1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ እና የአፍሪቃ መንግስታት ትብብር

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 4 2007

ምንም እንኳን ሰሞኑን የስደተኛ ጎርፉ በሐንጋሪ በኩል ቢጠናከርም፤ አሁን ድረስ በግሪክ፣ስፓኝ እና ኢጣሊያ በኩል አድርገው በርካታ የአፍሪቃ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመግባት ይሞክራሉ። ይህንን ፍልሰት ለማስቆም የአውሮፓ ሀገራት አዲስ እቅድ ይዘዋል።

https://p.dw.com/p/1GToe
Flüchtlinge in Melilla Flüchtling Grenzzaun Helikopter 06/2014
ምስል Reuters/Jesus Blasco de Avellaneda

[No title]

እቅዱ፤ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ክፉኛ ከሚወቀሱት እንደ ኤርትራ እና ሱዳን ያሉ መንግሥታት ጋር አብሮ መስራትን ይመለከታል። ስለዚሁ የስደተኞችን ቀውስ አስመልክቶ የአውሮፓ ህብረት በምን መልኩ ከአፍሪቃ ሀገራት ጋር በትክክል ሊሰራ እንዳቀደ ዝርዝር ዘገባ ማግኘቱ ቀላል አይደለም። ምናልባትም እቅዱ አምባገነን ከሚባሉት የኤርትራ እና ሱዳን መንግሥታት ጋር አብሮ መስራትን ስለሚተባበር ይሆናል ትላለች ፀሀፊዋ ካትሪን ማታይ።

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሆነ በየወሩ 5000 የሚጠጉ ኤርትራውያን ወደ አውሮፓ ይሰደዳሉ። ለዚህም ምክንያት ነው ሲል የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያስቀመጠው « የኤርትራ መንግሥት አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፈፀሙ ነው»። ከዶይቸ ቬለ ታማኝ ምንጭ የደረሰ መረጃ እንደሚጠቁመው፤ የአውሮፓ ህብረት ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመተባበር « የሰዎች ንግድን እና የህዝብ አዘዋዋሪዎችን መዋጋት ይፈልጋል።» ይህንንም እቅድ ያፀደቀው የአውሮፓ ህብረት -የአፍሪቃ ቀንድ የስደት መንገድ» የተሰኘው ድርጅት ኮሚቴ ነው። በዚህም ኮሚቴ ስር ፤ ከአውሮፓ ሀገራት ፤ ጀርመን፣ፈረንሳይ፣ጣሊያን እና ብሪታንያ ሲገኙበት፤ ከአፍሪቃ በኩል ደግሞ የአውፍቃ ህብረት፣ ግብፅ ፣ኢትዮጵያ፣ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትሪያ ይገኙበታል።

Menschenrechtsaktivistin Meron Estefanos
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሜሮን እስጢፋኖስምስል DW/Meron Estefanos

ኮሚቴው የተመሰረተው « የካርቱም ፕሮሰስ» በተባለው የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪቃ ሀገራት የትብብር ግንኙነት ምክንያት ነው። ዶይቸ ቬለ ስለዚሁ እቅድ በተደጋጋሚ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ቃለ መጠይቅ ለማግኘት ቢሞክርም፤ አልተሳካለትም። ይሁንና ኮሚሽኑ በፁሁፍ በሰጠው ምላሽ ዋና ዋና የተባሉትን እቅዶች አስቀምጧል። ይህም « የሰዎች ንግድን እና ሰው አዘዋዋሪዎችን ችግር ጉዳይ መመልከት፣ ለተጎጂዎች ርዳታ መለገስ፤ ለተፈናቀሉ ስደተኞች የሚቆዩበት ጣቢያ ማዘጋጀት የመሳሰሉት ይገኙበታል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሁማንራይትስ ዎች ባልደረባ ሎተ ላይሽት፤ የአውሮፓ ህብረት አሁን እንደ ሱዳን እና ኤርትራ ካሉ መንግሥታት ጋር መተባበር መፈለጉን ይተቻሉ።« የህግ የበላይነት በነዚህ ሀገራት እንደሌለ እና እንደማይከበር ፣ በሰዎች ላይ ዕለት ከዕለት በደል እንደሚፈፀም ፤ ይህም በደል ፤ፈፅሞ ፍርድ ሳይሰጥበት እንደሚቀር፤ እውቅና መስጠት ካልተፈለገ ብቻ ነው።

በርግጥ የሰው ንግድን መዋጋት ያስፈልጋል የሚሉት ባርባራ ሎህቢህለር ደግሞ የጀርመን የአረንጓዴው ፓርቲ የምክር ቤት አባል ናቸው።« ስደተኛውን ፤ የሚከታተሉት ከነሱ ጋር አብረው እንዲሰሩ የተፈለጉት ናቸው። እዚጋ የሚቃረን ነገር ይታያል። በርግጥ የተደራጁ ሰው አዘዋዋሪዎችን መዋጋት ያስፈልጋል፤ ነገር ግን ከለላ በሚሹት ሰዎች ወጪ አይደለም»

ሱዳንንም የተመለከትን እንደው የትብብር ስራው አስቸጋሪ ነው። የሱዳን ፕሬዚዳንት ኡማር አልበሽር በዓለም አቀፉ የወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በእስር ይፈለጋሉ። ዳርፉር ውስጥ ለተፈፀመ የዘር ጭፍጨፋ እና ግድያ ተጠያቂ ተብለዋል። እንደዛም ሆኖ በዚሁ የአውሮፓ ህብረት እቅድ መሰረት የሰዎች ንግድ እና አዘዋዋሪዎችን ለመታገል የማሰልጠኛ ጣቢያ ሊገነባ ታቅዷል። ጋዜጠኞች ስለተቹ እስር ቤት በሚገቡበት ሀገር እንደዚህ አይነት እቅዶች እንዴት እውን ሊሆኑ እንደታሰቡ ፈፅሞ አይገባኝም ይላሉ፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ላይሽት ።« እንደዚህ በከፍተኛ መጠን መብት ከማይጠብቁ ሀገራት ጋር አብሮ ሲሰሩ ውጤቱ ሊደርሱላቸው ላሉት ሰዎች ከለላ መስጠት ባይሆን ሊደንቅ አይገባም። ምናልባት የካርቱሙ ፕሮሰስ አላማ እውነታውን ከአውሮፓ ድንበሮች አርቆ ማቆየት ይሆናል፤ ሰዎች ጀልባ ላይ ወጥተው ወደዚህ ጉዞ ሲጀምሩ እንዳይታይ እና እዛው ያሉበት እንዲቀሩ የሚያደርግ።

Omar al-Baschir ARCHIV
ምስል picture-alliance/dpa/S. Elmehedwi

የጀርመኗ የምክር ቤት አባል ሎህቢህለርም ይሁኑ የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ባልደረባ ላይሽት ስለዚህ የትብብር ስራ እቅድ ለሁሉም ተደራሽ የሚሆን መረጃ አለመኖሩን ይተቻሉ።

ካትሪን ማታይ

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ