1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንጌላ ሜርክል የአፍሪቃ ጉብኝት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 6 2003

የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክል በሶሥት የአፍሪቃ አገሮች የሚያካሂዱትን ይፋ ጉብኝት ባለፈው ሰኞ ምሽት በኬንያ ጀምረው እያካሄዱ ነው።

https://p.dw.com/p/RZII
ምስል picture alliance/dpa

ሜርክል እስከፊታችን ሐሙስ ድረስ አንጎላንና ናይጄሪያንም የሚጎበኙ ሲሆን ትኩረታቸው በተለይም በጀርመን የጥሬ ሃብት ፍላጎት ላይ ያለመ መሆኑን ከዕርዳታ ይልቅ ስለ ሽርክና ማውራታቸውና አንድ የምጣኔ-ሃብት ዘርፍ ልዑካን ቡድን አስከትለው መጓዛቸው በጉልህ አሳይቷል። ወሮ/አንጌላ ሜርክል ጀርመን የአፍሪቃን ክፍለ-ዓለም ዕድገት አጥብቃ እንደምትሻ በመጥቀስ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ሽርክናን እንደሚፈልጉ ከወዲሁ ባለፈው ሰንበት ነበር ግልጽ ያደረጉት። ቻንስለሯ ትናንት የኬንያ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ወደ ሉዋንዳ ሲሻገሩ ይህም አንድ የጀርመን ቻንስለር አንጎላን ሲጎበኝ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ሜርክልን በነዳጅ ዘይት ሃብት የታደለችውን አገር እንዲጎበኙ ያነሳሳቸው በተለይ የኤኮኖሚ ጥቅም እንደሆነ ብዙም የሚያጠራጥር አይደለም። በጀርመን የምጣኔ-ሃብት ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ፔተር ሂንትሰ እንደሚሉትም ጉዞው የበርሊን መንግሥት በቅርቡ ካሰፈነው የአፍሪቃ ፖሊሲ ጋር የሚጣጣምም ነው።

“በአፍሪቃ ጽንሰ-ሃሣባችን ውስጥ የልማት ሽርክና፣ የኤኮኖሚ፣ የኤነርጂና የጥሬ ሃብት ጥያቄዎች ዓቢይ ሚና አላቸው። የምንፈልገው በዚሁ ጎረቤታችን ከሆነችው ክፍለ-ዓለም ጋር ትብብራችንን ማጠናከር ነው። ግባችን እንግዲህ ፍትሃዊ ሽርክናን ማስፈን ይሆናል”

የተጠቀሰው አዲስ የጀርመን መንግሥት የአፍሪቃ ጽንስ-ሃሣብ የልማት ዕርዳታን ከጀርመን የአፍሪቃ የሽርክና ፖሊሲ ጋር በአንድ በመጠቅለሉ አዲስ ባህርይ የሚኖረው ነው። በእኩልነት ላይ ለተመሠረተ ግንኙነት ክብደት ይሰጣል። በላይፕትሲግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪቃ ጥናት ኢንስቲቲዩት ሃላፊ ፕሮፌሰር ሄልሙት አሸ እንደሚሉት ጉብኝቱም በዚሁ መንፈስ የጀርመን ፍላጎት የሰመረበት ነው።

“ለጉብኝት የተመረጡት አገሮች ምርጫ በኤኮኖሚ ጥቅማችን ላይ መተኮሩን ያሳያል። ናይጄሪያና አንጎላ ሁለቱም ከልማት ትብብር ይልቅ ጠቃሚ የኤኮኖሚ ሸሪኮቻችን ናቸው። ኬንያም እንዲሁ! ኬንያ ከሁሉም በላይ ደግሞ አምሥት ሃገራትን በጠቀለለው የምሥራቅ አፍሪቃ ማሕበሰብ ውስጥ በኤኮኖሚ ዋነናዋ ናት። እናም የምሥራቅ አፍሪቃው ማሕበረሰብ ትልቅ ዕርምጃ የሚያደርገው የአካባቢ ገበያና የፖለቲካ ትስስር እንደመሆኑ መጠን ሊበረታታ ይገባዋል። ይህ ለኛም ጠቃሚ ነገር ነው”

ወደ አንጎላ እንመለስና እርግጥ አንጌላ ሜርክል ከሉዋንዳ ጋር ያለውን ሽርክና ለማጠናከር ብዙ ጊዜ አልነበራቸውም። የሉዋንዳው የ 24 ሰዓታት ቆይታቸው ከፕሬዚደንት ሆሴ-ኤዱዋርዶ-ዶሽ-ሣንቶሽ ጋር ተገናኝቶ በመነጋገርና በጀርመን-አንጎላ ኩባንያዎች የጋራ መድረክ ጉብኝት የተወሰነ ነው የሆነው። ነገር ግን የጉብኝቱ ጊዜ አጭር ይሁን እንጂ በሌላ በኩል ታላቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ከአንድ ዓመት ወዲህ በሉዋንዳ የጀርመንን የኤኮኖሚ ልዑካን የሚመሩት ሪካርዶ ጌሪክ ይናገራሉ። ይሄው አነስተኛ የንግድ ም/ቤት መሰል ተልዕኮ ተግባሩን የሚያራምደው ከጀርመን የምጣኔ-ሃብት ሚኒስቴር በሚቀርብለት በጀት ነው።

“ወሮ/አንጌላ ሜርክል ወደ አንጎላ መምጣታቸው ብቻ ራሱ ጥሩ ምልክት ነው። ሃያ ወይም 26 ሰዓታት ብቻ መቆየታቸው ትርጉም የለውም። ጠቃሚው ነገር የመግባቢያው ሰነድ ሊፈረም መቻሉ ነው። ስለዚህም ሜርክል ወደ አንጎላ መምጣቱ ስለተሳካላቸው በጣሙን ደስተኛ ነኝ”

በቻንስለር አንጌላ ሜርክል ጉብኝት ሂደት ሁለቱ መንግሥታት አንድ የባሕልና የመግባቢያ ሰነድ በፊርማ አጽድቀዋል። ይሄው የመግባቢያ ሰነድ ሁለቱ አገሮች ስልታዊ ትብብር ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት የሚገልጽ ነው። ስለዚሁ በዚህ በጀርመን የአንጎላ አምባሣደር አልቤርቶ-ዶ-ካርሞ-ሪቢየሮ ባለፈው ሰኔ ወር ሚዩኒክ ውስጥ በሁለቱ አገሮች የኤኮኖሚ መድረክ ላይ እንዲህ ነበር ያሉት።

“ወሣኙ መወሰድ ያለበት ዕርምጃ የጋራ የምጣኔ-ሃብት ኮሚሢዮን ማቋቋም ነው። እንዲህ ከሆነ ከሌሎች የአውሮፓ ሸሪኮች ጋር እንደሚደረገው ሁሉ በመንግሥታት ደረጃ ስለ ታላላቅ ፕሮዤዎች ልንወያይ እንችላለን። ከጀርመን ጋር የምናደርገውን የኤኮኖሚ ልውውጥ ካላሳደግን ከአውሮፓ ጋር ያለን ግንኙነት ለዘለቄታው የተዛባ ነው የሚሆነው”

ለግንዛቤ ያህል የሁለቱ አገሮች የጋራ ንግድ መጠን በ 2008 ዓ.ም. በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ የተነሣ በግልጽ ነው የቀነሰው። በቀዉሱ ሳቢያ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ሲያቆለቁል ይሄውም የአንጎላን መንግሥት ለብዙ ወራት የክፍያ ግዴታውን በጊዜው መወጣት እንዳይችል ችግር ላይ ነበር የጣለው። የአገሪቱ ኤኮኖሚም ከተለመደው 15 በመቶና ከዚያም በላይ ዕድገት ወርዶ ይሰናከላል። በዚሁ ጊዜ ከ 2008 እስከ 2010 ጀርመን ወደ አንጎላ የምታደርገው የውጭ ንግድም በሲሶ ነበር የቀነሰው። በትክክል ከ 388 ሚሊዮን ወደ 263 ሚሊዮን! አንጎላ ለጀርመን የምታቀርበው እንዲያውም ይብስ ነበር የመነመነው። ከ 469 ሚሊዮን በግማሽ ይቀንሣል።

እርግጥ ከያዝነው ዓመት መጀመሪያ ወዲህ የሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ እንደገና የዕድገት አዝማሚያ እየታየበት ነው። ይህም ሆኖ ግን የጀርመን ኩባንያዎች በአንጎላ የሌሎችን ያህል ለመቆናጠጥ ችለው አይገኙም። ታላላቁ የግንቢያ ኮንትራቶች የሚሰጡት ለብራዚል፣ ለፖርቱጋል ወይም ለቻይና ኩባንያዎች ነው። ነዳጅ ዘይት የማውጣቱ ፈቃድም በአሜሪካ፣ በፈረንሣይና በብራዚል ኩባንያዎች ዕጅ ነው። የጀርመን ኩባንያዎች በአንጻሩ በጥልቀት ቁፋሮ፣ በውሃ መረብ ማስፋፋት ዕቅድ አወጣጥና ጥሬ ሃብትን ለማውጣት በሚያስፈልጉ መሣሪያዎች አቅርቦት ላይ ያተኮረ ነው። በሉዋንዳ የጀርመን ምጣኔ-ሃብት ቢሮ ሃላፊ ሪካርዶ ጌሪክ ግን በወፊት ከዚህ የበለጠ ስራም ይኖራል ባይ ናቸው።

“አንጎላ ውስጥ በየቀኑ የምናወጣው ነዳጅ ዘይት ሁለት ሚሊዮን በርሚል ገደማ ይጠጋል። ይህ ደግሞ በጣም ብዙ ነው። አንጎላ ከናይጄሪያ ቀጥላ በአፍሪቃ ሁለተኛዋ ነዳጅ ዘይት አምራች አገር ናት። ግን ናይጄሪያ 150 ሚሊዮን ሕዝብ ሲኖራት የአንጎላ በአንጻሩ በ 17 ሚሊዮን የተወሰነ ነው። እና ብዙ ሃብት አለ። በአገሪቱ በወቅቱ ከወታደራዊው አገዛዝ ጋር ትስስር የሌለው መካከለኛ የሕብረተሰብ መደብ እየተስፋፋ ሲሆን ይሄው ደግሞ ለምርት ተግባር መዋዕለ-ነዋይ ማድረግ የሚችል ነው”

በጀርመንና በአንጎላ ግንኙነት ላይ በመሠረቱ ከኤኮኖሚው ይልቅ የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ጉዳይ ነው ከባድ ሆኖ የሚገኘው። አንጎላ በዚህ ረገድ ገና ብዙ መንገድ ነው የሚቀራት። ፕሬዚደንት ሆሴ-ኤዱዋርዶ-ዶሽ-ሣንቶሽ ከሊቢያው አምባገነን ገዢ ከሙአማር ጋዳፊ ቀጥለው አፍሪቃ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በሥልጣን ላይ በመቆየት ሁለተኛው ናቸው። ከ 31 ዓመታት በሚበልጥ የሥልጣን ዘመናቸው ደግሞ አንዴ እንኳ ተመርተውም አያውቁም።

ለማንኛውም ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ከጉዟቸው በፊት እንደገለጹት ጀርመን ከአንጎላ ጋር የኤነርጂ፤ ማለት የነዳጅ ሽርክና ትፈልጋለች። ይህም በዚህ በጀርመን አደጋ ላይ ለወደቁ ሰዎች ተሟጋች የሆነው ድርጅት ተጠሪ ኡልሪሽ ዲሊዩስ እንደሚሉት የጀርመንን የሰብዓዊ መብት አቋም አመኔታ የሚያሳጣ ነው። ሽርክናው ሙስናንና የሰብዓዊ መብት ጥሰትንም ያበረታታል።

“ይህ እርግጠኛ ነው። በዛሬው ጊዜ ከአንጎላ መንግሥት የሚተባበር ከማን ጋር በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ እንደተቀመጠ ማወቅ ይኖርበታል። የአንጎላ መንግሥት በዓለም ላይ ሲበዛ በሙስና ከሚወቀሱት መካከል አንዱ ሲሆን በሌላ በኩል በአገር ውስጥ ሰብዓዊ መብትን በሰፊው ይረግጣል፤ ተቃዋሚዎችን ያስራል። ሲበዛ አጠያያቂና ለረጅም ጊዜም በሥልጣን ላይ የቆየ መንግሥት ነው። ይህ ደግሞ የማይታወቅ ነገር አይደለም። የጀርመን መንግሥት በሰሜን አፍሪቃው የለውጥ እንቅስቃሴ ሳቢያ አገሪቱ ከንደነዚህ ዓይነት ገዢዎች ጋር ማበር እንደማትፈልግ ከገለጸ በኋላ አሁን የኤነርጂ ሽርክና መግባቱ ብርቱ ዓመኔታ መስጠቱን ነው የሚያሳየው”

የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ትናንት ናይሮቢ ውስጥ ከኬንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ከራኢላ ኦዲንጋ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጸረ-ሙስና ሕግ ጠቃሚ በመሆኑ ከአስተናጋጃቸው ጋር አንድነት መደረሱን አስታውቀዋል። ቻንስለሯ በተወሰነ ቅድመ-ግዴታ የሁለቱን አገሮች የኤኮኖሚ ግንኙነት ለማዳበር ፍላጎት እንዳላቸውም አስረድተዋል።

“በኬንያና በጀርመን መካከል ያለውን የኤኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር እንፈልጋለን። ግን በዚህ በኩል ለመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት ዋስትና መኖሩ ግድ ነው። በተቀረ ዛሬ የኤኮኖሚ ትብብራችንን ለማሻሻል የሚረዳ የጀርመን ልፑካን ቢሮ እዚህ ናይሮቢ ውስጥ ለመክፈት በመቻላችን በጣም ደስተኛ ነኝ”

አንጌላ ሜርክል የኬንያ መንግሥት በጨረታ ረገድ ግልጽነትን እንዲያሰፍን፣ ቢሮክራሲን እንዲያስወግድና ነጻ የገበያ አግባብን እንዲያመቻችም ጠይቀዋል። ጀርመን የላሙን ወደብ በመገንባቱና እስከ ኢትዮጵያ በሚዘልቅ የአውራ ጎዳና ስራም እንድትሳተፍ ከኬንያ በኩል የቀረላትን ጥሪም ቻንስለሯ በደስታ ተቀብለዋል።

ያም ሆነ ይህ የጀርመኗ ቻንስለር በነገው ዕለት በመጨረሻ ናይጄሪያን ይጎበኛሉ። በሕዝብ ብዛት በአፍሪቃ ቀደምት የሆነችው ናይጄሪያ ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ሃብት ቢኖራትም በሌላ በኩል ኢንዱስትሪ ባለመስፋፋቱ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ ናት። እናም ይሄው የነዳጅ ዘይት ገቢ በአንድ በኩልና የውጭ ምርት ጥገኝነት በሌላው ተጣምሮ ለውጭ ኩባንያዎች ማራኪ ያደርጋታል። የአውሮፓ ሕብረት ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛው የናይጄሪያ የንግድ ሸሪክ ሲሆን ጀርመን የተሰማራችው እርግጥ በነዳጅ ዘይት ሣይሆን በተለይ በግንቢያው ዘርፍ ነው። የጀርመን ኩባንያዎች ከዚሁ ሌላ በቴሌኮሙኒኬሺን፣ በአገልግሎት ዘርፍና በታላላቅ የንግድ ማከፋፈያዎች ረገድም ተሳታፊ ሲሆኑ በጉብኝቱ ሂደት ይህንኑ ይበልጥ ለማጠናከር ጥረት እንደሚደረግ ይጠበቃል። በተረፈ የጀርመን አዲስ የአፍሪቃ ሽርክና ጽንሰ-ሃሣብ ምን ፍሬ እንደሚሰጥ ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ