1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፋር ነፃ አዉጪ ግንባር ፓርቲ ባለስልጣናት ዉዝግብ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 21 2007

የአፋር ነፃ አዉጪ ግንባር ፓርቲ (ALFP) ሊቀመንበር ከአፋር መስተዳድር ገዢ ፓርቲ ከአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ)ጋር መዋሐዱን ካስታወቁ በኋላ በግንባሩ ባለሥልጣናት መካከል የተፈጠረዉ ዉዝግብ ተባብሶአል።

https://p.dw.com/p/1EDC9
Afar-Region in Äthiopien
ምስል picture-alliance / africamediaonline

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ከሁለቱም ወገኖች ደብዳቤ እንደደረሰዉና የቅሬታዉን ለማጣራት ምርመራ ላይ እንደሆነ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ ገልፆአል።

የአፋር ነፃ አዉጪ ግንባር ፓርቲ (ALFP) ሊቀመንበር አቶ ከዳ አፎ አይዳ አይስ ፓርቲዉ ከአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ)ጋር መዋሐዱን ለዶቼ ቬለ ራድዮ ከገለፁ በኋላ የፓርቲዉ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የዞን አምስት የጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ያኩሙ በላዕቱ ሁሴይን እርምጃዉን ተቃዉመዋል። የአፋር ነፃ አዉጭ ግንባር ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ከዳ አፎ አይዳ አይስ በአንፃሩ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ ግለሰብ በፓርቲዉ የሚታወቁ አይደሉም፤ ስልጣንም የላቸዉም በማለት ፤ አቶ ያኩሙ በላዕቱ ሁሴይንን እና ዶይቼ ቬለን ለመክሰስ ዝተዉ ነበር። ይሁንና አቶ ያኩሙ በላዕቱ ሁሴይን የፓርቲዉ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የዞን አምስት የፅሕፈት ቤት ሐላፊ መሆናቸዉን ዛሬ በድጋሚ አስታዉቀዋል። ለዚህ ሥልጣን የተመረጡትም የዛሬ ከሳሻቸዉ አቶ ከዳ አፎ አይዳ አይስ በነበሩበት ነበር ባይ ናቸዉ።

አቶ አሊ ሚራሕ የተባሉ ሌላ ግለሰብ ደግሞ የአቶ ያኩሙ በላዕቱ ሁሴይን ምክትል መሆናቸዉን ገልፀዉ የአፋር ነፃ አዉጪ ግንባር ፓርቲ (ALFP) ሊቀመንበር አቶ ከዳ አፎ አይዳ አይስ የሰጡትን መግለጫና ያደረጉትን ዉኽደት አዉግዘዋል። አቶ ያኩሙ በላዕቱ ሁሴይን የተባለዉ ዉኽደት ከህዝብ ተደብቆ መፈፀሙ ራሱ የሊቀመንበሩን የተሳሳተ አቋም የሚያሳይ ነዉ ይላሉ።

የሁለቱን ወገኞች ዉዝግብን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በሰጠን መግለጫ ከሁለቱም ወገኖች ደብዳቤ እንደደረሰዉ አረጋግጦአል። የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ምክትል ዋና ፀሃፊ አቶ ወንድሙ ጎላ እንደሚሉት የአፋር ነፃ አዉጪ ግንባር ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ አካሂዶ ፓርቲዉን ማፍረሱን በአንፃሩ ይህ ነገር ትክክል አይደለም የሚል የተቃዉሞ ደብዳቤ ከሌላ ወገን ደርሶዋቸዋል። ዞሮ ዞሮ ይላሉ የምርጫ ቦርድ ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ወንድሙ ጎላ ዞሮ ዞሮ እንዲህ አይነት ቅሪታ ሊመጣ ይችላል፤ ጉዳዩን ማጣራት ደግሞ የቦርዱ ሥራ ነዉ።

አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ