1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዌይስ መያዝ ና አንድምታው

ሐሙስ፣ ሰኔ 20 2005

ከቀድሞው የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት መሪዎች አንዱ የነበሩት ሼህ ሃሰን ዳሂር አዌስ ከአሸባብ ጓዶቻቸው አምልጠው በሸሹበት ማዕከላዊ ሶማሊያ ውስጥ መያዛቸው ተዘግቧል ። ሮይተርስ እንደዘገበው አዌስ አሁን አዳዶ በተባለው ከተማ ውስጥ በአንድ ደህንነቱ አስተማማኝ በሆነ ቤት ውስጥ ተይዘዋል ።

https://p.dw.com/p/18xfc
ምስል Bettina Rühl

የአዌስ ከአሸባብ መሸሽ በአሸባብ ውስጥ ክፍፍሉ እየሰፋ የመምጣት ምልክት ተደርጎ እንደሚወሰድ ፕሬቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ በሚገኘው ዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም የምስራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች ተንታኝ አንድሪውስ አታ አሳሞዋ አስታውቀዋል ። ከአሸባብ ሸሽተው ማዕከላዊ ሶማሊያ መግባታቸው የተነገረው ሼህ ሃሰን ዳሂር አዌስ እጎአ በ2006 መቅዲሾንና መላውን ሶማሊያ ለ 6 ወራት ያህል የተቆጣጠረውን የሶማሊያ የሸሪአ ፍርድ ቤቶች ህብረት ከመሰረቱ መሪዎች አንዱ ናቸው ። ያኔ ተሰሚነት የነበራቸው አዌስ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ህብረት በኢትዮጵያ ወታደሮች ከተሸነፈ በኋላ ወደ ኤርትራ ሄዱ ፣ እዚያ 3 ዓመት ቆይተው ሂዝቡል እስላም የተባለውን ቡድን መስርተው የሽግግር መንግሥቱን ለመወጋት እንደገና ወደ ሶማሊያ ተመለሱ ። ሆኖም አዌስ ሶማሊያ ከተመለሱ በኋላ ትግሉን ብቻቸውን ሳይሆን ከአሸባብ ጋር ሆነው ነው የቀጠሉት ።

Waffen in Afrika
ምስል AP

የአዌስ ቡድን ከአሸባብ ጋር የሶማሊያን መንግሥት መውጋት ከጀመረ በኋላ ግን ተሰሚነታቸው እንደ ቀድሞው አልዘለቀም ። ከዚህ ሌላ ፕሬቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ በሚገኘው ዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም የምስራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች ተንታኝ አንድሪውስ አታ አሳሞዋ እንደሚሉት አዌስና ከአሸባብ ጦር አዛዦች አንዱ የሆኑት አህመድ ጎዳኔም አይግባቡም ።

« በእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት ውስጥ ቁልፍ ሰው ነበሩ ። ከዚያ በኋላ የሂዝቦል እስላም መሪ ነበሩ ። ቡድናቸው ከአሸባብ ጋር ከአሸባብ ጋር ተቀላቅሏል ። በዚያን ወቅት ይበልጡን እንደ መንፈሳዊ መሪ ነበር የሚታዩት በመጠኑም ቢሆን ተሰሚነት ያላቸው ሰው ነበሩ ። ሆኖም አሁን በዚህ ደረጃ ላይ አይደለም የሚገኙት ። አሸባብ ውስጥ ዓለም ዓቀፍ ተዋጊዎች በሚጫወቱት ሚናና በአህመድ ጎዳኔ አመራርም አይስማሙም ። »

ከመቅዶሾ እንደሚወጡት ዘገባዎች አዌስን አሁን ለሽሽት ያበቃቸውም ከጎዳኔ ጋር መጋጨታቸው ነው ። እንደዘገባዎቹ የሁለቱ አለመግባባት ከ 1 ዓመት በላይ ዘልቋል ። እናም በአዌስ ታማኞችና በጎዳኔ ኃይሎች መካከል ግጭት ሲቀሰቀስ፣ አዌስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መቀመጫቸው የነበረችውን የባራዊ ደቡባዊ ወደብ ለቀው ሸሹ ። እንደ አሳሞዋ አዌስ የሽሹት ልዩነቱ እየሰፋ በመሄዱ ህይወታቸውን ለማትረፍ ነው ።

Bildergalerie Muttertag International Somalia
ምስል Mohamed Abdiwahab/AFP/Getty Images

« የሼክ ሃሰን ሽሽት ፣ በተለይ አሁን በአሸባብ ቡድን ውስጥ ግንኙነቱ እየተበላሸ የመሄዱ አንድ ተጨማሪ ምልክት ነው ። የውጭ ኃይሎችን በመጠቀምና በሶማሊያ ህዝብ ፍላጎት ላይ ልዩነት አላቸው ። ሼክ ሃሰን ዳሂር አዌስ ከውጭ ኃይሎች ይልቅ የሃገር ውስጥ አባላትን ይመርጣሉ ። አዌስ የጎዳኔን አመራር የሚቃወሙበት ሌላም አቅጣጫ አለ ። ይህም የውስጥ ግጭት አስከትሎ ህይወታቸውን ለማዳን የሸሹ ይመስላል ። »

አሳሞዋ እንደሚሉት የአዌስ ከአሸባብ ተለይቶ መኮብለል በአሸባብ ክፍፍል መኖሩን ና በአፍሪቃ ህብረት ኃይሎች መዳከሙንም አጉልቶ ያሳያል ። ከዚህ በተጨማሪም በብዙ አቅጣጫ ቡድኑን መጉዳቱም አይቀርም

«በእርግጠኝነት ፕሮፓጋንዳቸውን የሚያዳክም ይመስለኛል ። ምክንያቱም በፕሮፓጋንዳ በይበልጥ ይተማመናሉ ። እናም ለውጭው ዓለም ተባብረው ለጋራ ዓላማ እንደሚዋጉ ለሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ከባድ ምት ነው ። ሰዎችን ወደ ነርሱ ወገን ለማስገባት እንዲሁ አስቸጋሪ

ያደርግባቸዋል ። ማዕከላዊውን መንግሥት ባለማጠናከርና ሃገሪቱን አንድ አድርጎ ባለመግዛት ለሚያቀርቡት ወቀሳ አይመችም »

Bildergalerie Somalia Sicherheitslage Marka 2012
ምስል SIMON MAINA/AFP/GettyImages

እንደ አሳሞዋ አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ለሶማሊያ መንግሥት ጥሩ አጋጣሚ ነው ።

« መንግሥት ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የአሸባብ ፕሮፓጋንዳን ለማዳከም ሊጠቀምበት ይችላል ። ለዚህም ብቻ ሳይሆን አሸባብን ለማዳከም እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ለሶማሊያ ህዝብ ለማረጋገጥም ያስችላቸዋል ።ይህ ደግሞ ለሶማሊያ የሰላም ጥያቄ በጎ አካሄድ ነው ስለኢህ ይህ ለመንግሥት ጥሩ ይመስለኛል ። ምክንያቱም ጠላትህ የተ,ዳከመ በመሰለ ቁጥር አንድ ዓያነት ተፅእኖ በማድረግ ላይ እንዳለህ መከራከር ያስችላል ። »

አዌይስን በቁጥጥር ስር ያዋለው የአዳድ አስተዳደር የጎሳ መሪዎች ከመቅዲሾ መንግሥት ጋር በወደፊት እጣ ፈንታቸው ሁኔታ ላይ እየተደራደሩ ነው ።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ