1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብራቲስላቭ-የአዉሮጳ ሕብረት መሪዎች ጉባዔ

ዓርብ፣ መስከረም 6 2009

የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት መሪዎች በሕብረቱ የወደፊት ጉዞ ላይ ለመነጋገር ዛሬ ብራቲስላቭ-ስሎቫኪያ ዉስጥ ተሰብስበዋል። በጉባዔዉ ላይ ከሕብረቱ አባልነት ለመዉጣት የወሰነችዉ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ሲቀሩ፤ የተቀሩት የ27ቱ አባል ሐገራት ርዕሰነ ብሔራትና መራሕየነ መንግሥታት ተገኝተዋል።

https://p.dw.com/p/1K3vB
Slowakei EU Gipfel in Bratislava Gruppenfoto
ምስል Reuters/L. Foeger

ብሪታንያ ከሕብረቱ አባልነት ለመዉጣት ከወሰነች በኋላ የተቀሩት የሕብረቱ አባል መንግሥታት የሕብረቱን አንድነት ጠብቀዉ የሚቀጥሉበት ሥልት የየሃገሩን ፖለቲከኛ እያነጋገረ ነዉ። የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጉባኤዉ ከመጀመሩ በፊት እንዳሉት ሕብረቱ አንድነቱን ከማጠናከር በተጨማሪ ሌሎች በርካታ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች አሉበት። ይሁንና ሜርክል አክለዉ እንዳሉት የዛሬዉ ጉባዔ ለችግሮቹ ሁሉ መፍትሔ መስጠት አይችልም። «አዉሮጳ ያለባትን ችግሮች በሙሉ በአንድ ጉባዔ ማስወገድ አይቻልም። አሳሳቢ ሁኔታ ዉስጥ ነን። የዉጪና የዉስጥ ፀጥታ ጥበቃ ያሳስበናል።አሸባሪነትን በመዋጋትና በመከላከያ መስክ መተባበር፤ የኤኮኖሚ እድገትና የስራ ዕድል ፈጠራ ይበልጥ በማጠናከሩ መስክ ብዙ መስራት አለብን።»

የፈረንረንሳዩ ፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦሎንድም የሜርክልን ሐሳብ ተጋርተዋል።ኦሎንድ እንደሚሉት የብሪታንያ ከአባልነት መዉጣት ከባድ ፈተና ቢሆንም ሕብረቱ ሌሎች ፈተናዎችን እንደተወጣ ሁሉ ይኸኛዉንም መወጣቱ አይቀርም።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ