1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር

ዓርብ፣ ጥቅምት 10 2010

በአሁኑ ሰዓት የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ከሚያማርሯቸው ችግሮች መካከል፣ የስኳር ፣ የመብራት እና የውኃ እጥረት እንዲሁም ትራንስፖርት ዋንኞቹ ናቸው። በተለይ አዲሱ ዓመት እንደገባ እና ትምህርት ቤቶች እንደተከፈቱ የታክሲ እና የባቡር ወረፋ አማረረን የሚሉ አስተያየቶች በተደጋጋሚ ደርሰውናል።

https://p.dw.com/p/2mEsb
Äthiopien Bewohner von Addis Abeba
ምስል Imago/Schreyer

የወጣቶች ዓለም

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ከ 3,5- 4,6 ሚሊዮን  እንደሚደርስ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ከነዋሪው ብዛት ጋር ሲነፃደር በከተማዋ የሚገኙት የመጓጓዣ  አገልግሎቶች በቂ አይደሉም። በተለይ ደግሞ ዘንድሮ ትምህርት ቤቶች ከተከፈቱ በኋላ ታክሲዎች የሚያመላልሱት ሰው ቁጥር ጨምሯል። ሁሴን ትምህርት ቤት ለመሄድ ሶስት አማራጮች አሉት። በታክሲ፣ በእግር ወይም የሚያልፍ መኪና ለምኖ።ወጣቱ ከቤት ሲወጣ እንዴት ብሎ ትምህርት ቤት እንደሚደርስ በውል ስለማያውቅ አልፎ አልፎ ትምህርት ቤት አርፍዶ መድረስ ብቻ ሳይሆን በዚህም የተነሳ ተባሮም ያውቃል።
ልኡል በከተማዋ እምብርት ላይ በሚገኝ አንድ የመንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ ይሰራል። ሳናግረው፤ አርፍዶ ገና ቢሮ መግባቱ ነገር። « ታክሲ አጥቼ ከሁለት ሰዓት በላይ ነው የጠበቁት»ይላል። ልኡል ታክሲ ቢያገኝ እና መንገድ ባይዘጋጋ ቢበዛ ከቤቱ ስራ ቦታ እስኪደርስ የሚፈጅበት ጊዜ ግማሽ ሰዓት ያህል እንደሆነ ይናገራል። በብዛት ግን ቢያንስ አንድ ሰዓት ያህል ቀድሞ ነው ከቤቱ የሚወጣው፣ እንደዛም ሆኖ ያረፍዳል፤ በየጊዜው ማርፈዱ ስራው ላይ በተወሰነ ደረጃ ተፅዕኖ መፍጠሩ አልቀረም። ለልኡል ወደ ስራ ለመሄድ ታክሲ ብቸኛ አማራጩ አይደለም። የሚሰራበት ቦታ፣ ስቴዲዮም አካባቢ ቀላል ባቡርም ይጓዛል። ይሁንና በታክሲ መጓዝን ይመርጣል።  « ባቡር መቆየት አይቆይም ነገር ግን ሰልፉ ከታክሲ ይበልጣል። ልትሰረቂ ትችያለሽ።» ይላል።
ከሁለት አመት በፊት አገልግሎት መስጠት የጀመረው የቀላል ባቡር አገልግሎትን ብዙዎች ቢያወድሱም፤ አሁንም የከተማይቱን የትራንስፖርት ችግር አለመቀረፉ ያማርራቸዋል።  «በሰዓታቸው አይገኙም። ውስጡ ጭንውንቅ ነው።»ይላል፣ ሌላው የባቡር ተጠቃሚ እና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነው ታምራት። ታምራት ሰዓት አክብሮ ቢሮ መግባት ያለበት ስራ የለውም። መሄድ ሲኖርበት ያገኘውን አጋጣሚ ይጠቀማል። 
ካለፉት ሁለት ዓመታት አንስቶ በአዲስ አበባ የምትኖረው የከፍተኛ ተቋም ተማሪ ረሂማ የዮንቨርስቲ ጊቢ ነው የምትኖረው፤ ነገር ግን እሷም አንዳንዴ ከትምህርቷ ታረፍዳለች።« ብዙም አልመላለስም ግን በምሄድበት ሰዓት ትራንስፖርት አይገኝም።» ረሂማን የሚያናድዳት አርፍዳ መድረሷ ብቻ ሳይሆን መንገድ ላይ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚገጥማት ችግር ነው። 
ድሮ ሰልፍ ሳይኖር ሰዎች ተጋፍተው ነበር የሚሳፈሩት። አሁን ላይ ግን በባቡር፣ በታክሲም ይሁን በባስ የሚጓዙ ሰዎች ተራ ይዘው ይሰለፋሉ። ይህ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ባይቀርፍም ጥሩ አሰራር ነው ይላል ታምራት።
ሌላው የትራንስፖርት እጥረት አንዱ ተጎጂ ነኝ ያለን ዘላለም ነው። ስራው ቦታ ለመድረስ ከ 40 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ይፈጅበታል። «ታክሲዎች ጠዋት እና ማታ አይገኙም። በዛ ላይ ታክሲ የማይገባባቸው ቦታዎች አሉ።ይላል።ዘላለም ብዙም የባቡር ተጠቃሚ አይደለም። ምክንያቱ የባቡር አገልግሎቱ በተወሰኑ ስፍራዎች ብቻ ስለሆኑ ነው።
አዲሱ ዓመት 2010 ከገባ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የትራንስፖርት ችግር የቃኘው የወጣቶች ዓለም ዝግጅትን በድምፅ ማዳመጥም ይችላሉ።
 ልደት አበበ 

Äthiopien - Taxifahrer in Addis Ababa
ምስል AP
Addis Abeba Äthiopien Bahn Straßenbahn Haltestelle
ምስል picture-alliance/dpaMarthe van der Wolf
Äthiopien - Addis Abeba - City Churchill Road
ምስል DW/Y. Geberegziabehr

ነጋሽ መሐመድ