1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊቢያው ቀውስ

ማክሰኞ፣ የካቲት 10 2012

የተመድ በሊቢያ ላይ  የጣለው የጦር መሣሪያ ማዕቀብ መጣስ ብቻ ሳይሆን በሃገሪቱ የተኩስ አቁም ስምምነትም አለመተግበር ለሊቢያው ቀውስ መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።ታዲያ የጦር መሣሪያ ማዕቀቡ ተግባራዊነት ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ካለ ተኩስ አቁም ስምምነት ምን ያህል ውጤታማ ሊሆን ይችላል?

https://p.dw.com/p/3XxbY
Europäisches Treffen für Auswärtige Angelegenheiten | Josep Borrell, Heiko Maas und Jean Asselborn
ምስል picture-alliance/AP Photo/F. Seco

የሊቢያው ቀውስና የአውሮጳ ህብረት

የሊቢያን የርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም በጎርጎሮሳውያኑ 2020 ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል። በጥር ወር በርሊን ውስጥ የተካሄደው ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ ቀውሱን ለመፍታት ያስችላሉ የተባሉ የተለያዩ ውሳኔዎችምን ማሳለፉ ይታወሳል።አልተሳካም እንጂ በዚሁ ጉባኤ የተመድ እውቅና የሰጠውን የሊቢያ መንግሥት እና መንግሥትን የሚወጋውን ኃይል መሪዎች ፊት ለፊት አገናኝቶ የማወያየት ጥረትም ተደርጎ ነበር።ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደው የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ ላይም የሊቢያው ቀውስ አንዱ የመነጋገሪ ጉዳይ ነበር።ከዚሁ ጉባኤ ጎን ለጎን እዚያው ሙኒክ የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጉዳዩ ላይ የጀመሩትን ንግግር ትናንት በአውሮጳ ህብረት መቀመጫ ብራሰልስም ቀጥለው መፍትሄ ያሉት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። የህብረቱ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሊቢያ ላይ የተጣለው የጦር መሣሪያ ማዕቀብን ተግባራዊነት መቆጣጠር ያስችላል በተባለ አዲስ ተልዕኮ ላይ ነው የተስማሙት። ለቁጥጥሩ ሥራ የባህር ኃይል መርከቦች በሜዴትራንያን ባህር ላይ እንደሚሰማሩ ተገልጿል።ሚኒስትሮች በሊቢያ ላይ የተጣለውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ተግባራዊነት ለመቆጣጠር ትናንት የተስማሙት ጊዜ ከወሰደ ከባድ ክርክር በኋላ ነበር።ኦስትርያን የመሳሰሉ ሃገራት በሜዴትራንያን ባህር ላይ በሚሰማሩ መርከቦች ይከናወናል የተባለው ይኽው የባህር ኃይሉ ተልዕኮ እንደ ከዚህ ቀደሙ ተልዕኮ ስደተኞችን የሚስብ ይሆናል የሚል ስጋታቸውን ሲያነሱ ነበር። ህብረቱ ከዚህ ቀደም በሜዴትራንያን ባህር በኩል በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አውሮጳ የሚካሄድ ስደትን ለመከላከል ሲያካሂድ የቆየው ዘመቻ ሶፍያ ከኢጣልያ በኩል በተነሳበት ተቃውሞ ባለፈው ዓመት እንዲቋረጥ ተደርጓል። ዘመቻው የተጀመረው በጎርጎሮሳዊው 2015 በሜዴትራንያን ባህር ላይ በርካታ ስደተኞችን አጭቃ ትጓዝ የነበረች ጀልባ ሰጥማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ደብዛቸው ከጠፋ በኋላ ነበር። የኢጣልያ ተቃውሞ በሜዴትራንያን ባህር ቅኝት የሚያደርጉ የአውሮጳ ህብረት መርከቦች ስደተኞችን ከባህር አደጋ እያተረፉ በኢጣልያ ወደቦች ማራገፋቸው ነበር።ጉዳዩን ያንቀሳቀሱት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ ለዚህ ችግር መፍትሄው በሊቢያ ሰላም ማስፈን ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።ትንንት ብራሰልስ ውስጥ  እንዳሉት የሊቢያ ደህንነት የአውሮጳም ደህንነት ነው።

Münchner Sicherheitskonferenz
ምስል picture-alliance/dpa/M. Dalder

«የሊቢያ ጉዳይ የአውሮጳ የፀጥታ ጉዳይ ነው።ስለዚህ በአውሮጳ ደህንነታችንን ለማስጠበቅ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት ማወቅ አለበት።ስለ ፈላስያን የሚያስቡት ወገኖች፣የፍልሰት ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ሊቢያ አብረን ልንሰራ የምንችልበት የፀጥታ መዋቅር ያላት የከሸፈች ሃገር ካልሆነች ብቻ ነው።»

ሚኒስትሩ እንደሚሉት ይህን መሰሉን ተግባር ማከናወን የአውሮጳ ሃላፊነት ነው።

«የበርሊኑ ሂደት የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ቁጥጥር ፣ያ ማለት በባህር ላይ እስካላደረግን ድረስ ምንም ትርጉም የለውም።እንደ ኦስትሪያ ያለች ሃገር እንዴት በስተመጨረሻ እምቢ ልትል እንደቻለች አይገባኝም።እኛ አውሮጳዊ ሃላፊነት አለብን።»

«ተልዕኮው ስደተኞችን የሚስብ ይሆናል» የሚለውን ኦስትሪያን የመሳሰሉ ሃገራትን ስጋት ለማስቀረት መርከቦቹ በተለይ በምሥራቃዊ ሜዴትራንያን እንዲሰማሩ እንደሚደረግ ተገልጿል። ከስብሰባው በኋላ ብራሰልስ ውስጥ የተሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ የተከታተለው የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ  መርከቦቹ በዚህ አካባቢ እንዲሰማሩ የተደረገበትን ምክንያት ያብራራል።

የተመድ በሊቢያ ላይ  የጣለው የጦር መሣሪያ ማዕቀብ መጣስ ብቻ ሳይሆን በሃገሪቱ የተኩስ አቁም ስምምነትም አለመተግበር ለሊቢያው ቀውስ መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።ታዲያ የጦር መሣሪያ ማዕቀቡ ተግባራዊነት ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ካለ ተኩስ አቁም ስምምነት ምን ያህል ውጤታማ ሊሆን ይችላል? ከስብሰባው በኋላ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል መልስ የሰጡበት ጉዳይ ነበር ገበያው እንደሚለው ሌሎችም ከጦር መሣሪያ ቁጥጥሩ የተያያዙ ጥያቄዎችም በትናንቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተነስተው ነበር።

Bilder einer Rettung durch das Team der Ocean Viking
ምስል Anthony Jean/SOS Mediterranee

የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት በሊቢያ ቀውስ ላይ አንድ አቋም አለመያዛቸው አነጋጋሪ ሆኖ የዘለቀ ጉዳይ።ህብረቱን ጨምሮ አንዳንድ አባል ሃገራት ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጠውን የሊቢያ መንግሥት ሲደግፉ የተወሰኑት ደግሞ መንግሥትን የሚወጋውን ኃይል እያገዙ መሆናቸው ይነገራል።ከዚህ ከተራራቀው አቋማቸው አንጻር የትናንቱ ስምምነት አንድምታ ምን ይሆን?

የሊቢያው መሪ ሞአመር ጋዳፊ በጎርጎሮሳዊው 2011 ከተገደሉ በኋላ የአካባቢ ሚሊሽያዎች የጋዳፊን ጦር ሠራዊት መሣሪዎች ታጥቀዋል።የሊቢያው የርስ በርስ ጦርነት በ2014 ከተጀመረ በኋላም ወደ ሃገሪቱ በርካታ የጦር መሣሪያ ሲጎርፍ ቆይቷል። ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጠውን የሊቢያን መንግሥት የሚወጉት ጀነራል ካሊፋ ሀፍጣር ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከግብጽ ከዮርዳኖስ እና ከሩስያ የጦር መሣሪያ ድጋፍ እንደሚያገኙ ይነገራል።የተመድ እና የአውሮጳ ህብረት ድጋፍ ያለው የሊቢያ ብሔራዊ የስምምነት መንግሥት ደግሞ  ከቱርክ የጦር መሣሪያ ያገኛል ይባላል።ተንታኞች እንደሚሉት የአውሮጳ ህብረት በመጋቢት እጀምራለሁ የሚለው የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ተልዕኮ የአውሮጳ ህብረት ባለሥልጣናት እንዳሉት የቻሉትን ያህል ለማድረግ እንጂ የሊቢያን ቀውስ የሚፈታ አይሆንም።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ