1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአየር ንብረት ለዉጥና አፍሪቃ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 13 2005

አፍሪቃ በኢንዱስትሪ እዚህ ደረጃ ደርሳለች ለከባቢ አየር ብክለትም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጋለች ባይባልም በአየር ንብረት ለዉጥ የሚደርስባት ጉዳት ከዕለት ወደዕለት እየከፋ መሄዱ ነዉ የሚነገረዉ። ጉዳይን አስመልክቶ የሚካሄዱ ዉይይቶች ግን ይህነዉ የሚባል ዉጤት እስካሁን ማስመዝገቡ ተስኗቸዋል።

https://p.dw.com/p/18bhO
ምስል AFP/Getty Images

የተፈጥሮ ቁጣ መገለጫዎች በየአይነቱ በየአካባቢዉ ቢደርሱም ዛሬም ችግሩን በፅሞና አይቶ ለመፍትሄዉ ስልቶችን ለማመቻቸት የፖለቲካ ፈቃደኝነት እንደራቀ የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋቾች ያመለክታሉከሳምንታት በፊት ይህንኑ ችግር አንስቶ በተወያየ አንድ ጉባኤ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ አዲስ ሃሳብ በማቅረቧ ለብዙ ጊዜያት ሲብላላ የቆየዉን ጉዳይ ዳግም ጥሬ እንዳደረገዉ ነዉ የተነገረዉ። የዋሽንግተን ሃሳብ የብክለት ቅነሳዉ በኢንዱስትሪ ያደጉት ሀገሮች በጋራ በሚወሰን መጠን ላይ ከሚያተኩር እያንዳንዱ ሀገር የየራሱን እቅድ ነድፎ ያቅርብ የሚል ሲሆን በአሜሪካን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለዉጥ ልዩ ልዑክ ቶድ ስተርን እቅዱ በርካታ ሀገሮችን ለማስተባበር የታለ መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል። በግንባር ቀደም የከባቢ አየር ብክለት የምትወቀሰዉ ቻይና በአንፃሩ ከመነሻዉ ሀብታም ሀገሮች አስገድጅና አሳሪ ለሆነዉ የጋራ ርምጃ እና እቅድ ይበልጥ ቁርጠንነት እንዲያሳዩ ስትወተዉት ቆይታለች። ዩናይትድ ስቴትስ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ጉዳይ አስመልክታ ይፋ ያደረገችዉ እቅድ ግን ከዚህ ተቃራኒና ይልቁንም የኪዮቶ ስምምነት ቀጣይነት እንዳይኖረዉ የሚያደናቅፍ ሊሆን እንደሚችል ነዉ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች የሚገልፁት።

Klimawandel ist in der Sahel-Zone
ምስል picture-alliance/dpa

በርሊን ላይ በተካሄደዉ በዚህ ጉባኤ ላይ በሰፊዉ ለመወያያነት ከቀረቡ ነጥቦች ዋነኛዉ የበለፀጉ ሀገሮች የካርቦን ብክለትን እንዲቀንሱ የሚለዉ ነዉ። አፍሪቃ ምንም እንኳን አይን የሚገባ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ባይኖራትም የብክለቱ መዘዝ የሆነዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ከፍተኛ ተጠቂ መሆኗ እየታየ ነዉ። የበለፀጉትና ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ የሚታዩት ሀገሮች ከፍተኛዉ የብክለት መጠን የሚታይባቸዉ ሆነዉ ሳለ የካርቦን ብክለት ከዜሮ ነጥብ ዘጠኝ እንዳልበለጠ የሚገመትባት አፍሪቃ በአየር ንብረት ለዉጥ የመጠቃቷ ምክንያት ምን ይሆን? የግሪን ፒስ የአየር ንብረትና የኃይል ምንጭ ጉዳይ ተሟጋች ሚልታ ስቲል፤

«በመሠረቱ በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም የተለያዩ ይዞታዎች እንዳሉ አስባለሁ። ለምሳሌ ደቡብ አፍሪቃ ከትላልቆቹ የዓለማችን በካይ ሀገሮች 13ኛዋ ሀገር ናት። ይህም ማለት ደቡብ አፍሪቃ በድንጋይ ከሰል የተለከፈች ሀገር ናት ማለት ይቻላል። የኃይል ምንጭዋ በድንጋይ ከሰል ላይ የተመሠረተ ነዉ። በዚህም ምክንያት ከቀሪዉ የአህጉሪቱ ሀገሮች ምንም ወይም እጅግ አነስተኛ ብክለት ካለባቸዉ ጋ ስትነፃፀር ሀገሪቱ በከፍተኛ ብክለት ተጠቅታለች። ስለዚህ ከዚህ አንፃር የሚታዩ ሁለት ገፅታዎች ናቸዉ ደቡብ አፍሪቃ በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ለሚታየዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ተጠያቂ ሀገር ናት። በዚህ ምክንያትም በተለይ እጅስ ሰፊ በሆነዉ የአፍሪቃ ክፍለ ዓለም የእርሻ ስልታቸዉ የዝናብ ጥገኛ የሆኑ ወገኖች የዝናብ ወቅት መለዋወጥ ትልቅ ተፅዕኖ ይነረዋል።»

ሚልታ ስቲል እንደሚሉትም በካርቦን ብክለት ምክንያት ለችግር የተጋለጡ የአፍሪቃ ሀገሮች የሚገጥማቸዉን ፈተና የሚቋቋሙባቸዉ መንገዶች ለጊዜዉ የትኞቹ እንደሆኑም ሲያስረዱ፤

«እንደአዳጊ ሀገር የከፋዉ ነገር ሲገጥም ያለዉን ጥሬ ሃብት ለማዳን እና በአግባቡ ለመጠቀም ያሉት መንገዶች ሁለት ናቸዉ። አንደኛዉ ብክለትን ለመቀነስ ለምሳሌ የመጓጓዣ ስልቱን መለወጥ፤ የኃይል ማመንጫዉን ስልት ማስተካከል የመሳሰሉት ተከትሎ አንድ ሀገር ለአየር ንብረት ለዉጥ የምታደርገዉን አሉታዊ አስተዋፅኦ መቀነስ ነዉ። ሁለተኛዉ ደግሞ ከለዉጡ እና ችግሩ ጋ ተላምዶ የመኖር ሂደት ነዉ። ይህም የአየር ንብረት ለዉጥ አይቀሬ ሆኗል ስለዚህ ሀገሮች ለዚህ ችግር የሚሰጡት ምላሽ ምን ይመስላል? የሚለዉ ነዉ። እርግጥ ነዉ በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም አብዛኞቹ ሀገሮች በከፍተኛ ሁኔታ ያላደጉ ናቸዉ፤ እጅግ የደኸዩም ናቸዉ፤ ስለዚህ በከፍተኛ ሁኔታ ለችግር የተጋለጡ ሰዎች አፍሪቃ ዉስጥ በጣም ብዙ ናቸዉ። በዚህ ምክንያትም አፍሪቃ ዉስጥ ሀገሮች ችግሩን ተላምደዉ የመኖራቸዉ ሁኔታ እጅግ አዳጋች ነዉ ይሆናል። ሁኔታዉም የለም።»

Grönland Eis schmilzt
ምስል DW/I.Quaile

እሳቸዉ እንደሚሉትም በእርግጥም አስቀድሞ ሁኔታዎች ባልተስተካከሉበትና ልማቱ ባልተስፋፋበት ይዞታ የአፍሪቃ ሀገሮች በአየር ንብረት ለዉጥ መዘዝ የሚደርስባቸዉን ለመቋቋም አቅም ያላቸዉ አይመስልም። ይህም በየዓመቱ የሚታየዉን የምግብ ርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ብዛት፤ የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ እና የመሳሰሉትን መመልከቱ ግልፅ አመላካች መሆኑ ይታመናል። የግሪን ፒስ አፍሪቃ ባልደረባ ሜሊታ ስቲል የአየር ንብረት ለዉጥ የምግብ ምርትን በተለይ አፍሪቃ ዉስጥ ምን ያህል ጎድቷል ይላሉ?

«የአየር ንብረት ለዉጥ ቀጣይነት ያለዉ ክስተት ሲሆን በመጪዎቹ 10 አስራ አምስት ዓመታት ያለዉን ተፅዕኖ ይበልጥ የሚያሳይ ይሆናል። እንዲያም ሆኖ ግሪን ፒስ ማሊና ኬንያ ላይ በተለይ የዝናብ መጠን በሚለዋወጥባቸዉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የሚደርስባቸዉን ችግር አስመልክቶ ጥናት አካሂዷል። ለምሳሌ ማሊ ዉስጥ የሚወርደዉ የዝናብ መጠን በመለዋወጡ ምክንያት ሰዎች የሚዘሩትን የእህል አይነት ለመለወጥ ተገደዋል። ኬንያ ደግሞ ለግጭት መንስኤ የሚሆን ሁኔታ ይታያል፤ ቱርካና ሐይቅ ማለትም ሰዎች ዓሣ ለማስገር የሚጠቀሙበት ሐይቅ የሙቀት መጠን በመጨመሩ መጠኑ እየቀነሰ ነዉ። ይህ ማለት ምንድነዉ የተፈጥሮ ጥሬ ሀብት መጠን እያነሰ እየቀነሰ በመሄድ ላይ በመሆኑ ለግጭት መነሳት ዋና ምክንያት ይሆናል።»

ይህን ሁኔታ የሚያስተዉሉና በየጊዜዉ በአየር ንብረት ጉባኤዎች ላይ እየተገኙ የባለሙያዎችን የጥናት ዉጤቶች የሚያደርምጡ፤ አልፎ ተርፎም በየአድራሻቸዉ እየተላከ እንዲያነቡ የሚቀርብላቸዉ የአፍሪቃ ሀገራት መሪዎች ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋቿ ሜሊታ ስቲል ከክፍለ ዓለም አፍሪቃ በከፍተኛ የእድገት ጎዳና ላይ የምትገኘዉ ደቡብ አፍሪቃ በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና ይኖራታል ነዉ ተስፋቸዉ።

Trockenheit Maisernte in Mexiko
ምስል Ofelia Harms

«ደቡብ አፍሪቃ የብሪክስ እና የቤዚክ ቡድን አካል ናት፤ ቤዚክ የሚባሉት ብራዚል፤ ህንድ ቻይና እና ደቡብ አፍሪቃ ናቸዉ። እነዚህ ደግሞ የዓለም ዓቀፉ ድርድር የዚያ ወገን አባላት እና በመዉጣት ላይ ያለ ታላቅ ኤኮኖሚ ባለቤቶች ናቸዉ። እናም ደቡብ አፍሪቃ እዚህ ጋ ትልቅ ሚና ይኖራታል፤ አንድ በሀገር ዉስጥ ብክለትን ለመቀነስ ከድንጋይ ከሰል ወደታዳሽ የኃይል ምንጭ መሸጋገር ይኖርባታል፤ ደቡብ አፍሪቃ ከዓለማችን ለታዳሽ የኃይል የሚያገለግሉ ምርጥ የተባሉ ምንጮች ያሏት ሀገር ናት ነገር ግን ዛሬም 93 በመቶ የሚሆነዉ የኤሌክትሪክ ኃይሏ የሚገኘዉ ከከሰል ነዉ። እናም በዚህ ረገድ ደቡብ አፍሪቃ ቀዳሚነቱን መዉሰድ ይኖርባታል እላለሁ። ሌላዉ የአፍሪቃ ሀገሮች የበለፀጉት ወይም የአዉሮጳ ሀገሮች የሚያቀርቡትን ሃሳብ ወይም ግፊት ያለመቀበል ሁኔታ አለ። በተቃራኒዉ የአፍሪቃ ሀገሮች እንዲሁም ያልበለፀጉት ሀገሮች፤ እንዲሁም የደሴት ሀገሮች በጋራ በመሆን በኢንዱስትሪ ያደጉት ሀገሮች ብክለትን እንዲቀንሱ ግፊት ማድረግ ይኖርባቸዋል።»

ምንም እንኳን የአየር ንብረት ለዉጥን ለመቆጣጠር ከየኢንዱስትሪዉ የሚለቀቀዉ ካርቦን ብክለት ለመቀነስ የሚደረገዉ ጥረት ወሳኝ መሆኑ ቢነገርም የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋቿ እንደሚሉት ዛሬም ለእርምጃዉ እንቅፋት የሚሆኑ ሀገሮች አልጠፉም። በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙት በካዮች መመሪያዎችን እንዲያከብሩም አቅም ያላቸዉ ኃያላን ቅድሚያ ተግባራዊ ሲያደርጉ መታየት ይኖርባቸዋል።

«በዓለም ዓቀፉ ድርድር እንቅፋት ከሆኑ አካላት አንዷ ዩናይትድ ስቴትስ ናት። የኪዮቶ ዉልን አልፈረሙም፤ በድርድሩም እጅግ ዉስብስብ ሚና እየተጫወቱ አንደዉም አንዳንዴ ሂደቱ እርምጃ እንዳይኖረዉ የሚያደናቅፉ ይመስላል። የለአየር ንብረት ለዉጥን ለመከላከል ዓለም ዓቀፍ ስምምነት በእርግጥም ያስፈልጋል። ለዚህም አዳጊ ሀገሮች በሙሉ በጋራ መቆም ይኖርባቸዋል። ሀገሮች እንደተስማሙት ከሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ ዉሉ ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ላይ ደግሞ ሀገሮች በየግላቸዉ ብክለትን ለመቀነስ በከሰል ኃይል ከማመንጨት መላቀቅ አለባቸዉ። የመጓጓዣ ስልቶቻቸዉንም መፈተሽ አለባቸዉ። በመሠረቱ የበለፀጉት ሀገሮች ከባቢ አየሩን በካርቦን ዳይኦክሳይድ መበከል የጀመሩት ከኢንዱስትሪ አብዮት አንስቶ ነዉ። ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላይ ያሉትና በማደግ ላይ ያሉት ሀገሮች ናቸዉ በዉጤቱ አሁን ለመዘዙ የተጋለጡት። ስለዚህ ከፍተኛዉ ኃላፊነት ከበለፀጉት ሀገሮች ራስ አይወርድም፤ በመቀጠል ደግሞ በፍጥነት እያደጉ የሚገኙት ሀገሮች እንደ ቻይና ህንድ ብራዚል ደቡብ አፍሪቃም በበኩላቸዉ በየግል የሚያደርሱትን ብክለት ለመቀነስ ርምጃ መዉሰድ አለባቸዉ።»

የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋቿ እንዳሉትም ከሁሉም ወገኖች ዝግጁነት ቢጠበቅም ስምምነቱ ወዴት እንደሚያመራ መገመት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክ በጉባኤዉ ወቅት መጠቆማቸዉ አልቀረም።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ