1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአየር ንብረት ድርድር በፓሪስ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 28 2008

የዓለም የሙቀት መጠን እየጨመረ ከሄደ ምድራችን ለሰዉ ልጅ የማትመች ልትሆን እንደምትችል የዘርፉ ተመራማሪዎች እያሳሰቡ ነዉ። የዓለም መንግሥታት መሪዎች የአየር ንብረት ለዉጥን ለመከላከል የጋራ መፍትሄ ለማምጣት የጀመሩትን ዉይይት ዘንድሮም ፓሪስ ላይ ቀጥለዋል።

https://p.dw.com/p/1HJ3c
Frankreich Klimagipfel in Paris Protest Eifelturm
ምስል Reuters/B. Tessier

የአየር ንብረት ድርድር በፓሪስ

እንዲህ ያለዉ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ሲካሄድ ባለፈዉ ሰኞ ፓሪስ ላይ የተጀመረዉ ጉባኤ 21ኛዉ መሆኑ ነዉ። የፓሪሱ ጉባኤ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም ደርባን ደቡብ አፍሪቃ ላይ የተነደፉ የመግባቢ ሃሳቦችን መነሻ በማድረግ አቀራርቦ ሁሉ የሚስማማበት ሕጋዊ ማዕቀፍ ያለዉ ዉሳኔ ላይ እንዲደርሱ ያመቻቻል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። በዚህ ጉባኤ ከምንም በላይ የዓለም የሙቀት መጠን እንዳይጨምር ለዚህ የሚዳርገዉን የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት መንግሥታት ለመቀነስ ቁርጠኛ አቋም እንዲይዙ እና እያንዳንዳቸዉም በምን ያህልም እንቀንሳለን የሚሉትን እንዲያሳዉቁ ይጠበቃል።

Frankreich Klimakonferenz COP21 in Paris
ምስል Reuters/S. Mahe

ለከባቢ አየር ብክለት ምክንያት የሆነዉን ሙቀት አማቂ ጋዝ በመልቀቁ ረገድ በሀገር ደረጃ ኢትዮጵያም ሆነች አህጉር አፍሪቃ እዚህ ግባ የሚባል አስተዋፅኦ እንደማያደርጉ ነዉ የሚነገረዉ። በግንባር ቀደምትነት ቻይና እና ዩናይትድ ስቴትስ ከ35 እና 10ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ CO2 ወደከባቢ አየር ይለቃሉ። ኢትዮጵያ በአቅሟ 150 ሜትሪክ ቶን ሙቀት አማቂ ጋዝ ወደከባቢ አየር እንደምትለቅ ተመዝግቧል።

የዓለማችን የድሀ ድሀ (LDC) የሚባሉ 48 ሃገራት የአየር ንብረት ለዉጥን ለመከላከል ያዘጋጁትን እቅድ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2020 እስከ 2030 ድረስ ባሉት ጊዜያት ለማሳካት እንዲችሉ በየዓመቱ 93,7 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልጋቸዉ ተገልጿል። ኢትዮጵያ እና ዛምቢያን እንዲሁም የመን እና የፓስፊክ የደሴት ሃገራትን ጨምሮ ገና ያላደጉ የሚባሉት እነዚህ ሃገራት በአየር ንብረት ለዉጥ መዘዝ ለከፋ ድርቅ፤ ጎርፍ እና ማዕበል የተጋለጡ መሆናቸዉ ተዘርዝሯል።

Frankreich Klimakonferenz COP21 in Paris
ምስል Reuters/S. Mahe

እነዚህ ሃገራት በየግላቸዉ የነደፏቸዉን የአየር ንብረት ለዉጥን ለመቋቋም እና ለመግታት የሚያስችሉ መርሃግብሮች ተግባራዊ ለማድረግ ብቻቸዉን አቅም ስለሚያንሳቸዉን አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያሻቸዉም ተወስቷል። ለዚህም ገና በጉባኤዉ መጀመሪያ 11 ለጋሽ መንግሥታት ሃገራት ማለትም ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ጣሊያን፣ ስዊድን፣ ስዊትዘርላንድ፣ ብሪታንያ እና ዩናይትድስቴትስ 250 ሚሊየን ዶላር ለመስጠት ዝግጁነታቸዉን ገልጸዋል። በፓሪሱ ጉባኤ መክፈቻ ዕለት ፈረንሳይ አፍሪቃ ለታዳሽ የኃይል ምንጮች ማስፋፊያ እንድታዉለዉ 2 ቢሊየን ዩሮ ለመስጠት መዘጋጀቷን አሳዉቃለች።

China Smog in Peking
ቤጂንግን ያፈናት ጭስምስል Reuters/K. Kyung-Hoon

የዓለማችን ግንባር ቀደም በካይ ሀገር ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ የሚታየዉ የብክለት መጠን ቀይ መስመር ማለፉን ሰኞ ዕለት ይፋ አድርጋለች። በሀገሪቱ ከእንግዲህ የግልም ሆኑ የመንግሥት ተሽከርካሪዎች እየተግበሰበሱ በዋና ከተማ ጎዳናዎች ላይ እንዲዘዋወሩ አይፈቀደም። በታርጋ ቁጥራቸዉ ሙሉና ጎዶሎ በሚል ተከፋፍለዉ ይሆናል በየተራቸዉ የሚሽከረከሩት። መንግሥትን ከዚህ ዉሳኔ ያደረሰዉ መላ ቤጂንግ ለመተንፈስ በሚያዳግት ጭስ በመታፈኗ ነዉ። ምናልባት አጋጣሚዉ ድንጋይ ከሰልን ለኃይል ምንጭነት አብዝታ የምትጠቀመዉ በኢንዱስትሪ እያደገች የምትገኘዉ ቻይና ልብ ገዝታ ልትቀንስ የሚገባትን የብክለት መጠን ጨመር እንድታደርግ ያስገድዳት ይሆን?

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ