1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአኸን ከተማ የሰላም ሽልማት

ረቡዕ፣ ነሐሴ 27 2007

የዘንድሮዉ የአኸን ከተማ የሰላም ሽልማት ለሁለት የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ዜጎች ተሰጠ። ተሸላሚዎቹ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ዱዶኔ ናዛፓላንጋ እና የሀገሪቱ ሙስሊም ማኅበረሰብ ሊቀመንበር ኢማም ኮቢነ ላይማ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/1GQEC
Bildkombo Aachener Friedenspreis Oumar Kobine Layama / Dieudonné Nzapalainga
ምስል Getty Images/AFP/J. Demarthon - DW/S. Blanchard

[No title]

ሁለቱ የሐይማኖት መሪዎች ለሽልማቱ የተመረጡት በማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፑብሊክ አማፂያንና በመንግሥት ጦር መካከል ተጀምሮ የነበረዉ ዉጊያ ወደ ሃይማኖታዊ እልቂት ተሸጋግሮ ብዙ ሕዝብ የጨረሰዉ ግጭት ሰክኖ በሃይማኖቶች መካከል መከባበር እንዲኖር እና የታጠቁ ቡድኖችን ትጥቅ እንዲፈቱ ላደረጉት ጥረት ነዉ። ከዚህ በተጨማሪም ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙ ሃገራት ተሰደዉ ሞሮኮ ዉስጥ የሚገኙትን ስደተኞች በመርዳት አፍሪቃዉያን ተማሪዎችም ተሸልመዋል።

ሽልማቱ የተሰጠዉ ትናንት ነበር። ትህትና የተላበሱት ካቶሊካዊዉ ጳጳስ ዲዩዶኔ ናዛፓሊንጋ እና ኢማም ኮቢኒ ላያማ ለቃለመጠይቁ በርጩማዎች ላይ ነዉ የተቀመጡት። የአኸን የሰላም ሽልማቱንም እነዚህ ሁለት የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ የሃይማኖት አባቶች ራሳቸዉን ዝቅ እንዳደረጉ ነዉ የወሰዱት። ሊቀጳጳስ ናዛፓሊንጋ ሽልማቱን የተቀበሉት በሰላም፣ በዕርቅና አብሮ በመኖር በሚያምኑ ወገኖቻቸዉ ስም መሆኑን ተናግረዋል።

Logo Aachener Friedenspreis e.V.
ምስል Aachener Friedenspreis e.V.

«ታላቅ ቀን ነዉ፤ የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ወንዶችና ሴቶች በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን በጠንካራ ፍላጎት ተንቀሳቅሰዋል፤ ከፍተኛ ጥረትም አድርገዋል። ዛሬ ደግሞ በዓለማችን አኸን ዉስጥ ለዚህ ጥረት እዉቅና በመስጠት እኛን የሸለመ ቡድን አለ። እናም ለሁሉንም የሰብዓዊ ርዳታ ድርጅቶች፤ ለሁሉም በሰላምና በዕርቅ እና በሰላም አብሮ በመኖር ለሚያምኑ ማዕከላዊ አፍሪቃዉያን መታሰቢያ ይሁንልን። ሽልማቱ በተጨማሪም ከእኛ ቀድመዉ በሞት ለተለዩን ንፁሀን መታሰቢያም ይሁንልን። ደማቸዉ አዲሲቱን ማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፑብሊክ ለመዉለድ ዘር ይሆናል ብለን እናስባለን።»

ኢማም ላያማም እሳቸዉ ያሉትን በአዎንታ በማጠናከር የሰላም ሽልማቱ የሚያበረታታ እና ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ዉስጥ የእርስበርስ ጦርነትን የሚያቀጣጥሉ እንዳሉ ሁሉ ለሰላምም የሚደክሙ እንደሚገኙ ያመለክታል ብለዋል። ሃይማኖትም የግጭት መንስኤ ሳይሆን ተከባብሮ የመኖሪያ ስልት መሆኑ መታወቅ እንደሚኖርበትም አመልክተዋል።

«ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ብቻ ሳይሆን መላዉ ዓለም ሃይማኖት የኖረዉ ሊያስተሳስረን መሆኑን ለማሳየት እፈልጋለን። Religion (ሃይማኖት)የሚለዉ የእንግሊዝኛዉ ቃል ከላቲኑ ሬሊጋሬ ማለትም መተሳሰር ከሚለዉ የተገኘ ቃል ነዉ። እኛም ሰዎችን ከፈጣሪያቸዉ ማስተሳሰር ዓላማ እና ግባችን ነዉ። ይህን ግብ ማጣት አንሻም። ለዚህም ነዉ እኛ ራሳችን ተባብረን፤ በጓደኝነት ምግብ፤ ሃሳቦች እና ፕሮጀክቶችን መጋራት የጀመርነዉ። እናም አሁን ሌሎችም ከሌሎች ሰዎች ጋር ግንኙነት እንዲመሠርቱ ጥሪ እናቀርባለን።»

ለዘንድሮዉ የአኸን የሰላም ሽልማት ሁለቱን የሃይማኖት አባቶች በእጩነት ያቀረቡት ለይላ ፋናህመም እነሱ ላይ የሚታየዉን ተስፋ የተጋሩት ይመስላል። ፋናህመ ጀርመን ትኩረቷን አፍሪቃ ላይ እንድታደርግ ይሻሉ። ሊቀጳጳስ ናዛፓሊንጋን ለዓመታት ያዉቋቸዋል፤ ለዚህም ነዉ የእሳቸዉ ሀገር ዕጣ ፈንታ ትኩረታቸዉን የሳበዉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012ዓ,ም ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ዉስጥ አማፂያን ሥልጣን በያዙ ማግሥት የተነሳዉ ሐይማኖታዊ ግጭት በሁለት ቡድኖች መካከል ተባብሶ ታይቷል። በብዛት ሙስሊሞች የተሰባሰቡት ሴሌካ የተሰኘዉ ቡድንና ፀረ ባላካ የተባለዉና ክርስቲያኖች የሚበዙበት ቡድን አሰቃቂዉን መገዳደል ሲፈፅሙ አፍሪቃዉያኑ ጓደኞቻቸዉ ያደረጉትን ለማድነቅም ተገድደዋል። በመቶዎችና ሺዎች የሚገመቱ የሀገሪቱ ዜጎች ከዚህ አስከፊ አመፅና ጥቃት ሽሽት ተሰደዋል። ሌሎቹም ወደዋና ከተማ ባንጊ ፈለሱ። ለይላ ፋናህመ ስለሁለቱ የሃይማኖት አባቶች ጓደኝነት ሲናገሩ አድናቆታቸዉን መሸሸግ ይከብዳቸዋል። በጋራ ያከናወኑትን አርአያነት ያለዉ ተግባርም ሌሎችም ሊከተሉት ይገባል የሚል ፅኑ እምነት አላቸዉ።

Verleihung des Aachener Friedenspreises 2015 Kobine Layama Dieudonné Nzapalainga
ጳጳስ ዲዩዶኔ ናዛፓሊንጋ እና ኢማም ኮቢኒ ላያማምስል DW/S. Blanchard

«ለአባላት ጉባኤዉ እነሱን እንዲመርጥ ሃሳብ ብቻ ነዉ ያቀረብኩት። ለእኔ አስፈላጊዉ ነገር አንድ ነዉ፤ እሱም ጀርመን ትኩረቷን አፍሪቃ ላይ እንድታደርግ። በ2012 ማለቂያ ላይ ቀዉሱ ሲከሰት ሊቀጳጳሱ ለኢማሙ እና ቤተሰቦቻቸዉ እንዲሁም ለሌሎች 10,000 ለሚሆኑ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች እሳቸዉ በሚገኙበት ስፍራ መጠጊያ መስጠታቸዉን በምስክርነት አቅርቤያለሁ። እዉነታዉ ደግሞ ከግድያና ጭፍጨፋ ያዳነ ከለላ ነዉ፤ ከዚህም የላቀ ጓደኝነት እና የጋራ ቁርጠኝነት ተፈጥሯል። ይህ ለእኔ ለሌሎች ወደር የሌለዉ ምሳሌና ሰዎችን የሚያስተሳስር አርአያ ነዉ።»

Verleihung des Aachener Friedenspreises 2015 Studenten Initiative Marokko
የበጎ ፈቃድ ለጋሶቹ ወጣቶችምስል DW/S. Blanchard

ከእነሱ ሌላ ትናንት ሶስት አፍሪቃዉያን ወጣቶችም የአኸንን የሰላም ሽልማት ተቀብለዋል። ወጣቶቹ ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙ የተለያዩ ሃገራት ለመጡ ሕገወጥ ስደተኞችን ሞሮኮ ዉስጥ በሰብዓዊነት ያደረጉት ድጋፍ እና ርዳታ ለዚህ ያበቃቸዉ። ምግብ፤ ልብሶችና ድንኳኖችን ከማቅረብ በተጨማሪ የታመሙት ሃኪም ዘንድ በመዉሰድ ያሳክማሉ። ወጣቶቹ በበጎ ፈቃደኝነት የሚያደርጉት ተግባር ከሌሎች ዓይን ገብቶ እዉቅና ማግኝቷል። እነሱ ግን በሚኖሩባት ዑዥዳ ከተማ የተሰባሰቡትን ስደተኞች እያዩ እንዳላየ ማለፍ ስላልቻሉ የሚችሉት ለማድረግ መሞከራቸዉን ነዉ የገለጹት። ተሰዳጆቹ ሞሮኮ ዉስጥ ለዘረኝነት ጥቃት የተጋለጡ ናቸዉ። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ በሕጋዊነት እዚያ የሚገኙ ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙ ሃገራት የመጡ አፍሪቃዉያንም የፖሊስ ጥቃት ጭምር ይደርስባቸዋል። በእነሱ እምነትም ስደተኞችን እንዲህ ማድረጉ ከሰብዓዊነት የወጣ ነዉ።

ሳንድሪን ብሎንሻር/ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ