1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አቶ ሽፈራው ሽጉጤ

ሰኞ፣ የካቲት 26 2010

አቶ ሽፈራው በርዕሰ መስተዳድርነታቸው ዘመን አሳኩ ተብሎ የሚጠቀስላቸው ተግባር አለ። ወደዚህ ሃላፊነት የመጡትም በወቅቱ በክልሉ የነበረውን ችግር ታሳቢ በማድረግ ነበር።

https://p.dw.com/p/2tjen
Äthiopien Shiferaw Shigute, Vorsitzender der SEPDM
ምስል Getenet Teruneh

አቶ ሽፈራው ሽጉጤ

 

የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ያስገቡትን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ሊተኩ ይችላሉ ከሚባሉት የኢህአዴግ ባለሥልጣናት መካከል የኢህአዴግ አባል ድርጅት የሆነው የደኢህዴን ሊቀመንበር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አንዱ ናቸው። በቅርቡ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ደኢህዴን ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት አቶ ሽፈራው የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነትን ጨምሮ በልዩ ልዩ ሃላፊነቶች ሰርተዋል። 
 በአሁኑ ወቅት የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽፈራው ሹጉጤ አቶ ኃይለ ማርያምን በመተካት የድርጅታቸው የደኢህዴን ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት  አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከመንግሥትም ከፓርቲም ሥልጣን እንደሚለቁ ከተናገሩ እና ስለሚተኩበት ሂደትም ካሳወቁ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነበር።  አቶ ሽፈራው በተወለዱበት ባደጉበት እና በተማሩበት በደቡብ ክልል  በልዩ ልዩ ሃላፊነቶች ሰርተዋል። በሲዳማ ዞን ሀሮሪሳ ወረዳ የተወለዱት አቶ ሽጉጤ ለከፍተኛ ሃላፊነቶች ከመብቃታቸው በፊት መምህር ነበሩ። መምህር ሳሉ ነበር የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ደኢህዴን አባል የሆኑት። ከሲቪል ሰርቪስ በአካውንቲንግ ከተመረቁ በኋላ ደግሞ ኦዲተር ሆኑ። አቶ ሞላልኝ አባይ የአዋሳ ከተማ ነዋሪ እና በደቡብ ህዝቦች ክልል የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ  የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ አባል ናቸው። አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተጠሪነቱ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ለሆነው የደቡብ ክልል ዋና ኦዲተር መስሪያቤት በኦዲተርነት ይሰሩ ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ ያውቋቸዋል። በባህርያቸው ተግባቢ ጥሩ ሠራተኛም ነበሩ ይላሉ።አቶ ሽፈራው በ1998 የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከሆኑ በኋላ  ከህዝቡ ቅሪታዎች ይነሱባቸው እንደነበር አቶ ሞላልኝ  ያስታውሳሉ። አቶ ሽፈራው በርዕሰ መስተዳድርነታቸው ዘመን አሳኩ ተብሎ የሚጠቀስላቸው ተግባር አለ። በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር አቶ ዳንኤል መኮንን እንደሚያስረዱት አቶ ሽፈራው ወደዚህ ሃላፊነት የመጡት በወቅቱ በክልሉ የነበረውን ችግር ታሳቢ በማድረግ ነው።
ርዕሰ መስተዳድር ሲሆኑ የሲዳማን ጥያቄ በማርገብ ከሞላ ገደል በተገኘው ውጤት ስኬታማ የተባሉት አቶ ሽፈራው የክልሉን ትልቁን ሃላፊነትም ከያዙ በኋላ በዘመነ ሥልጣናቸው በክልሉ እየተባባሱ ሄደዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ሙስናም ከሚወቀሱት አንዱ ነበሩ ይላሉ አቶ ዳንኤል ። አቶ ዳንኤል እንዳሉት አቶ ሽፈራው በዚህ ወቀሳ ቢገመገሙም አልተቀበሉትም። ከደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት ከተነሱ በኋላ በአቶ ኃይለማርያም ካቢኔ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት አቶ ሽፈራው በሥልጣን ዘመናቸው ጠባሳ ጥሎባቸው ያለፈ ሌላም ነገር ደርሷል። በ2008 ብሔራዊ ፈተና ሾልኮ ወጥቶ ተሠራጭቷል። በኢንተርኔት ወጥቷል። አቶ ሞላልኝ ይህ በደቡብ ክልል ሳይቀር አነጋገሪ እንደነበር ያስታውሳሉ።
አቶ ሽፈራው የትምህርት ሚኒስትር በሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈተናው  በኢንተርኔት መበተኑ ርሳቸውን ብቻ ሳይሆን መስሪያ ቤቱን አስገምቷል እንደ አቶ ዳንኤል።
አቶ ሽፈራው ለኢህአዴግ ሊቀመንበርነትም ሆነ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ብቃት የላቸውም የሚሉ በርካታ አስተያየት ሰጭዎች አሉ ። አቶ ዳንኤል ግን አቶ ኃይለ ማርያም የሥልጣን ዘመናቸውን ሳይጨርሱ በመውረዳቸው ደኢህዴን ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ለኔ ይገባል የሚል ጥያቄ ሊያቀርብ የመቻሉ እድል እንዲሁም ሃሳቡ የህወሀትን ድጋፍ ካገኘ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ  ይችሉ ይሆናል የሚል ግምት አላቸው። 

Shiferaw Shigute
ምስል E.G. Godane

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ