የተባለ ተቋም ኃላፊ ናቸው። ተቋሙ አነስተኛ እና መካከለኛ ተቋማትን በማስተሳሰር ድጋፍ ይሰጣል። የተቋማቸው አጠቃላይ ተጽእኖው ምናልባት በቂ ሊባል የሚችል ነው፤ ኾኖም ስኬታማ ጉዳዮችንም ፈጽሟል። 

«ሴኔጋል መዲና ዳካር ውስጥ ባራካ የሚባል የጎስቋሎች መንደር አለ። እዚያ 2,000 ግድም ሰዎች ይኖራሉ። የጀርመኑ አነስተኛ እና መካከለኛ ተቋማት

ድርጅት ይኽን አካባቢ ወጣቶች ብሩኅ ተስፋ እንዲታያቸው ራሱን ወደሚችል ከተማ ማሸጋገር አለብን´ ይላል። እናስ ምን ኾነ? ጥቂት ተቋማት ወደ ሥፍራው አቅንተው ዕውቀታቸውን አካፈሉ። ከዚያም በርካታ አነስተኛ እና መካከለኛ ተቋማት አባላት ኾነው አኹን ከተማዪቱን ከጎስቋላ መንደር ወደ አዲስ ከተማነት እየገነቧት ነው።»

ከሞያዊ ሥልጠና ድጋፍ ባሻገር በአፍሪቃ እና አውሮጳ አኅጉራት መካከል የሚደረገው የምጣኔ ሐብታዊ ትብብር የኹለቱንም አኅጉራት ጥቅም የጠበቀ መኾን እንደሚገባው ባለሞያዎቹ አበክረው ይናገራሉ። አፍሪቃ በምጣኔ ሐብቱ ረገድ ለመበልጸግ ከአውሮጳ ኅብረት ድጋፍ ከመጠበቅ ይልቅ በአኅጉሯ ውስጥ የምታደርገው የምጣኔ ሐብታዊ የእርስ በእርስ ትብብርም ሊበረታታ እና ሊጎለብት ይገባል ብለዋል። 

እንደ የአውሮጳ ምክር ቤት አባሉ ሚካኤል ጋለር ከኾነ አፍሪቃ ከአውሮጳ ጋር የምታደርገው ትብብር እርስ በእርስ ከምታደርገው እጅግ የላቀ ነው። አፍሪቃ ከአውሮጳ ጋር  የምታከናውነው ትብብር 70 በመቶ ሲኾን፤ አፍሪቃውያን ከአፍሪቃውያን ጋር አኅጉሪቱ ውስጥ ያላቸው የንግድ ትብብር ግን 16 ከመቶ ቢደርስ ነው። 

Belgien: Statue "Europa" vor EU-Parlament, Brüssel
ምስል picture-alliance/D. Kalker

«አፍሪቃ ንግድ እና መዋዕለ-ንዋይ ፍሰቱ ተሻሽሎ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ውስጣዊ ድንበሯን በቀላሉ ክፍት ልታደርግ ይገባል። እኛ እንደ አውሮጳውያን እርስ በእርስ በመነገድ ተጠቃሚዎች ኾነናል። ያም ጠንካራ እና ሐብታም አድርጎናል። እናም ይኼ በአፍሪቃ ነጻ የንግድ ቃጣና ጉዳይ በእና በኩልም ሊደገፍ ይገባል። አፍሪቃውያን ከእኛ ራሳቸውን መጠበቅ ከፈለጉ የፓን አፍሪቃ ቀረጥ ደንብ በማበጀት ከአውሮጳ፤ ከአሜሪካ እና ከእስያ የሚገቡ ምርቶች ላይ የቀረጥ ደንቡን ሊተግብሩ ይችላሉ። አፍሪቃን በደንብ አድርጎ ይጠብቃታል። በዚህ ጉዳይ ላይ አፍሪቃውያን ስምምነት ካበጁ አንዳችን አንዳችንን በሚጎዳ መልኩ መሥራት አንችልም።»

ነጻ ንግድ የአውሮጳ ኅብረት ፖሊሲ ዋነኛ ጉዳይ ነው። ብራስልስ በአፍሪቃ ዲሞክራሲ እንዲጎለብት እና መልካም አስተዳደር እንዲጠናከር ቊርጠኛ ናት። በዚያም የኑሮ ኹኔታ እንዲሻሻል ትፈልጋለች። ለአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት የሚመረጡ ተወካዮች ይኽን የአኅጉሪቱን ቊርጠኛ አቋም ተግባራዊ በማድረግ ወደ ፍሬ የመቀየር ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል።  

ሄለን ሲነይ/ ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተስፋለም ወልደየስ