1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳው ምክርቤት አሠራርና ሥልጣን

ሐሙስ፣ መጋቢት 30 1996

አውሮጳው ምክርቤት--እ.ጎ.አ. በ፲፱፻፶፯ የተፈረመው የሮማው ውል እንደሚያብራራው--በማኅበረሰቡ ውስጥ የተጣመሩት አባል-ሀገራት ሕዝቦች ወኪሎች የሚገኙበት አካል ነው። በዚህ አኳኋን፣ ዛሬ ከ፲፭ቱ የአውሮጳው ኅብረት አባል-ሀገራት የተውጣጡና ፫፻፸፭ ሚሊዮን አውሮጳውያንን የሚወክሉ ፮፻፳፮ የሕዝብ እንደራሴዎች ናቸው በዚያው በአውሮጳው ምክርቤት ውስጥ በሚደርሷቸው ውሳኔዎች መሠረት፣ በአውሮጳ ግንባታ የሚሳተፉት። እ.ጎ.አ. በመጭው ግንቦት ፩ የአውሮጳው ኅ

https://p.dw.com/p/E0fq
የአውሮጳው ምክርቤት በሽትራስቡርግ
የአውሮጳው ምክርቤት በሽትራስቡርግምስል EU

ብረት በ፲ አዲስ አባላት በሚስፋፋበት ጊዜ የምክርቤቱ አባላትም አሃዝ እንዲሁ የሚገዝፍ ይሆናል።

አሁን በሽትራስቡርክ/ፈረንሳይ የሚገኘው የአውሮጳው ምክርቤት ከ፳፭ ዓመታት በፊት--እ.ጎ.አ. በ፲፱፻፸፱ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ በጠቅላላው ቀጥተኛ ምርጫ የተሰየመው። ከዚያው ጊዜ ወዲህ አውሮጳውያኑ በየአምስት ዓመታት ነው የጋራውን ምክርቤት የሚመርጡት። አውሮጳውያን ባለፈው ምእተ-ዓመት እርስበርሳቸው በከባድ ጦርነት የተጣመዱበት ዓይነቱ ሁኔታ ተወግዶ፣ በቦታው እርቀ-ሰላም የተተካበትን የእፎይታ ድርጊት አጉልቶ የሚያንፀባርቅ ጉልህ ምልክት ነው ይኸው የጋራ ምክርቤት።

በአውሮጳው ኅብረት አባል-ሀገራት ውስጥ በሚኖረው ሕዝብ ጠቅላላ ቀጥተኛ ምርጫ አማካይነት ሕጋዊ ሰውነት የሚያገኘው የአውሮጳው ምክርቤት በኅልውናው መጀመሪያ ዓመታት ውስጥ እንደ ወረቀት ነምር እየተቆጠረ ትርጓሜ አጥቶ ከቆየ በኋላ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ሄዶ፣ በአውሮጳው የፖለቲካና የኤኮኖሚ ሕይወት ላይ ከፍተኛውን ተጽኖ የሚያሳርፍና ውሳኔዎችንም ለመድረስ ኣቅም ያለው አካል ለመሆን በቅቷል። በተለይም የአውሮጳው ኅብረት የጋራ ሸርፍና የጋራ ማዕከላይ ባንክ እንዲፈጠር ያስቻሉት፣ የአውሮጳውም ምክርቤት እርከን በእርከን አሳሪነት ከሌለው ምክርሰጭነት ሚና እየተላቀቀ፣ የሐጋጊነትና የቁጥጥር ሥልጣን ያለው አካል እንዲሆን ያበቁት በማስትሪኽትና በአምስተርዳም የተደረሱት ውሎች ናቸው። የጋራው ምክርቤት ዛሬ በአውሮጳ ደረጃ የሚፈጽማቸው ተግባራት ከአባላቱ ሀገራት ብሔራዊ ምክቤቶች ተግባራትጋር የሚነፃፀሩ ናቸው።

በአውሮጳው ምክርቤት ውስጥ ተወካዮቹ የሚቀመጡት፣ በየብሔራዊ ልኡካን ቡድን ሳይሆን፣ በየፓርቲዎቹ የፖለቲካ አግጣጫ መሠረት በአንጃ እየተለዩ ነው። ባሁኑ ጊዜ ሰባት አንጃዎችና ጥቂት አንጃ-አልባ አባላት ናቸው ጎራ እየለዩ የምክርቤት መቀመጫዎችን የሚይዙት። ከእነዚሁ ከሰባቱ አንጃዎች መካከል ዋንኞቹ “የአውሮጳ ሕዝባዊ ፓርቲ” የሚሰኙት የመላው አባል-ሀገራት ክርስቲያን-ዴሞክራቶች እና “የአውሮጳ ሶሻልዴሞክራት ፓርቲ” የሚሰኙት የመላው አባል-ሀገራት ሶሻልዴሞክራቶች ናቸው።

የአውሮጳው ምክርቤት ማዕከል በሽትራስቡርክ/ፈንሳይ ሲሆን፣ አባላቱ በየወሩ ለአንድ ሣምንት የሚሰበሰቡት፣ እዚያው ሽትራስቡርክ ውስጥ ነው፤ የምክርቤቱ ዋና ጽ/ቤት ግን በሉክሰምቡርክ ነው የሚገኘው። በወር ለሁለት ሣምንታት የምክርቤቱ ኮሚቴዎች በብሩክሴል/ቤልዥግ ይሰበሰባሉ፤ የተቀረው(ማለት የወሩ አራተኛው ሣምንት ለየአንጃዎቹ ስብሰባ ነው የተመደበው።

የተርጓሚዎችና ያፍታ ትርጁማኖች አገልግሎት እጅግ አመች እንዲሆን ከመደረጉ የተነሳ፣ ምክርቤቱና ኣካላቱ በየአባል-ሀገራቱ ብሔራዊ ቋንቋዎች ነው የሚጠቀሙት። የአውሮጳ ምክርቤት ፫ የሥራ ቦታዎች፣ ሽትራስቡርክ/ፈረንሳይ፣ ብሩክሴል/ቤልዥግ እና ሉክሰምቡርክ ናቸው። እነዚሁ ፫ቱ ከተሞች ለምክርቤቱ ሥራ ማዕከልነት የተመረጡት፣ የአውሮጳውያኑ ተቋማት ከተመሠረቱ በኋላ መፋፋት የጀመሩት እዚያው ስለነበር ነው። በታሪክ ውስጥ ሲራኮቱ የነበሩት ጀርመንና ፈረንሳይ የእርቅ ምልክት እንዲሆናቸው ነበር የፈረንሳይ ከተማ ሽትራስቡርክ የአውሮጳ መማክርት እና የአውሮጳው ምክርቤት ምልዓተ-ጉባኤ ማዕከል እንድትሆን የተደረገችው።

የአውሮጳው ኅብረት አባል-ሀገራት ከግማሽ ምእተ-ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ነው ዛሬ በሰላም የሚኖሩት። ኅብረቱ የተመሠረተባቸው እሴቶች የሰብዓዊውን ክብር፣ የሰብዓዊውን መብትና የነፃነትን ጥበቃ፣ የዴሞክራሲን፣ የእኩልነትንና የፍትሐዊ መንግሥትን ሥርዓት የሚያጎሉ ናቸው። የኅብረቱ አባል-ሀገራት ነዋሪዎች ገደብ የሌለበት ሙሉ የዝውውር ነፃነት አላቸው፤ የንግድ ግኙነቶች ከእክል የነፁ ናቸው፤ አሁን ፲፭ ከሆኑት የኅብረቱ አባል-ሀገራት መካከል በ፲፪ቱ ውስጥ አሁን የጋራው ሸርፍ ኦይሮ ነው የክፍያ አሃድ ሆኖ የሚያገለግለው።

የ፶ ዓመታት ታሪክ ያለው የአውሮጳው ኅብረት በኤኮኖሚውና በፖለቲካው መስክ ከፍተኛ የስኬት ደረጃ ነው የሚንፀባረቅበት። ፲፭ቱ አባል-ሀገራት በአንድነት ትልቅ የኤኮኖሚ ኃይል ናቸው፤ በዓለም ፖለቲካ መድረክም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ነው ያላቸው። ለዚህ ሁሉ ስኬት መሠረት የሚሆኑት፥ የጋራ ተቋማቱ ናቸው--እነዚሁም የጋራው ምክርቤት፣ የሚኒስትሮች መማክርት አካል እና የአውሮጳው ኮሚሲዮን መሆናቸው ነው። የራሱ የኅብረቱ በጀትና የሐጋጊነቱ ሥልጣን የስኬቱ ምልክቶች ናቸው። ባሁኑ ጊዜ በአባላቱ ሀገራት ውስጥ የሚሠራባቸው ብዙዎቹ ሕግጋት ከአውሮጳው ኅብረት ውሳኔዎች የሚመነጩ ናቸው።

ልክ እንደ እያንዳንዱ ብሔራዊ ምክርቤት፣ የአውሮጳውም ምክርቤት ፫ ማዕከላዊ ሥልጣናት አሉት--የሐጋጊነት፣ የበጀትና የቁጥጥር ሥልጣን። የአውሮጳው ምክርቤት ከሚኒስትሮቹ ምክርቤት ጋር በመተባበር ነው የአውሮጳን ሕግጋት የሚሰጠው። ይኸውም፣ የሚኒስትሮቹ መማክርትና የአውሮጳው ምክርቤት ባላቸው የእኩልነት ጥምረት፣ የአውሮጳው ኮሚሲዮን የነደፋቸውን ሕግጋት ውሳኔ ያደርጉባቸዋል። ዛሬ አውሮጳ ውስጥ ያለጋራው ምክርቤት የሚሳካ ነገር የለም። የአብሮ ውሳኔው መብት የምክርቤቱን ጉልህ ሥልጣን ነው የሚያንፀባርቀው። ይኸው የአብሮ ውሳኔ መብት ለምሳሌ የሙያተኞችን ነፃ ዝውውር፣ የውስጣዊ ገበያውን ክንውን፣ የምርምርንና የሥነቴክኒኩን ዕድገት፣ የሸማቾችን ጥቅም፣ ትምህርትን፣ ባሕልንና ጤና ጥበቃን የሚመለከት ይሆናል። የአውሮጳው ምክርቤት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ካሳለፋቸው ዓበይት ውሳኔዎች መካከል ለምሳሌ የኃይል ምንጮችና የሞተር ዘይቶች ለተፈጥሮ ጓዳ ጭነት በማይሆኑበት ይዘት እንዲቀርቡ፣ የእንስሳት ገፈራ ከጎጅ ተዋጽኦዎች እንዲነፃ፣ የትምባሆ ፍጆታ ለጤንነት ስላለው ጉዳት ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ የተደረገበት ድንጋጌ ይጠቀሳል።

የአውሮጳው ምክር’ቤት፣ ኮሚሲዮኑ ያንቀሳቀሰውን የሕግ ሠነድ ውሳኔ የሚያደርግበት፣ ቋሚው ኮሚቴ ባዘጋጀለት ዘገባ መሠረት ነው። ምክርቤቱ የሕጉን ሠነድ ብዙውን ጊዜ ማሻሻያ ያደርግበታል። የሚኒስትሮቹ ምክርቤት የፓርላማውን ማሻሻያ ከተቀበለው፣ ሕጉ ጽድቂያን ያገኛል። ብዙውን ጊዜ የአውሮጳው ኮሚሲዮን የፓርላማውን ማሻሻያ ተቀብሎ፣ ለውጡን ለሚኒስትሮቹ ምክር’ቤት ያስተላልፋል። የሚኒስትሮቹ ምክርቤት በበኩሉ ለውጡን የሚደግፈው፣ በድምጽ ብልጫ ቢሆንም፣ የሠነዱን ይዘት የሚለውጠው በሙሉ ድምጽ ብቻ ነው። ፓርላማው(ማለት የአውሮጳው ምክርቤት) እና የሚኒስትሮቹ ምክርቤት በረቂቅ ሕጉ ሠነድ ካልተስማሙበት፣ ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጣ አንድ ገላጋይ ኮሚቴ አስማሚ ሆኖ ይቀርባል።

የአውሮጳው ምክርቤት(ወይም ፓርላማ) እና የሚኒስትሮቹ ምክርቤት ተቀናጅተው የበጀቱን ኃላፊ አካል ይመሠርታሉ። በሌላም አነጋገር፥ ሁለቱ ወገኖች ልክ እንደ ሐጋጊነቱ ሥልጣን፣ የበጀት አደላደሉንም ሥልጣን ነው የሚጋሩት። በያመቱ በወርሃ ታህሣሥ የሚወሰነው የአውሮጳው ኅብረት በጀት፣ የፓርላማው ሊቀመንበር ከፈረሙበት በኋላ ነው የሚፀድቀው። በዚህ አኳኋን ነው ኅብረቱ ለቀጣዩ ዓመት የፊናንሱን አቅም የሚያገኘው። በዓመታዊው በጀት ምደባ አማካይነት ነው ፓርላማው ቅድሚያን ማግኘት የሚገባው ሆኖ ለሚያየው ጉዳይ የፖለቲካውን ክብደት ለመስጠት ዕድል የሚያገኘው። ይኸው የአውሮጳው ምክርቤት በዓመታዊው የበጀት ዕቅድ ረገድ ለብዙዎቹ የወጭ ዓይነቶች የመጨረሻውን ቃል ለመናገር መብት አለው። ለምሳሌ የተለየ የኤኮኖሚ ችግር ላለባቸው አካባቢዎች ማነቃቂያ ወይም ለሥራ አጥነት መታገያ አስፈላጊ ስለሚሆነው ወጭ የምክርቤቱ ቃል ይከበራል። ግን የግብርናውን ዘርፍ መደገፊያ በመሳሰሉት ወጭዎች ረገድ ፓርላማው ለውጥ ወይም ማሻሻያ እንዲደረግ ሐሳብ ሊያቀርብ ይችላል፤ የመጨረሻው ውሳኔ የሚኒስትሮቹ ምክርቤት ፈንታ ነው።

የአውሮጳው ኅብረት በጀት ራሱን የቻለ ነው፣ የአባላቱን ሀገራት መዋጮ የሚመረኮዝ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ ራሱን የቻለው የኅብረቱ ወጭ የሚሟላው ከባላቱ ሀገራት ጠቅላላ ብሔራዊ ገቢ ከፊል፣ አባላቱ ሀገራት ከዕቃዎች ሽያጭና ከአገልግሎት መስጫው ዘርፍ ከሚሰበስቡት እሴት-ቀረጥ፣ በኅብረቱ አፍአዊ ድንበር ላይ ከሚከፈለው ጉምሩክ-ቀረጥ’ና ከልይዩ ገቢዎች ነው።

ፓርላማው/ማለት የአውሮጳው ምክርቤት በበጀት ቁጥጥሩ ኮሚቴ አማካይነት የበጀት ገንዘቡን አዋዋል ይቆጣጠራል፣ ለዚሁ የቀልጣፋ በጀት አዋዋል ቁጥጥር መሠረት የሚያደርገው፣ የአውሮጳው ሂሳብ መቆጣጠሪያ መሥሪያቤት የሚያቀርበውን ዘገባ ነው።

የአውሮጳው ምክርቤት ከበጀት ቁጥጥሩ ሥልጣን ጎንለጎን፣ በጠቅላላው የአውሮጳውን ኅብረት ተግባራት የሚፈትሽበት የፖለቲካ ቁጥጥር ሚናም ነው ያለው። ይኸው የፖለቲካ ቁጥጥር ሥልጣን የኮሚሲዮኑን ተግባራት ብቻ ሳይሆን፣ ዪኒስትሮቹን ምክርቤትና የውጭውን፣ የፀጥታ አጠባበቁን ፖለቲካ መርሕ ጭምር ነው የሚመለከተው። የአውሮጳውን ኮሚሲዮን በመሰየምም ረገድ ነው የአውሮጳው ምክርቤት ዓቢዩን ሚና የሚይዘው። ኮሚሲዮኑን እምነት ካጣበት ሊያሰናብተውም ይችላል። የፓርላማው ሚና በሐጋጊነት፣ በበጀት ድልድልና በቁጥጥር ሥልጣን ብቻ ኣያበቃም፤ ከዚህም አልፎ ኅብረቱ በሚደመድማቸው ዓለምአቀፍ ውሎች፣ በአዲስ አባላት አቀባበል፣ በውጭ ፖለቲካና በፀጥታ አጠባበቅ መርሕ፣ በኅብረቱ አባል-ሀገሮች ውስጥ ባሉት የፍትሕ ጥያቄዎች፣ በሰብዓዊ መብቶች አዋጅ፣ በሽርፉ ኅብረትና በተሐድሶ ለውጥ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ነው ያለው፤ ለእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች የምክር’ቤቱ አዎንታዊ ውሳኔ አስፈላጊ ነው።

“ግሎባላይዜሽን” የሚሰኘው የኤኮኖሚው አጽናፋዊነትና የዓለም ንግድ ድርጅት ሚና ለአውሮጳው ምክርቤት ማዕከላዊ ጉዳዮች ናቸው። የአውሮጳው ኮሚሲዮን የኅብረቱ ድርድር መሪ በሚሆንበት ሚናው ረገድ ምክርቤቱ የሚሰጠው ሐሳብ ትልቅ ክብደት ነው የሚኖረው፤ በዓለም ንግድ ድርጅት በኩል የሚደረጉትን ድርድሮች ውጤት ምክርቤቱ ማጽደቅ አለበት።

የአውሮጳው ምክርቤት ባለው ሥልጣን በመጠቀም፣ በኅብረቱ ውስጥም ሆነ በውጭ ሰብዓዊው መብት እንዲከበር ይሟገታል፤ ለምሳሌ ሰብዓዊውን መብት ከማያከብሩ ሦሥተኛ ሀገሮች ጋር ሕብረቱ የሚደርሳቸውን የፊናንስ ርዳታ ሰነዶች የሚያግድበት ሥልጣን አለው። በዚህ አኳኋን፣ እነዚያው በደለኛ ሀገሮች የፖለቲካ እሥረኞችን እንዲለቅቁ፣ ወይም በሰብዓዊው መብት ጥበቃ ረገድ ዓለምአቀፍ ውሎችን እንዲፈራረሙ ለማስገድድ ይጥራል።

በአውሮጳው ኅብረትና በ፸፯ቱ ያፍሪቃ፣ የከራይብና የፓሲፊክ አካባቢ(አከፓ)ሀገሮች መካከል የተደረሰው የትብብር ስምምነት/ማለት “ኮቶኑ-ውል” የዴሞክራሲ መጠበቂያ አንቀጽ እንዲታከልበት ለማድረግ የተቻለው፥ በአውሮጳው ምክርቤት ተጽእኖ አማካይነት ነው። ይኸው የዴሞክራሲ አንቀጽ፣ ከባድ የሰብዓዊ መብት በደል የሚፈጽሙት ሀገሮች የልማት ርዳታ እንዲቋረጥባቸው ለማድረግ ያስችላል። ከቅርብ ጊዜ በፊት ኅልውናው የታወጀለት የአፍሪቃው የጋራ ምክር’ቤት ይህንኑ የአውሮጳውን ፓርላማ ነው አርአያ የሚያደርገው፤ ግን ብዙ ያፍሪቃ ሀሮች የሚተዳደሩት በመፈንቅለመንግሥት አድማዎች አማካይነት ሥልጣን በቀሙ፣ ወይም በተጭበረበረ ምርጫ ወደ ሥልጣን በተወጣጡ መሪዎች እንደመሆኑ መጠን፣ ወደ አውሮጳው ደረጃ ተቻኩሎ ውድና አሸብራቂ ተቋማትን ለመፍጠር በመዋተት ፈንታ፣ በመጀመሪያ ዴሞክራሲን በብሔራዊ ደረጃ መገንባት በተገባቸውም እንደነበር ታዛቢዎች ያስገነዝባሉ።

የሆነ ሆኖ፣ ያው የአፍሪቃው ምክርቤት አርአያ ያደረገው የአውሮጳው ምክር’ቤት ያጎላውን የዴሞክራሲ ፋና በመከተል፣ ለዚያው የሕግን ገዥነት፣ ማኅበራዊውንና ባሕላዊውን መብት ማሟላት ለተሳነው ኋላቀር አህጉር የኑሮ እፎይታን ለማስገኘት የሚጥር ደንዳና ተቋም ሊሆን እንደሚበቃ ተሥፋ ይደረጋል።